«ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለየች » ማለት ነው፡፡ ምስጢራዊ መልእክቱ ግን የምስጢረ አድኅኖት ታላላቅ ሥራውን ለመጀመር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም የምትጀመርበትን ሁለተኛ ሳምንት ከልብ ያሳስበናል፡፡ ማቴ. 4-2
ቅድሰት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ስያሜውም ከኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ ና ወንጌል ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
‹‹ቅዱስ›› ማለት ልዩ፤ክቡር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ መጻሕፍትም የባሕርይ ቅድስናውን ተባብረው መስክረዋል፡፡ ባባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ‹‹ቅዱስ፡ቅዱስ፡ቅዱስ›› እየተባለ ይመሰገናል፡፡( ኢሳ 6፡1-3፤40፡25 ራዕ 15፡4 ፤ 1ሳሙ2፡2-3፡፡) እኛም ቅዱስ ልጁ በሥጋ ተገልጦ እንዳስተማረን በየዕለት ጸሎታችን ‹‹ስምህ ይቀደስ›› እንለዋለን፡፡ የቅድስና ምንጭ ፡ ቅድስናን የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ ቅዱስ›› የሚለው ቃል ለሰዎች ፡ለመላእክት ፡ ለቦታ ፡ለዕቃ፡ ለዕለታት … ቢቀጸልም ቅድስናቸው በባሕርይው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡ይህም የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡
እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ በመልኩና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን›› ተብሎ ስለተጻፈ የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ›› ያለንም ይህንን ሲያስተምረን ነው፡፡ ከመፈጠራችን አስቀድሞ መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ለውርደት ሳይሆን ለክብር፤ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ፡ ጽድቅ ከኃጢአት፡ጋር ኅብረት የለውምና ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሰን ለመኖር በቅድስና መኖር ይጠበቅብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና ›› ያለንም ለዚህ ነው፡፡/1ተሰ 4*7/ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን አላማ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዲህ ገልጾላቸዋል ‹‹ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰማያዊ ሥፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ብሎ ካመሰገነ በኋላ ‹‹ ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን ፡ንጹሐንና ያለነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን›› ኤፌ 1፡3-4 አስቀድሞ ስለወደደንና ስላከበረንም ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ የሚያስፈልገንን ሁሉ አዘጋጅቶ በእጆቹ ካበጀን በኋላ የሥነ ፍጥረት ዘውድ አድርጎ በገነት አኖረን ፡፡( ዘፍ 1፡26 ፤መዝ 8፡1)
የቀደመው አዳም አታድርግ የተባለውን በማድረጉ በንዝህላልነትና በስንፍና በከይሲ ዲያብሎስም ምክር ተዋረደ፡፡ በሞተ ሥጋ ላይም ሞተ ነፍስ ፤በርዕደተ መቃብር ላይ ርዕደተ ሲኦል ተፈረደበት፡ በባሕርዩ ሞት ገባበት፡ተዳደፈ፡፡ ክፉ ፍትወታት የሚያጠቁትና የሚያሸንፉት የዲያብሎስና የኃጢአት ባርያ ሆነ፡፡ በማይለወጥ ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ግን ጠፍተን እንድንቀር አልተወንም፡፡ በሰጠን ተስፋ፡በተቆጠረው ሱባኤና በተነገረው ትንቢት መሰረት ዘመኑ ሲደርስ በተዋህዶ ሰው ሆነ፤ የተዋረደ ሥጋችንን አከበረ፡፡ በከበረ ደሙ ዋጀን፤ከኃጢአታችን አጠበን፡፡ በእርሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን ፡፡ጌታችንና መድኃኒታችን ሰው የሆነውና ለመዳናችን የሆነውን ዋጋ ሁሉ የከፈለው ለእኛ ያለውን ፍቅርና ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ለእኛ ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹ ነገር ግን የኃጢአትን ሥራ ይሽር ዘንድ ከእርሱ ጋር የተሰቀለውን አሮጌውን ሰውነታችን እንደሆነ ይህን እናውቃለን ›› የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ (ሮሜ 6፡6) እኛን ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ የተከፈለውም ዋጋ ታላቅ ከሆነው የጋብቻ ምስጢር ጋር በማያያዝ እንዲህ ገልፆታል ‹‹ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርሰቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና … ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት ራሱንም ስለእርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ፡፡ በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኩሰት እንዳይገኝባት ቤተ ክስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ…›› ኤፌ 5፡23-28
