Thursday, April 8, 2021

ሚያዝያ 1

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

ሚያዝያ 1-የእመቤታችን ምሳሌ የተገለጠለት የሙሴ ወንድም ካህኑ አሮን ዕረፍቱ ነው፡፡

+ በሕይወተ ሥጋ ሳለ ገነትንና ሲኦልን በግልጽ ያየ የከበረ አባ ስልዋኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡ 

+ ታላቁ ሰማዕት አባ ብሶይ ልደታቸው ነው፡፡  

+ ጌታችን የአባ መቃርስ ገዳም መነኮሳትን ጸሎታቸውን ሰምቶ ከዐረቦች ወረራ ጠበቃቸው፡፡ 

+ ቅድስት መጥሮንያ ዕረፍቷ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳታል፡፡   

+ ከአበከረዙን ጋር በሰማዕትነት ያረፉት ቅዱስ ዮስጦስና ሚስቱ መታሰቢያቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡   

ካህኑ ቅዱስ አሮን፡- አሮን ማለት ‹‹ደብረ እግዚአብሔር›› ማለት ነው፡፡ ከሌዊ ነገድ ሲሆን የሊቀ ነቢያት ሙሴ ወንድም ነው፡፡ የቤተ መቅደሱ የደብተራ ኦሪቱ አገልጋይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር በእጆቹ ታላላቅ አስደናቂ ተአምራትን አድርጓል፡፡ የቆሬም ልጁች በጠላትነት በተነሡበ ጊዜ እግዚአብሔር ፈርዶ አጥፍቷቸዋል፣ ምድርንም አዘዛትና አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሞተ በኋላ እስራኤልን የመራቸው አሮን ነው፡፡ እርሱም ሲሞት ልጁ አልዓዛር የካህናት አለቃ ሆኖ እስራኤልን መርቷቸዋል፡፡ ሙሴን እግዚአብሔር አዞት ወደ ደብረ ሲና ተራራ ወጥቶ ታቦተ ጽዮንን ከመቀበሉ በፊት 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጾም ስለዘገየባቸው እስራኤላውያን በአሮን ላይ በነገር ተነሡበት፡፡ ‹‹በፊታችን የሚሄዱልን አማልክት ሥራልን›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ የሚባል ሰው ምን እንደሆነ አናውቅም፣ ወደ ግብፅ ተመልሶ ሄዶ እንደሆነ ወይም በደብረ ሲና ያያት እሳት አቃጥላው እንደሆነ አናውቅም›› አሉት፡፡ አሮንም ‹‹ወርቃችሁን ሰብስባችሁ አምጡ›› አላቸው፡፡ አሮን እንዲህ ማለቱ ‹‹እስራኤላውያን እጅግ ክፉዎችና ቁጡዎች ስለሆኑ በድንጋይ ወግረው በእሳት አቃጥለው ይገድሉኛል፣ ይሁን ብላቸውም እግዚአብሔር ይፈርድብኛል የወርቅ ጌጣቸውን አምጡ ያልኳቸው እንደሆነ ግን እስራኤል ገንዘብ እጅግ ወዳጆችና ስስታሞች ስለሆኑ በወርቃችሁ ልሥራላችሁ ብላቸው ጨክነው ወርቃቸውን አይሰጡኝም ነገ ከነገ ወዲያ ሲሉ ወንድሜ ሙሴ ይመጣልኛል ከነገርም እድናለሁ›› ብሎ ስላሰበ ነው፡፡ ዳግመኛም አሮን ወርቁ ጠፍቶና ቀልጦ ይቀራል ብሎ በማሰብ ጉድጓድ ቆፍሮ እሳት አንድዶ ወርቁን ሁሉ ከዚያ ቢጥለው ሰይጣን የጥጃ ምስል አድርጎት ከጉድጓዱ አወጣው፡፡ (ኦሪት ዘጸአት አንድምታ ትርጓሜ፡፡) 

