Monday, March 17, 2014

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ)

ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ /መዝ 2፡11-12/

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ) ለአጠቃላይ ጾሙ መግቢያ የሚሆኑ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች(መልዕክቶች) ይተላለፉበታል። እነዚህን ቀጥለን እንመለከታለን።

1. ስለ ጾም

ዘወረደ የታላቁ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን የጾም አዋጅ ታውጅበታለች፤ ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋእል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግእዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል።
ጾም ፈቃደ ስጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር/ለመንፈስ ቅዱስ/ የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሳሪያ ነው፡፡ጾሙ ይህ የሚደረግበት መሆኑን ቤተክርስቲያን ሳምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብላ ታሳስባለች፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣በረዓድም ደስ ይበላችሁ” /መዝ 2፡11-12/ ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። ጾም ውጤታማ እንዲሆን እነዚህ መከልከሎች ከጸሎት ፣ ከፍቅርና ራስን ከማዋረድ ጋር መተባበር አለባቸውና በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ እያለች ታስተምራለች፦“ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሃቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም ፤ወንድማችንንም እንውደድ”
(ጾመ ድጓ)።በዘወረደ እሁድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን መልዕክት የያዙ ናቸው።“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” /ያዕ 4÷6-10/
“ በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” /ዕብ 13÷15-16/
“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና ። ” /ዕብ. 13፥9/በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተክርስቲያን ትጠቁማለች፡፡ ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክትእንዲህ ይላል፡፡
“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው።” /ዕብ. 13፥7/ጾመ ድጓው ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንዲህ እያለ ያስታውሰናል፤“የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

2. ስለ እግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሥጋዌ)

ከዐቢይ ጾም ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያሉት ዕለታት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን ያደረጋቸው ነገሮች (ማስተማሩ፣ ተአምራት ማድረጉ፣ በፈቃዱ ተላልፎ መሰጠቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ መንፈስ ቅዱስን መላኩ…) በስፋት የሚነገርባቸው ናቸው።
የእነዚህ ሁሉ ነገሮች መሠረትና ያገኘናቸው ጸጋዎች ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሰው መሆን) ነው።ይህ ሣምንት የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሣምንት እንደመሆኑ ቀጥለው ለሚነገሩት ነገሮች መሠረት የሆነው ይህ የእግዚአብሔር መውረድ ይነገርበታል። ዘወረደ (የወረደው) የሚል ስያሜ የተሰጠውም ከዚህ በመነሳት ነው።
ሣምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት የሚነበበው ወንጌል ይህን መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።“እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ነገር ግን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም። በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ፥ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ።በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና።” /ዮሐ. 3፥11-16/ጾመ ድጓው የሚጀምረውም እንዲህ በማለት ነው፣ “ዘወረደ እምላዕሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ…. እግዚአ ኩሉ ዘየሀዩ በቃሉ፤ ….በቃሉ የሚያድነውን ከላይ የወረደውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት… ”

3. ስለ ትምህርት

ዐቢይ ጾም የትምህርት ዘመን ነው። በጥንት ቤተ ክርስቲያን አዳዲስ አማንያን /ንዑሰ ክርስቲያን/ የሚጠመቁት በትንሣኤ በዓል ስለነበር በዐቢይ ጾም ሰፊ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር።ዛሬም ዐቢይ ጾም ጌታችን በዚህ ምድር በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው ነገሮች (ትምህርቱ፣ ተአምራቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው … ) በሣምንታት ተከፋፍለውና ተደራጅተው የምንማርበት የትምህርት ዘመን ነው። በአብነት ትምህርት ቤቶቻችንም ዐቢይ ጾም ዋነኛ የትምህርት ዘመን መሆኑ ይታወቃል።
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ዘመን በሆነው ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ስለ ትምህርትና ስለ መምህራን እንዲህ እያለች ትሰብካለች፤
“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም የሚኖር እርሱ ነውና። ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ።” /ዕብ. 13፥7-9/
“ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደመሆናቸው፣ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና፡፡” /ዕብ. 13፥17/
አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ መዋዕለ ጾሙን በሠላም አሳልፈህ የትንሣኤህን ብርሃን ለማየት እንድታበቃን እንለምንሃለን። አሜን።

በዲ/ን አሉላ መብራቱ

LIKE OUR PAGE >>>

No comments:

Post a Comment