Monday, April 12, 2021

ሚያዝያ 5

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

ሚያዝያ 5-ጌታን በኪሩቤል ላይ እንዳለ በራእይ ያየውና ስለእመቤታችንም ዘላለማዊ ደንግልና ትንቢት የተናገረው ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሕዝቅኤል በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ 

+ የደብረ ዓሣው ታላቁ አባት አባ ዮሐኒ ልደታቸው ነው፡፡

+  የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ አካሏ የሆነ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ልደቱ ነው፡፡

+ አፍላሚ፣ ታዖድራ፣ ዋስለዲስ እና መነኩሴው አርሳኒ መታሰቢያ በዓላቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል፡- ይኽም ቅዱስ ነቢይ ሕዝቅኤል ካህንም ነቢይም ሆኖ ሲያገለግል ንጉሥ ናቡከደነጾር የእስራኤልን ልጆችን በማረካቸው ጊዜ እርሱም ተማርኮ ወደ ባቢሎን ሔደ፡፡ በባቢሎን አገርም ሳለ ትንቢትን የሚናገር ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከክብርት እመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ስለመወለዱ እርሷም አምላክን ከወለደች በኋላ ለዘላለም በድንግልና ጸንታ እንደምትኖር ትንቢት ተናገረ፡፡ ‹‹እኔ ወደ ምሥራቅ ስመለከት የተዘጋች ደጅ አየሁ፣ ይህቺ በር ተዘግታ ትኖራለች አትከፈትም፣ የሚገባባት የለም፣ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደተዘጋች ይገባባታልና ከእርሱ በቀር የሚገባም የሚወጣም የለም አለኝ›› በማለት ተናገረ፡፡

የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልናዋን መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ የተገለጸለት ድንቅ ምስጢር ሲገልጽ "ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር፤ እግዚአብሔርም ይኽ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፤ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" በማለት የዘላለማዊ ድንግልናዋን ነገር ተናግራል (ሕዝ ፵፬፥፩-፪)፡፡ ይኸውም መቅደስ የቅድስት ድንግል ማርያም፤ በር የድንግልናዋ፤ መቈለፊያው የማኅተመ ድንግልናዋ ምሳሌ፤ አምላክ ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት ሲወጣ ማየቱ እንበለ ዘርዕ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን፤ "አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" ብሎ መናገሩ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀንዋ የተሸከመቺው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ማኅተመ ድንግልናዋ የማይለወጥ ዘላለማዊት ድንግል መኾኗን ሲገልጽለት ነው፡፡ ለነቢዩ ሕዝቅኤል የተገለጸለትን ይኽነን አስደናቂ ምስጢር ሊቁ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ዘእንዚናዙ ሲተረጒም "ከመ ኆኅት ዘርእየ ሕዝቅኤል ነቢይ ዘኢቦአ ውስቴታ ብእሲ ዘእንበለ አምላከ እስራኤል ቦአ ውስቴታ ወወጽአ እንዘ ኢይትረኀው ኆኅት ኢታስተማስሉኬ ኦ አብዳን ፅንሳ ለእግዝእትነ ማርያም ወወሊዶታ ከመ ኲሎን አንስት ሐሰ ላቲ ለእግዝእትነ ማርያም አላ ፀንሰቶ ለቃለ እግዚአብሔር ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ ወወለደቶ ዘእንበለ ፃዕር ወሕማም ወኢያእመረት ወኢተዐውቃ ፍጹመ ሕማመ ወሊድ ወበእንተዝ ፅንሳ ይትነከር ወኀይለ ዕበየ ወሊዶታ ኢይትነገር ወከመዝ ወለደት ዘኢይረክቦ መኑሂ ክዋኔሁ ወኢተነሥተ ማኅተመ ድንግልናሃ" (ከእስራኤል ፈጣሪ በቀር ሰው እንዳልገባበት ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዳያት ደጃፍ ማኅተመ ድንግልዋ ሳይለወጥ በኅቱም ድንግልናዋ ተፀንሶ ተወለደ፤ እናንት አላዋቆች የእመቤታችን የማርያምን ፅንሷንና መውለዷን እንደ ሌሎች ሴቶች ኹሉ አታስመስሉ፤ ለእመቤታችን ለማርያም በፅንስና በወሊድ በሌሎች ሴቶች መመሰል አይገባትም፤ የእግዚአብሔር ቃልን ያለወንድ ዘር ፀነሰቺው፤ ያለ ጭንቅና ያለምጥም ወለደቺው እንጂ፤ በመውለድ ጊዜ የሚኾን ምጥ ፈጽሞ አላገኛትም፤ ስለዚኽ መፅነሷ በጣም ይደነቃል፤ የመውለዷ ምስጢር ኀይልም አይመረመርም፤ ማንም ማን ባሕርዩን የማያውቀው ርሱን ወለደችው፤ ማኅተመ ድንግልናዋም አልተለወጠም) በማለት የወላዲተ አምላክ ምሳሌ ስለኾነቺው ነቢዩ ሕዝቅኤል ስላያት የተዘጋች ደጃፍ በስፋትና በጥልቀት አስተምሯል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ እንዚራ የተባለው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት የረቡዕ ውዳሴ ማርያም መጽሐፉ ላይ "ሕዝቅኤል ነቢይ ኮነ ስምዐ በእንቲአሃ ወይቤ ርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦአ ዘእንበለ እግዚአ ኀያላን ቦአ ውስቴታ ወወፅአ" (ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለርሷ መሰከረ ድንቅ በኾነ ታላቅ ቊልፍ የተዘጋች ደጅ በምሥራቅ አየኊ አለ፤ ከኀያላን ጌታ በቀር ወደርሷ ገብቶ የወጣ የለም) "ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ እንተ ወለደት ለነ መድኅነ እምድኅረ ወለደት ኪያሁ ነበረት በድንግልና ከመ ትካት" (ደጃፍም የተባለች መድኀኒታችንን የወለደች ድንግል ናት፤ ርሱን ከወለደች በኋላ እንደቀድሞው በድንግልና ኖራለች) በማለት አምላክን ከመውለዷ በፊት ድንግል፤ ከወለደችውም በኋላ ድንግል መኾኗ ነቢዩ ሕዝቅኤል ባያት ራእይ አስቀድሞ የተገለጸ መኾኑን መስክሯል፡፡ ይኽ የእመቤታችን ጣዕመ ውዳሴዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም በድጋሚ በድርሳኑ ላይ "Ezekiel, born in the captivity... " (በምርኮ የተወለደው ሕዝቅኤል የዳዊት ሴት ልጅ የኾነችውን ድንግል በትንቢት ዐይን አይቶ ነበር፤ እንዲኹም ከእግዚአብሔር በተላከው የርሱ ራእይ ውስጥ የድንግልናዋን አምሳል ገለጸ፤ በከለዳውያን ምድር ትንቢት የማርያምን አምሳል አሳየ፤ ርሷንም በነቢያት መጻሕፍት አስቀመጣት፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም የርሷን ታሪክ አስጠበቀ፤ ስለዚኽም ማንም ሰው ይኽነን በማንበብ ሊረዳ ይችላልና፤ በሩ በጥብቅ ተዘግቶ እንደሚኖር "እግዚአብሔር ገብቶታል ተዘግቶ ይኖራል" በማለት ጌታ ለነቢዩ በካህናት ጉባኤ መኻከል ገልጾለታልና) ሲል ጌታ አስቀድሞ ስለ እናቱ ዘላለማዊ ድንግልና በሕዝቅኤል ዐድሮ ማናገሩን ገልጾታል፡፡

 

ዳግመኛም ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል ስለ ክርስትና ጥምቀት ትንቢት ሲናገር ‹‹በንጹሕ ውኃ እረጫችኋለሁ ከኃጢአታችሁም ከእርኩሰታችሁም ሁሉ ትነጻላችሁ፡፡ አዲስ ልብስ እሰጣችኋለሁ፣ አዲስ ዕውቀትንም አሳድርባችኋለሁ፡፡ ድንቁርና ያለበትንም ልብ ከሰውነታችሁ አርቄ ዕውቀት ልብ እሰጣችኋለሁ›› አለ፡፡ የጥምቀት ልጆችም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚሆኑ ተናገረ፡፡

ካህናቱም ሕዝቡን ማስተማራቸውን ስለተው ገሥጾዋቸዋል፡፡ ‹‹…ካላስተማራችኋቸውና ካላነቃችኋቸው እግዚአብሔር የሰዎቹን ነፍስ ከእናንተ ይፈልጋል›› እያለ ካህናቱን ገሥጾዋቸዋል፡፡ ዳግመኛም ነቢዩ ነፍስ በዕለተ ትንሣኤ ከሥጋ ጋር ተዋሕዳ ለፍርድ እንደምትቀርብ ትንቢት ተናገረ፡፡ ትንቢቶቹም ብዙ ናቸው፡፡

እግዚአብሔርም በነቢዩ በቅዱስ ሕዝቅኤል እጆች ብዙ አስገራሚ ተአምራትን አድርጓል፡፡ የእስራኤልም ልጆች በባቢሎን ሳሉ ጣዖትን ባመለኩ ጊዜ ገሥጾዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አለቆቻቸው በነቢዩ ላይ በክፋት ተነሥተውበት በግፍ ገድለውታል፡፡ የትንቢቱም ዘመን 20 ዓመት ነው፡፡

የነቢዩ የቅዱስ ሕዝቅኤል ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን! 

+ + + + +

ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ አካሏ የሆነ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ልደቱ ነው፡፡ ሙሉ ታሪኩን በዓመታዊ የዕረፍት በዓሉ ዕለት ግንቦት 11 ቀን እናየዋለን፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!

 

+ + + + + 

የደብረ ዓሣው ታላቁ አባት አባ ዮሐኒ፡-  መጽሐፍ አባታቸውን ዘስዩመ ተንቤን እሁሁ ይላቸዋል፡፡ እናታቸው ደግሞ ዓመተ መንፈስ ቅዱስ የሚባሉ ደገኛ ምግብራቸው ያማሩ ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ አቡነ አሞኒ የካቲት 5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆቻቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንደጢስ በነው ጠፍተዋል፡፡ አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው፡፡

 

አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖላቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው፡፡ በደመና ተጭነው ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ እብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል፡፡ አባ ዮሐኒን ያሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡ መነሻ ታሪኩም እንዲህ ነው፡-

 

የተንቤን አውራጃ ገዥ የነበረው ሰው በዘመኑ ዐፄ ካሌብ የነበሩበት ዘመን ነበርና አብሯቸው ወደ ምድረ ኖባ ሄደው ሰባት ዓመታትን የፈጀ የጦር ዘመቻ ክርስያኖችን በሚያሠቃዩ ነገሥታት ላይ አዳሄዱ፡፡ የተንቤኑ አውራጃ ገዥም ወደ ዘመቻው ከሄደ ቆይቶ ነበርና ታናሽ ወንድሙ የገዥውን ሚስት ‹‹ወንድሜ የቀረው ሞቶ ነው እንደ ኦሪቱ ሕግ እኔው ላግበሽና ልጆቹን ላሳድግ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ባሌ ቢሞት ይነገረኝ ነበረዘመቻ የሄደው ሁሉ አልተመሰም›› ብላ እምቢ ብትለው በግድ ተገናኛት፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ዮሐኒ ተፀነሱ፡፡ በሚያዝያ 5 ቀንም ተወለዱ፡፡

 

ከዘጠኝ ወር በኋላ ማሏ ከዘመቻ መጣና ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ የአካባቢውም ሰው ወጥቶ በክብር ሲቀበለው ሚስቱ ግን ምጥ ተይዛ ታማ ስለነበር ወጥታ አልተቀበለችውም፡፡ ‹‹የት ሄደች? ምንስ ሆነች?›› ብሎ ሲጠይቅ ልጅ አይደብቅምና አንድ ሕፃን ‹‹አርግዛ ልትወልድ በምጥ ላይ ትገኛለች›› አለው፡፡ የአውራጃውም ገዥ ያለችበት ድረስ ሄዶ ቢያያት ያማረ ወንድ ልጅ ታቅፋ አገኛት፡፡ ከዚህም በኋላ ከቤቱ ምሰሶ ጋር ጥፍንግ አድርግ አስሮ እየገረፋትና እያስጨነቃት ከማን እንዳረገዘች ጠየቃት፡፡ እርሷም የወንድሙን ምሥጢር ለመጠበቅና ወንድማማቾቹን ላለማጣላት ሥቃዩን ታግሳ ዝም አለች፡፡ በዚህ ቅጽበት የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤል 40 ዓመት ሙሉ ዘግተው በበረሃ ለሚኖሩት ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸው እንደ አውሎ ነፋስ አምዘግዝጎ ወስዶ አውራጃ አገረ ገዥው ቤት አደረሳቸው፡፡

 

እንደደረሱ ዓመተ ማርያም በጽኑ ድብደባና ግርፋት እየተሠቃየች እያለ አባ አሞኒ የጸጉራቸውን አጽፍ ለብሰው ራቁታቸውን ደጇ ላይ ቆመው አየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ለባሏ ‹‹ያውና ከዚህ መነኩሴ ነው የወለድኩት›› አለቸው፡፡ አተንቤቱ አውራጃ አገረ ገዥውም አባ አሞኒን ይዞ ጽኑውን ግርፋት በወታደሮቹ አስገረፋቸው፡፡ በመቀጠልም ገና የእናቱን ወተት እንኳን ያልቀመሰውን ጨቅላ ሕፃን አንሥቶ ‹‹እንካ ልጅህን ይዘህ ጥፋ ከዚህ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡ አባ አሞኒም በዚህ ጊዜ ‹‹ዮ ሀበኒ ዮ ሀበኒ›› አሉ፡፡ በትግርኛ እሽ ስጠኝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ሕፃኑ በኋላ ላይ ‹‹አባ ዮሐኒ›› የተባሉት፡፡ አባ አሞኒም ሕፃኑን ተረክበው ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ ሥር ሄደው ልጁን ከወይራ ዛፍ ሥር አስተኝተው ‹‹አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ኃጢአቴን ተመራምረህ ይህንን ሕፃን የሰጠኸኝ አላጠባው ጡት የለኝ አላበላው እህል የለኝ›› ብለው የጨቅላው ሕፃን ነገር እጅግ ቢያስጨንቃቸው ምርር ብለው አለቀሱ፡፡ ጸሎታቸውንም እንደጨረሱ ተራራውን በመስቀል ምልክት ቢባርኩት በተራራው መሐል ላይ እንደመደብ ያለ አልጋ በተአምራት ተሠርቶ አገኙት፡፡ ሕፃኑንም ከዚያ አስተኝተው ድጋሚ ጸሎት ሲጀምሩ ቶራ (ሰሳ) መጥታ እግርና እግሯን አንፈራጣ ሕፃኑን አጠባችውና ሄደች፡፡