የአሮን በትሩ የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ እነ አቤሮንና ዳታን ደጋፊዎቻቸውም ጭምር በሙሴና በአሮን ሹመት ላይ በጠላትነት በመነሣታቸው ምድር ተከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ከ12ቱ የእስራኤል ነገድ 12 በትር ወስዶ የእያንዳንዱንም ስም በበትራቸው ላይ ጽፎ በመገናኛው ድንኳን በመስክሩ ታቦት ፊት እንዲያኖራቸው አዘዘው፡፡ እግዚአብሔርም ለሹመቱ የመረጠው ሰው በትሩ እንደምታቆጠቁጥ ነገረው፡፡ ሙሴም እንደታዘዘው አድርጎ ሲጸልይባቸው አድሮ በትሮቹን ቢያወጣቸው የአሮን በትር ከሌሎቹ በትሮች ተለይታ ሳይተክሏት በቅላ፣ ውሃ ሳያጠጧት ለምልማ፣ አብባ፣ የበሰለ ለውዝ አፍርታ ተገኝታለች፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ያች በትር ለሚያምፁ ልጆች ሁሉ ምልክት ሆና እንድትጠበቅ አዘዞታል፡፡ በኦሪት ዘኁልቅ 7፡1-10 ላይ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው›› ተብሎ ነው የተጻው፡፡ ይኸውም ምሳሌ ነው፡፡ ለጊዜው እስራኤል በሹመት ምክንያት ተጣልተዋልና በዚህ ለይቷቸዋል፡፡ ፍጻሜው ግን የአሮን በትር ከሌሎች ተለይታ ለምልማ አብባ ፍሬ አፍርታ እንደተገኘች ሁሉ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሌሎች ከእስራኤል ሴቶች ተለይታ በሥጋ፣ በነፍስ፣ በልቡና አብባ አጊጣ ያለዘር ያለሩካቤ በድንግልና ወልዳ ተገኝታለችና በእውነት የአሮን በትሩ የወላዲተ አምላክ ምሳሌ ናት፡፡ ይህንንም ሊቃውንት አባቶቻችን እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ ያሬድና እነ አባ ጊዮርጊስ በሚገባ አመስጥረውታል፡፡ እንደመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ የአሮን በትር እንዳይሞቱ ለሚያምፁ ልጆች ምልክት ሆና እንደተጠበቀች ሁሉ ድንግል ማርያምም ለእኛም ለሐዲስ ክርስቲኖች በኃጢአት እንዳንሞት ምልክት ሆና ተሰጥታናለች፡፡ ነቢያቱም ‹‹ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች….›› እያሉ የነገሩንም ይህንኑ ነው፡፡ ኢሳ 7፡14፡፡ ቅዱስ አሮንም በበጎ ተጋድሎውና የኦሪትንም ሕግ በመጠበቅ እግዚአብሔርን ካገለገለ በኋላ ሚያዝያ 1 ቀን በሖር ተራራ ላይ ሲያርፍ እስራኤላውያን 30 ቀን አልቅሰውለታል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን! 

+ + +


ሰማዕቱ አባ ብሶይ፡- አማኝ ክርስቲያን የሆኑ ወላጆቻቸው ልጅ ሳይኖራቸው 17 ዓመት ኖረዋል፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ብርሃንን የለበሰ ጻድቅ ሰው ወደ አባቱ መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልድና ስሙን ብሶይ እንደሚለው ልጁም በመጨረሻ ሰማዕት እንደሚሆን ነገረው፡፡ ብሶይም ሚያዝያ 1 ቀን ተወለደና በሃይማኖት ኮትኩተው አሳደጉት፡፡ ለመምህርም ሰጡትና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ ተማረ፡፡ በ27 ዓመቱም ክርስቲያኖችን ይገድል ወደ ነበረው ከሃዲ ንጉሥ ዘንድ ሄዶ ክርስቲያን መሆኑን ተናገረ፡፡ ንጉሡም አሳሰረውና በማግሥቱ ለጣዖቱ እንዲሰግድ አዘዘው፡፡ አባ ቢሶይም የንጉሡን ትእዛዝ መቀበልን እምቢ ባለ ጊዜ ንጉሡ ይዞ እጅግ አሠቃየው፡፡ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ ተገልጾ አበረታው፡፡ 


ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ቁልቁልያኖስ ወደሚባል መኰንን ላኩት፡፡ ይህም ከሀዲ መኰንን ‹‹ለምን ለጣዖቶቻችን አትሰግድም?›› ብሎ ብዙ አሠቃየው፡፡ በብረት ችንካሮች ዐይኖቹን አወጣቸው፣ በፈላ ውኃ ውስጥም ጨመሩት፣ እጆቹንና እግሮቹንም በየተራ ቆረጧቸው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም የተቆራረጡ አካሎቹን ሁሉንም ፈውሶ እንደቀድሞው አንድ አደረጋቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ሀገርም አመጡትና ለዲዮቅልጥያኖስ አስረከቡት፡፡ እርሱም በተራው እጅግ ጽኑ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ሰኔ 5 ቀንም አንገቱን በሰይፍ አስቆርጦት የሰማዕትነት ፍጻሜ ሆኖ የክብርን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ የሰማዕቱ የአባ ብሶይ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን! 

+ + +  kegdedlat andebet yetewesede                                                                     

Telegram: https://t.me/tewhahdohaimanotachin                                    

LIKE OUR PAGE https://www.facebook.coBm/tewadhdohaimanotachin

No comments:

Post a Comment