ስለዚህ ጌታችን በደሙ ኃጢአታችንን እንደ ቸርነቱ ይቅር ብሎናል፡፡ኤፌ 1፡7 ከእንግዲህ የራሳችን አይደለንም ፡፡ በሰውነታችንም ኃጢአትና ዐመፃን ልናደርግበት አይገባም ፡፡‹‹በዚህ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አታንግሷት፤ለምኞቱ እሺ አትበሉት፡፡ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት፤ ሰውነታችሁንም ለእግዚአብሔር የጽድቅ የጦር መሣሪያ አድርጉ››ተብለናል፡፡ (ሮሜ6፡12-13)
የተወደዳችሁ ምዕመናን እግዚአብሔር ደስ ብሎት የሚቀበለውን ህይወት ለመኖር አንፈልጋለን ፡፡ ለመሆኑ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ብንመላለስ ነው? መልሱን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮቱ ከንቱ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ወላጆች የሌሉአቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በችግራቸው መጠየቅ በዓለምም ከሚገኝ ርኩሰት ሰውነትን መጠበቅ ነው፡፡››በማለት ይመልስልናል( ያዕ 1፡26-27)፡፡ በክርስቶስ ደም የተቀደሰና የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችንን በዓለም ከሚገኝ ርኩሰት መጠበቅ የሰማያዊ ርስት ወራሾች ያደርገናል፡፡ በዓለም የሚገኘውን ርኩሰትም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሥጋ ሥራ ›› በማለት ገልጾታል፡፡‹‹እርሱም ዝሙት ፣ርኩሰት፣መዳራት፣ጣዖት ማምለክ፣ሥራይ ማድረግ፣መጣላት፣ ኩራት፣የምንዝር ጌጥ ፣ቅናት፣ቁጣ ፣ጥርጥር፣ፉክክር፣ ምቀኝነት፣ መጋደል፣ ስካር ፣ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡››እነዚህን የሚያደርጉ ሰዎችም ከመንግስተ እግዚአብሔር በአፍአ ወይም በውጭ እንደሚቀሩ ሲያስረዳ‹‹አስቀድሜ እንደነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግስት አያይም›› ብሏል ( ገላ5፡19)።
በሕይወታችን ሁሉ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን መገኘት ለቅድስና የጠራንን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡እነዚህንም ነገሮች ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመንፈስ ፍሬዎች ›› ብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ፍቅር፣ደስታ ፣ሰላም፣ትዕግስት፣ምጽዋት፣ቸርነት ፣እምነት ፣ገርነት ንጽሕና ››ናቸው፡፡ገላ 5፡22 እግዚአብሔር ማደርያው ይሆን ዘንድ የመረጠውን ሰውነታችንን እርሱ የሚከብርበትን ሥራ ልናደርግበት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በሕይወት የሚኖሩትም ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ›› እንደተባለ በሕይወታችን ሁሉ ፋቃዱን በመመርመርና በመፈጸም በቅድስና ልንኖር ይገባናል፡፡2ቆሮ 5፡15
ቅድስናችን በኑሮአችን ሁሉ እንዲሆን ታዘናል (1ጴጥ1፡15)፡፡ ስለዚህ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣በማኅበራዊ ኑራአችን ፣በምንበላው ምግብ ፣በምንለብሰው ልብስ ፣በንግግራችንና በመሳሰለው ሁሉ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን በማድረግ እግዚአብሔርን በሚሞት ሥጋችን እናክብረው፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ፡፡ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ ፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል ›› ተብሎ እንደተጻፈ ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ ተጋድሎ አድርገን ከኃጢአት ርቀት በቅድስና እንድንኖር ይገባናል(ዕብ 12፡1)። ሥጋዊ ምኞታችንንና መሻታችንን ሰቅለን አሮጌው ሰዋችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድናኖር ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Source: http://www.eotc-mkidusan.org/
LIKE OUR PAGE >>>
No comments:
Post a Comment