Monday, March 11, 2013

ዘወረደ ወይም ሕርቃል ወይምሙሴኒ


የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ሌላም ስም አለው ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

«ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት = ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ.3-13፡፡

ሳምንቱ ሙሴኒ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ እምትእይንት» «ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ» ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ ስለሚያጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ከአለፉ በኋላ የሙሴ ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው ምላካችን እንደ እነሱ 40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን የሚያስታውስ ነው፡፡ /ዘፀ.24-18፤ 1ኛ.ነገ.19-8፤ ማቴ. 4-1-4/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡- ጾምና ምጽዋት

No comments:

Post a Comment