 

አባ አሞኒም በዚህ ደስ ተሰኝተው ሕፃኑን ‹‹የምግብህ ነገር ከተያዘ ግዴለም›› ብለው ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ አድረው መለስ ቢሉ ዳግመኛም ሕፃኑን የታዘዘ ንስር አሞራ በክንፎቹ ጋርዶ አልብሶትና አቅፎት እንዳደረ ተመለከቱ፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ተኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ቀን ቀን ቶራዋ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራው አልብሶት እያደረ ሕፃኑ ሦስት ዓመት ሆነው፡፡ አባ አሞኒም ከሰባት ዓመቱ ጀምረው እስከ 12 ዓመቱ ድረስ ፊደል፣ ንባብ ከነትርጓሜው፣ ብሉይንና ሐዲስን፣ ምግባር ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስያንን ሁሉ አስተማሩት፡፡

 

አባ አሞኒ ልጃቸው አድጎ 12 ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዓሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን ‹‹አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድናቸው? እንደእኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?›› አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም ‹‹አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ›› አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው ‹‹በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?›› ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡

ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡

 

አባ ዮሐኒ 20 ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ 40 በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና ‹‹አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው ‹‹በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ›› አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው ‹‹አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ›› ብለው ነግረዋቸው በዛሬዋ ዕለት ኅዳር 5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡

 

አባ አሞኒ ካረፉ ከ12 ዓመት በኋላ የአባ ዮሐኒ ወላጅ እናታቸው የልጇን ነገር ስታጠና ኖራ ነበርና አሁን ባሏም ስለሞተ አባ አሞኒም ስላረፉ ልጇን ልታይ ከ32 ዓመት በኋላ መጣች፡፡ ቀሚስ ለብሳ ፀጉሯን ተሠርታ በሴትነቷ ልጇ ካለበት ቦታ በመሄድ ማነጋገር እንደማትችል ስላወቀች ፀጉሯን ተላጭታ የወንድ ልብስ ቁምጣ ለብሳ በሁለመናዋ ወንድ መስላ ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ አመራች፡፡ እዚያም እንደደረሰች በቅዱሳን ሥርዓት መሥረት ሦስት ጊዜ ‹‹አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን›› አለች፡፡ ሰይጣን ይህን ስም ሲሰማ 40 ክንድ ይርቃል፡፡ የደብረ ዳሞ መነኮሳት እንደ ሰላምታ መለዋወጫ ይጠቀሙበታል፡፡ አባ ዮሐኒም ይህን ድምጽ ከውጭ በሰሙ ጊዜ ‹‹አንተ ማነህ?›› አሉ፡፡ እርሷም ‹‹ዓመተ መንፈስ ቅዱስ ነኝ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም አንድም ድምፁዋ ወትሮ ከሚያውቁት ድምፅ ስተለየባቸው ደግሞም ትዝ ሲላቸው እነዚያ እንስራ አዝለው ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ሆነው ውኃ ቀድተው ሲሄዱ በመነገድ ያዩአቸው ሴቶች ድምፅ ሆነባቸው፡፡ ደግሞም ‹‹ወልደ እከሌ፣ ክንፈ እከሌ›› ሲባል እንጂ ‹‹ዓመተ፣ ወለተ›› ሲባል ሰምተው አያውቁም ነበርና አባታቸው አባ አሞኒ የነገሯቸው ትዝ አላቸው፡፡ በዚያውም ቅጽበት የሚጽፉባትን ብዕር ጆሮአቸው ላይ እንደሰኩ 500 ሜትር ርዝመት ካለው ትልቅ ተራራ ላይ ራሳቸውን ቁልቁል ወረወሩ፡፡ ነገር ግን መሬት ሳይደርሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአየር ላይ እንዳሉ ተቀበላቸው፡፡ ብዕራቸው ግን መሬት ላይ ወድቃ ሸምበቆ ሆነች፡፡ ወዲያውም አባ ዮሐኒ ክንፍ አውጥተው ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ጎን ለጎን ሆነው በዛሬው ዕለት ኅዳር 5 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ይዟቸው ገባ፡፡

 

ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው?›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን/›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡  

 

ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ደብረ ዓሣ ተመልሶ መጥቶ ለአባ አበይዶ ተገለጠላቸውና አባ ዮሐኒን ብሔረ ሕያዋን እንዳስገባው ነገራቸው፡፡ በመጀመሪያ ሄኖክና ኤልያስ አላስገባ ብለው እንደነበርና በኋላም መልአኩ ራሱ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን ከነገራቸው በኋላ በምስጋና እንደተቀበሉት ለአባ አበይዶ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን እንዲጽፉትና እንዲያስተምሩበት ለአባ አበይዶ አዘዛቸውና ዐረገ፡፡ አባ አበይዶም አባ ዮሐኒ ከገደሉ ተወርውረው ሲወደቁ አንድ ደስ የሚል ወንድ ሲቀበለው አይተው ነበርና አሁን መልአኩ ሲነግራቸው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አባ አበይዶም በመልአኩ በታዘዙት መሠረት የአባ ዮሐኒን ገድል ጻፉት፡፡

የአባ ዮሐኒ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!

 

kegdedlat andebet yetewesede                                                                    

Telegram: https://t.me/tewhahdohaimanotachin  

 LIKE OUR PAGE https://www.facebook.coBm/tewadhdohaimanotachin

Thursday, April 8, 2021

ሚያዝያ 1

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

ሚያዝያ 1-የእመቤታችን ምሳሌ የተገለጠለት የሙሴ ወንድም ካህኑ አሮን ዕረፍቱ ነው፡፡

+ በሕይወተ ሥጋ ሳለ ገነትንና ሲኦልን በግልጽ ያየ የከበረ አባ ስልዋኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡ 

+ ታላቁ ሰማዕት አባ ብሶይ ልደታቸው ነው፡፡  

+ ጌታችን የአባ መቃርስ ገዳም መነኮሳትን ጸሎታቸውን ሰምቶ ከዐረቦች ወረራ ጠበቃቸው፡፡ 

+ ቅድስት መጥሮንያ ዕረፍቷ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳታል፡፡   

+ ከአበከረዙን ጋር በሰማዕትነት ያረፉት ቅዱስ ዮስጦስና ሚስቱ መታሰቢያቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡   

ካህኑ ቅዱስ አሮን፡- አሮን ማለት ‹‹ደብረ እግዚአብሔር›› ማለት ነው፡፡ ከሌዊ ነገድ ሲሆን የሊቀ ነቢያት ሙሴ ወንድም ነው፡፡ የቤተ መቅደሱ የደብተራ ኦሪቱ አገልጋይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር በእጆቹ ታላላቅ አስደናቂ ተአምራትን አድርጓል፡፡ የቆሬም ልጁች በጠላትነት በተነሡበ ጊዜ እግዚአብሔር ፈርዶ አጥፍቷቸዋል፣ ምድርንም አዘዛትና አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሞተ በኋላ እስራኤልን የመራቸው አሮን ነው፡፡ እርሱም ሲሞት ልጁ አልዓዛር የካህናት አለቃ ሆኖ እስራኤልን መርቷቸዋል፡፡ ሙሴን እግዚአብሔር አዞት ወደ ደብረ ሲና ተራራ ወጥቶ ታቦተ ጽዮንን ከመቀበሉ በፊት 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጾም ስለዘገየባቸው እስራኤላውያን በአሮን ላይ በነገር ተነሡበት፡፡ ‹‹በፊታችን የሚሄዱልን አማልክት ሥራልን›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ የሚባል ሰው ምን እንደሆነ አናውቅም፣ ወደ ግብፅ ተመልሶ ሄዶ እንደሆነ ወይም በደብረ ሲና ያያት እሳት አቃጥላው እንደሆነ አናውቅም›› አሉት፡፡ አሮንም ‹‹ወርቃችሁን ሰብስባችሁ አምጡ›› አላቸው፡፡ አሮን እንዲህ ማለቱ ‹‹እስራኤላውያን እጅግ ክፉዎችና ቁጡዎች ስለሆኑ በድንጋይ ወግረው በእሳት አቃጥለው ይገድሉኛል፣ ይሁን ብላቸውም እግዚአብሔር ይፈርድብኛል የወርቅ ጌጣቸውን አምጡ ያልኳቸው እንደሆነ ግን እስራኤል ገንዘብ እጅግ ወዳጆችና ስስታሞች ስለሆኑ በወርቃችሁ ልሥራላችሁ ብላቸው ጨክነው ወርቃቸውን አይሰጡኝም ነገ ከነገ ወዲያ ሲሉ ወንድሜ ሙሴ ይመጣልኛል ከነገርም እድናለሁ›› ብሎ ስላሰበ ነው፡፡ ዳግመኛም አሮን ወርቁ ጠፍቶና ቀልጦ ይቀራል ብሎ በማሰብ ጉድጓድ ቆፍሮ እሳት አንድዶ ወርቁን ሁሉ ከዚያ ቢጥለው ሰይጣን የጥጃ ምስል አድርጎት ከጉድጓዱ አወጣው፡፡ (ኦሪት ዘጸአት አንድምታ ትርጓሜ፡፡) 

የአሮን በትሩ የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ እነ አቤሮንና ዳታን ደጋፊዎቻቸውም ጭምር በሙሴና በአሮን ሹመት ላይ በጠላትነት በመነሣታቸው ምድር ተከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ከ12ቱ የእስራኤል ነገድ 12 በትር ወስዶ የእያንዳንዱንም ስም በበትራቸው ላይ ጽፎ በመገናኛው ድንኳን በመስክሩ ታቦት ፊት እንዲያኖራቸው አዘዘው፡፡ እግዚአብሔርም ለሹመቱ የመረጠው ሰው በትሩ እንደምታቆጠቁጥ ነገረው፡፡ ሙሴም እንደታዘዘው አድርጎ ሲጸልይባቸው አድሮ በትሮቹን ቢያወጣቸው የአሮን በትር ከሌሎቹ በትሮች ተለይታ ሳይተክሏት በቅላ፣ ውሃ ሳያጠጧት ለምልማ፣ አብባ፣ የበሰለ ለውዝ አፍርታ ተገኝታለች፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ያች በትር ለሚያምፁ ልጆች ሁሉ ምልክት ሆና እንድትጠበቅ አዘዞታል፡፡ በኦሪት ዘኁልቅ 7፡1-10 ላይ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው›› ተብሎ ነው የተጻው፡፡ ይኸውም ምሳሌ ነው፡፡ ለጊዜው እስራኤል በሹመት ምክንያት ተጣልተዋልና በዚህ ለይቷቸዋል፡፡ ፍጻሜው ግን የአሮን በትር ከሌሎች ተለይታ ለምልማ አብባ ፍሬ አፍርታ እንደተገኘች ሁሉ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሌሎች ከእስራኤል ሴቶች ተለይታ በሥጋ፣ በነፍስ፣ በልቡና አብባ አጊጣ ያለዘር ያለሩካቤ በድንግልና ወልዳ ተገኝታለችና በእውነት የአሮን በትሩ የወላዲተ አምላክ ምሳሌ ናት፡፡ ይህንንም ሊቃውንት አባቶቻችን እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ ያሬድና እነ አባ ጊዮርጊስ በሚገባ አመስጥረውታል፡፡ እንደመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ የአሮን በትር እንዳይሞቱ ለሚያምፁ ልጆች ምልክት ሆና እንደተጠበቀች ሁሉ ድንግል ማርያምም ለእኛም ለሐዲስ ክርስቲኖች በኃጢአት እንዳንሞት ምልክት ሆና ተሰጥታናለች፡፡ ነቢያቱም ‹‹ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች….›› እያሉ የነገሩንም ይህንኑ ነው፡፡ ኢሳ 7፡14፡፡ ቅዱስ አሮንም በበጎ ተጋድሎውና የኦሪትንም ሕግ በመጠበቅ እግዚአብሔርን ካገለገለ በኋላ ሚያዝያ 1 ቀን በሖር ተራራ ላይ ሲያርፍ እስራኤላውያን 30 ቀን አልቅሰውለታል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን! 

+ + +


ሰማዕቱ አባ ብሶይ፡- አማኝ ክርስቲያን የሆኑ ወላጆቻቸው ልጅ ሳይኖራቸው 17 ዓመት ኖረዋል፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ብርሃንን የለበሰ ጻድቅ ሰው ወደ አባቱ መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልድና ስሙን ብሶይ እንደሚለው ልጁም በመጨረሻ ሰማዕት እንደሚሆን ነገረው፡፡ ብሶይም ሚያዝያ 1 ቀን ተወለደና በሃይማኖት ኮትኩተው አሳደጉት፡፡ ለመምህርም ሰጡትና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ ተማረ፡፡ በ27 ዓመቱም ክርስቲያኖችን ይገድል ወደ ነበረው ከሃዲ ንጉሥ ዘንድ ሄዶ ክርስቲያን መሆኑን ተናገረ፡፡ ንጉሡም አሳሰረውና በማግሥቱ ለጣዖቱ እንዲሰግድ አዘዘው፡፡ አባ ቢሶይም የንጉሡን ትእዛዝ መቀበልን እምቢ ባለ ጊዜ ንጉሡ ይዞ እጅግ አሠቃየው፡፡ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ ተገልጾ አበረታው፡፡ 


ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ቁልቁልያኖስ ወደሚባል መኰንን ላኩት፡፡ ይህም ከሀዲ መኰንን ‹‹ለምን ለጣዖቶቻችን አትሰግድም?›› ብሎ ብዙ አሠቃየው፡፡ በብረት ችንካሮች ዐይኖቹን አወጣቸው፣ በፈላ ውኃ ውስጥም ጨመሩት፣ እጆቹንና እግሮቹንም በየተራ ቆረጧቸው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም የተቆራረጡ አካሎቹን ሁሉንም ፈውሶ እንደቀድሞው አንድ አደረጋቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ሀገርም አመጡትና ለዲዮቅልጥያኖስ አስረከቡት፡፡ እርሱም በተራው እጅግ ጽኑ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ሰኔ 5 ቀንም አንገቱን በሰይፍ አስቆርጦት የሰማዕትነት ፍጻሜ ሆኖ የክብርን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ የሰማዕቱ የአባ ብሶይ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን! 

+ + +  kegdedlat andebet yetewesede                                                                     

Telegram: https://t.me/tewhahdohaimanotachin                                    

LIKE OUR PAGE https://www.facebook.coBm/tewadhdohaimanotachin

Wednesday, June 19, 2019

ሰኔ 13 እና 14


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

<3 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

ሰኔ 13 እና 14

+ ከታላቁ ጻድቅ ከቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጋር በታናሽነቱ በአባ ኤስድሮስ ገዳም መንኩሶ በታላቅ ተጋድሎ የኖረው የኢየሩሳሌሙ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ዮሐንስም በሹመቱ ሳለ ገንዘብን በመውደድ ጌታችንን ቢያሳዝነው ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዐይኖቹን አሳውሮ በኋላም እንደገና መልሶ አንድ ዐይኑን በማብራት በተአምራት ወደ ንስሓ የመለሰው ነው፡፡

+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የሄኖስ ልጅ ቃይናን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ቃይናንም 170 ዓመት ኖሮ መላልዔልን ወደለደው፡፡ መላልዔልንም ከወለደው በኋላ 740 ዓመት ኖረ፡፡ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፡፡ የቃይናንም መላ ዘመኑ 910 ዓመት ሲሆነው በዚህች ዕለት ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

+ + + + +
አቡነ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም፡- ይኸውም ቅዱስ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ሲሆን ከታላቁ ጻድቅ ከአቡነ ኤጲፋንዮስ ጋር በታናሽነቱ በአባ ኤስድሮስ ገዳም መንኩሶ በታላቅ ተጋድሎ ይኖር የነበረ ነው፡፡ የእርሱም ደግነቱ፣ ትሩፋቱ፣ ቅድስናውና ታላቅ ተጋድሎው በቦታው ሁሉ ተሰማ፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ኤጲፋንዮስን በቆጵሮስ ሀገር ኤጲስቆጶስ አድርገው ሲሾሙት አቡነ ዮሐንስን ደግሞ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አድገው ሾሙት፡፡

አቡነ ዮሐንስም በሹመት በነበረ ጊዜ ሰይጣን በገንዘብ ፍቅርና በዚህ ዓለም ክብር አሳተው፡፡ የቀድሞ ግብሩን እረስቶ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች የማይራራ ሆነና ቁራሽ እንጀራን እንኳን የማይሰጣቸው ሆነ፡፡ ይልቁንም ለራሱ ብዙ ገንዘብ ሰብስቦ ለማዕዱ የሚመገብበትን የወርቅና የብር ሣህን አሠራና በድሎት የሚኖር ሆነ፡፡
አቡነ ኤጲፋንዮስም ይህን በሰማ ጊዜ የአቡነ ዮሐንስን የቀድሞውን ተጋድሎውንና የዓለም መናኒነቱን፣ ፍቅሩንም አስታውሶ እጅግ አዘነ፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ መንፈሳዊ ወንድሙና ወዳጁ ነበር፡፡ ስለዚህም ብፁዕ ኤጲፋንዮስ ከቆጵሮስ ተነሥቶ ወደ ኢየሩሰሌም ወደ አቡነ ዮሐንስ መጣ፡፡ ከስሕተቱ ይመልሰውና በጥበብ ያድነው ዘንድ አስቦ የጌታችን መቃብር ባለበት ቤተ መቅደስ ለመስገድ እንደመጣ ነገረው፡፡ በተገናኙም ጊዜ አቡነ ዮሐንስ አቡነ ኤጲፋንዮስን ወደ ቤቱ አስገብቶ ማዕድ አዘጋጀለት፡፡ በማዕዱም ላይ በወርቅና በብር ያሠራቸውን ሣህኖቹን አስቀመጠ፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ ወደ አንዱ ገዳም ሄዶ አደረ፡፡ ወደ አቡነ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መልእክት ላከ፡- ‹‹ወንድሜ ሆይ ከቆጵሮስ ሀገር ሽማግሎችና የሕዝቡ መምህራን ወደ እኔ መጥተዋልና በእነርሱ ፊት ታከብረኝ ዘንድ ከወርቅና ከብር ያሠራሃቸውን የማዕድ ዕቃዎችህን ይመገቡባቸው ዘንድ እንድትክልኝ›› ብሎ መልእክት ላከበት፡፡ አቡነ ዮሐንስም የከበሩ ዕቃዎቹን ላከለት፡፡

አቡነ ኤጲፋንዮስም የከበሩ የማዕድ ዕቃዎቹን ወስዶ ሸጣቸውና ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተው፡፡ ሁለቱም በተገናኙ ጊዜ አቡነ ዮሐንስ ‹‹የላኩልህን የከበሩ የማዕድ ዕቃዎቼን መልስልኝ›› አለው፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስም ‹‹እሺ›› አለው፡፡ በሌላ ጊዜም እስከ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ጠየቀው፡፡ በአንዲት ዕለትም የጌታችን መቃብር ካለበት ቤተ መቅደስ ሲወጣ አግኝቶ ያዘውና ‹‹ንብረቶቼን ካልሰጠኸኝ›› ብሎ ያዘው፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስም ወደ ጌታችን ቢጸልይ የአቡነ ዮሐንስ ሁለት ዐይኖቹ ወዲያው ታወሩ፡፡ እርሱም እጅግ ደንግጦ ይቅር ይለው ዘንድ አቡነ ኤጲፋንዮስን ለመነው፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስም የእውነት መጸጸቱን አይቶ አንዲቱን ዐይኑን አበራለት፡፡ እንዲህም አለው፡- ‹‹ነፍስህን ታስብ ዘንድ አንዲቷን ዐይንህን ዕውር እንደሆነች ትቀር ዘንድ ጌታችን ትቶልሃል›› ብሎ ገሠጸው፡፡ ‹‹እነሆ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀድሞ ድካምህንና ተጋድሎን አስቦ እራርቶልሃልና ከስሕተትህም አድኖሃል›› አለው፡፡
ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አቡነ ዮሐንስ ከእንቅልፉ እንደነቃ ሆኖ የቀድሞ መልካም ሥራውንም መሥራት ጀመረ፡፡ ምንም ሳያስቀር ጥሪቱን ሁሉ አውጥቶ በመሸጥ መጸወተው፡፡ ተጋድሎውንም እንደበፊቱ በጽኑ ጀመረ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን የመፈወስ ሀብት ሰጠው፡፡ ብዙ አስገራሚ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ብዙ ካገለገለና ጌታችንም ታላቅ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + +

ሰኔ 14-የከበሩ ቅዱሳን አክራ፣ ዮሐንስ፣ አብጥልማ እና ፊሊጶስ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ እነዚህም አራት የከበሩ ቅዱሳን በጌታችን ስም ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ በምክር ተስማሙ፡፡ አክራና ፊሊጶስ ወንድማማቾች ሲሆኑ እነርሱም የከበሩ ባለጸጎች ናቸው፡፡ ዮሐንስና አብጥልማ ግን የከበሩ ቀሳውስት ናቸው፡፡ አራቱም ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ ከተስማሙ በኋላ ቀርጥስ ወደሚባል አገር ሄደው በከሃዲው መኮንንነ ፊት ቆመው የጌታችንን አምላክነት መሰከሩ፡፡ መኮንኑም በቀስት እንዲነድፏቸው አዘዘ፡፡ ነገር ግን ቀስቶቹ ሳይነኳቸው ቀሩ፡፡
ዳግመኛም በእቶን እሳት ውስጥ ጨመሯቸው፣ ጌታችንም መልአኩን ልኮ አዳናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በፈረሶች ጅራት ላይ አሥረው ከቀርጥስ እስከ ይምንሑር አገር ድረስ ጎተቷቸው፡፡ አሁንም ጌታችን ፈውሳቸውና ምንም ጉዳት እንዳላገኛቸው ሆኑ፡፡ ከዚህም በኋላ መኮንኑ ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራስ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ፡፡ እንደትእዛዙም ከይምንሑር ከተማ አውጥተው በሰይፍ አንገታቸውን ቆረጧቸውና የሰማዕትነታቸው ፍጻሜ ሆነ፡፡ እነርሱም የክብርን አክሊል ተቀዳጁ፡፡
ፃ ከምትባል አገር ሰዎቸ መጥተው የቅዱስ አክራን ሥጋ ወሰዱ፡፡ ከይምንሑር ከተማ የመጡ ሰዎች ደግሞ የቅዱስ ፊሊጶስን፣ የቅዱስ ዮሐንስንና የቅዱስ አብጥልማ ሥጋቸውን ወስደው ለሁሉም የተዋቡ አብያተ ክርስቲያናትን ሠርተውላቸው የሰማዕታትን ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ፡፡ ከቅዱሳኑም ሥጋ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/tewadhdohaimanotachin
https://ttewahdo.blogspot.com/