Tuesday, February 18, 2014

የካቲት 8

የካቲት 8 በዚህች ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የአይሁድን ህግ ሊፈጽም ከሁለት የርግብ ጫጩቶች ጋር ወደ ምኩራብ የገባበት ቀን ነው። ሉቃ 2፤22 የአረጋዊ ስምኦንን ታሪክ እዚህ ጋር ያመጡታል። በጥሊሞስ የሚባል ኃያል ንጉስ ነበር ይላል ከገናንነቱ የተነሳ ዓለምን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ የገዛ፤ “ስሜ ዝንት ዓለም እንዲታወስ ምን ልስራ” አለ፤ አማካሪዎቹ “46ቱን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን አስተርጉም” አሉት 70 የአይሁድ ሊቃውንትን ሰብስቦ ከዕብራይስጥ ቋንቋ ወደ ጽርዕ ቋንቋ እንዲተረጉሙ አደረገ ከ 70 ሊቃውንት አንዱ ስምኦን ነበር ትንቢተ ኢሳይያስን እንዲተረጉም ደረሰው፤ ሲተረጉም ኢሳ 7፤14 ድንግል በድንግልና ትጸንሳለች ከሚለው ደረሰ፤ እንዴት ድንግል ትጸንሳለች ይህንን ብጽፍ ንጉሱ ከፍ ብሎ አንገቴን ዝቅ ብሎ ባቴን ይቆርጠኝ የለምን ብሎ “ድንግል” የሚለውን “ሴት” አለው እንቅልፉን ተኝቶ ሲነቃ ሴት የሚለው ተፍቆ “ድንግል” ተብሎ ተጽፎ ያገኛል አሁንም ሰርዞ “ሴት” ብሎ ይጽፋል እስከ ሦስት ጊዜ እንዲሁ ሆነ፤ በሶስተኛው ሊያጠፋው ሲል መልአኩ ተገልጾ አታጥፋው ይህን ሳታይ አትሞትም ብሎታል፤ሉቃ 2፤26 ይህንን ተስፋ ሲጠባበቅ 500 ዓመት በምኩራብ ከአልጋ ተጣብቆ ኖረ። በዛሬዋ ቀን ግን ያ የተነገረው ተስፋ ተፈጸመ ድንግል በድልግልና ወልዳ አየ ማየት ብቻ አይደለም ህጻን የሆነውን እግዚያብሔር በእጁ ታቀፈው እንዲህም አለ “አይኖቼ ማዳንህን አይተዋል ባሪያህን በሰላም አሰናብተው” ሉቃ 2፤30። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን የገዳመ ሲሐቱ አባ ኤልያስ አረፈ፤ የበቃ ባህታዊ ነው ከዕለታት በአንዱ ቀን ንጉስ ቴዎዶስዮስ አንድ የሚያረጋጋኝ አባት ላኩልኝ ብሎ ወደ ገዳመ ሲሐት መልእክት ይልካል አባቶችም የበቃ አባት ነው ብለው አባ ኤልያስ ይልኩታል፤ ንጉሱ እንዲህ ይለዋል በገድል ነብዩ ኤልያስን እንደምትመስል መነኮሳቱ ነገሩኝ አለው፤ አባ ኤልያስም ቆፍጠን ብሎ ንጉስ ይቅርታ ያድርጉልኝ ነብዩ ኤልያስ ስለደግነቱ ቁራዎች ምግቡን ያመጡለት ነበር (1ኛ ነገ 17፤6) እኔ ግን ምግቤን በጸሐይ ላይ ባሰጣው ቁራ ይዞት ይሄዳል አለው፤ ንጉሱ ሰምቶ ከቃሉ ጣዕም ከአንደበቱ ቅልጥፍና የተነሳ አደነቀ ይላል፤ ይህ አባት ወደ ገዳሙ እስኪመለስ ከንጉሱ ማዕድ ምንም ምን አልቀመሰም በተጋድሎ ኖሮ በዛሬዋ ቀን አርፏል፤ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን የከበረች እመቤት ቅድስት አመተ ክርስቶስ አረፈች አገሯ ቊስጥንጥንያ ነው፤ባሏ መስፍን ነበር ሲሞት ገንዘቧን ሁሉ ለድሆች ሰጥታ በአንድ ጥልቅ ዋሻ ውስጥ 11 ዓመት በተጋድሎ ኖረች ዘወትር በሰርክ አዕዋፍ የእፅዋት ፍሬ ያመጡላት ነበር፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ የንጉሱ ግብር ሰብሳቢ በዘመናችን ቋንቋ ግብር የሚተምን ሲዘዋወር ከአንድ ገዳም ይደርሳል ብዙ የእጽዋት ፍሬ ያለበት ዛፍ ያገኛል ይህ የማን ነው ብሎ አበምኔቱን ይጠይቀዋል እኛ አናውቅም አዕዋፍ ዘወትር ከነቅርንጫፉ እየቆረጡ ሲበሩ እንመለከታለን ራሳቸው ግን አይበሉትም ይህ ሁሌም ያስደንቀናል አሉት፤ አዕዋፉ የሚበሩበትን አቅጣጫ ተከትለው ጉዞ ጀመሩ ከብዙ ድካም በኋላ ወለተ ክርስቶስ ካለችበት ዋሻ ደረሱ ገብተው በረከቷን ተቀበሉ ለአበምኔቱ ታሪኳን ነገረችው እርሱም ጻፈው በበነጋው አረፈች በታላቅ ክብር በብዙ ዝማሬ ቀበሯት፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከቅዱሳኑ በረከት ያሳርፈን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment