Sunday, May 5, 2013

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤዉ በሰላም አደረሳቹ

ትንሣኤውን የምናከብረው ያጡትን በማሰብ ይሁን

የትንሣኤን በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሞትን በመስቀል ላይ ከተቀበለ በኋላ በሦስተኛው ቀን መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ዕለት ነው፡፡

የትንሣኤውም ዓላማ የሰው ልጅ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ አለመቅረቱን ለማስረዳት፣ ክርስቲያኖች ከሞት በኋላ ተስፋ ትንሣኤ እንዳለን ለማጠየቅና ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሐ መነሣት እንዳለብን ለማስተማር መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡

በቤተክርስቲያናችንም እነዚህ ታላላቅ ዓላማዎች ያሉት የትንሣኤ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችን ሞትና ሰይጣን ድል የተነሡበት፣ የሰው ልጅም ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣበት፣ በአዳምና በሔዋን ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ የድል፣ የነጻነትና የሰላም ዕለት ስለሆነ ነው፡፡


ስለዚህም በቤተክርስቲያናችን የትንሣኤ ሰላምታ የተለየ ነው፡፡ ይኸውም፡-

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን. . . በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን. . .  አጋዐዞ ለአዳም
ሰላም . . .  እም ይእዜሰ
ኮነ . . .  ፍስሐ ወሰላም  የሚል ነው፡፡

እንግዲህ ይህንን በዓል በየዓመቱ ስናከብር ዓላማውን ዘንግተን በዓሉን የምግብና የመጠጥ ብቻ እንዳናደርገው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በልዩ ልዩ መንገድ በፈቃዱ የሰይጣን ባሪያ የሆነ፣ ከክርስቲያናዊ ምግባርና ትሩፋት የራቀ ሁሉ ራሱን እንዲመረምርና ለመልካም ሥራ እንዲነሣ የሚያደርግ በዓል መሆኑን ተረድተን ራሳችንን ልናስተካክል ያስፈልጋል፡፡

በዓለም በሥጋ ሥራ በመመላለስ የምንኖር ከዚህ ሥራችን በልቦና ትንሣኤ ተነሥተን የንስሐ ፍሬ የምናፈራበት እንዲሆን ልንተጋ ይገባናል፡፡

ክርስትናችን በስም ብቻ ተወስኖ በዓለም በሥጋ ሥራ የምንኖር ደግሞ ራሳችንን በመመርመር በንስሐ ታጥበንና ታጥነን ትንሣኤውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን በመቀበል እናክብረው፡፡
ሁልጊዜም በዓሉን ከነዳያን ጋር እየተካፈልን የምንኖር መልካም ልማድ ያለን የትሩፋት ሥራችንን እያሳደግን፣ በሃይማኖትና በምግባርም እየበረታን ልንሔድ ያስፈልጋል፡፡ ክርስትና ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ የምናፈራበት የዕድገት ጉዞ እንጂ በምንሠራት ጥቂት የትሩፋት ሥራ ብቻ ረሥተን የምንቆምበት አይደለምና በትሩፋት ላይ ትሩፋት፣ በጸጋ ላይ ጸጋ እየጨመርን መሔድ ይገባናል፡፡

ትንሣኤውን በማሰብ ነዳያንን የምናስፈስከውም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራትም ሁልጊዜ በሬ እያረዱ ፋሲካውን ማክበር ብቻ ሳይሆን፤ ነዳያኑንና ወጥተው ለመለመን አፍረው በየቤቱ የተቀመጡ ወገኖቻችንን ጭምር በማስታወስ እንዲሁም በልማት የሚያሳትፍ ሥራ ወደመሥራት በማደግ ችግረኞቹን በዘላቂ ልማት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይገባናል፡፡

ከዚህም ሌላ ነዳያኑን በዚህ ዓለም በሥጋ ስላጡ በነፍሳቸው በመንፈሳዊ ሕይወት እውቀት አግኝተዋል ማለት ስላልሆነ፤ በነፍሳቸው የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ  መንፈሳዊውንም ምግብ ልንመግባቸው ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ በዓሉን በምናከብርባቸው ዕለታት ሁሉ ነገረ መስቀሉን በማሰብ፣ መልካም ሥራን በመሥራትና በትሩፋት ላይ ትሩፋት በመጨመር፣ በንስሐ እንዲሁም በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን በመቀበል ይሁን፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን

No comments:

Post a Comment