አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥር 10 እና 11-ይህቺ ዕለት በዮናኒ ቋንቋ ኤጲፋንያ ትባላለች፣ ትርጓሜውም መለኮት የተገለጠበት ማለት ነው፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ልዩ የሆነች የሦስትነቱን ምሥጢር ገልጦባታልና ይህች ዕለት እጅግ የከበረች ናት፡፡ መጥምቁ ዮሐንስም ለዚኽ ነው ጌታችንን ከማጥመቁ በፊት ጌታችንን ፡- "አቤቱ አምላኬ ሆይ! የአብ ስም በአንተው አለ፣ የወልድ ስም አንተው ነህ፣ የመንፈስ ቅዱስም ስም በአንተው ሕልው ሆኖ አለ፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፣ አንተን ግን በማን ስም አጠምቃለሁ?› ብሎ የጠየቀው!
በዚኽች በከበረች የጥምቀት ዕለት በጥምቀት ወቅት የክብር ባለቤት ጌታችንና ያጠመቀው ቅዱስ ዮሐንስ ብለው እንደተነጋገሩ፡- ‹‹በዚያን ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ያጠምቀው ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወደ ዮሐንስ መጣ፡፡ ዮሐንስም በእርሱ ላይ አድሮበት ባለው በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ጌታችን ወደ እርሱ ሲመጣ ባየው ጊዜ አሰምቶ ጮኸ፤ በታላቅ ቃልም እንዲህ አለ፡- ‹እኛን ለማዳን የመጣው የእግዚአብሔር በግ እነሆ፡፡ ነቢያትም ስለ እርሱ ትንቢት የተናገሩለት ንጉሠ ነገሥት ይህ ነው፡፡ በዕውነት ቀዳሚና ተከታይ የሌለውና ለመንግሥቱም ፍጻሜ የሌለው አምላክ ይህ ነው፡፡› ዮሐንስም ይህን ቃል እየተናገረ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠርቶ እንዲህ አለው፡- ‹ዮሐንስ ሆይ! ስለ እኔ የተጻፈውን ሕግ ሁሉ ትፈጽም ዘንድ እነሆ ይገባሃል፤ እነሆ በአየኸው ሁሉ ምስክር ትሆን ዘንድ በአንተ እጅ የምጠመቅበት ጊዜ ስለደረሰ አጥምቀኝ› አለው፡፡ ዮሐንስም ለጌታችን እንዲህ ብሎ መለሰለት፡- ‹ወደ አንተ መጥቼ መጠመቅ ለእኔ ይገባኛል እንጂ እኔ ባሪያህ ሆኜ ሳለሁ በእኔ እጅ ትጠመቅ ዘንድ ስለምን ወደ እኔ መጣህ? አንተ ጌታ ሆነህ ይህ ነገር ፈጽሞ አይገባም› አለው፡፡ ጌታችንም ‹ዮሐንስ ሆይ! በአንተ እጅ ስለመጠመቄ ደስ መሰኘት ይገባሃል፤ አትፍራም፡፡ አንተ እጅህን በራሴ ላይ ታኖራለህ፤ ሰውነቴንም እኔ አጠምቃታለሁ፡፡ ዮሐንስ ሆይ! እንቢ አትበለኝ እነሆ ነቢያት ስለ እኔ የተናገሩትን ሕግና ትእዛዝን ሁሉ ልፈጽም መጥቻሁና› አለው፡፡ ጌታችንም ይህን ቃል ለዮሐንስ ነግሮት ከጨረሰ በኋላ ወደ ዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ገባ፡፡ ያንጊዜ ዮርዳኖስ አርባ ክንድ ወደኋላው ተመለልሶ ሸሸ፣ ውኃውም በእሳት እንዳፈሉት ሆነ፡፡ በጸናችው የጥበቡ ኃይል አዳምን ከነልጆቹ ለማዳን ወደዚህ ዓለም ከመጣው ከጌታችን ፊት ዮርዳኖስ ስለ መሸሿና ወደ ኋላዋ ስለ መመለሷ ነቢዩ ዳዊት ትንቢት ተናግሮአል፡- ‹አቤቱ ውኆች አዩህ፣ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፡፡› አንቺ ባሕር የሸሸሽው፣ አንቺ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የተመለሽው ምን ሆናችኋል? ጌታችንም ዮርዳኖስን እንዲህ በማለት ገሠፀው፡- ‹ዮርዳኖስ ሆይ! በጥምቀቴ ጊዜ አትሽሽ፣ ባለህበት ቦታም ተመልሰህ ቁም› አለው፡፡ ጌታችንም ይህን ቃል በተናገረው ጊዜ የነቢዩ ዳዊት ትንቢት ይደርስ ዘንድ ውኃው ወደ ቦታው ተመልሶ ቆመ፤ ከጌታችንም ፊት ሰገደ፡፡ ዮሐንስም ዮርዳኖስ ወደ ኋላዋ ተመልሳ መሸሿንና በጌታችን ትእዛዝ ወደ ቀድሞ ቦታዋ ተመልሳ ከጌታችን ፊት ስትሰግድ ባየና በተመለከተ ጊዜ ፈራ፣ ደነገጠ፣ ታላቅ መንቀጥቀጥም አደረበት፣ በፊቱም ሰገደለት፡፡ ‹እነሆ አንተ ጌታዬና ፈጣሪዬና ነህ እኔ አገልጋይህ ባሪያህ ነኝ፣ አቤቱ ጌታዬ ሆይ! ይህን ሁሉ ደካማነቴን ተመልክተህ እጁን በራስህ ላይ ያኖር ዘንድ ባሪያህን አታስገድደው› አለው፡፡ ጌታችንም ለዮሐንስ እንዲህ አለው፡- ‹ይህ ለእኛ ተድላ ደስታ ነውና እውነትን ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና ያዘዝኩህን አድርግ› አለው፡፡ ‹አንተም መጥምቀ መለኮት ተብለህ ክብርህ ይነገራልና እኔም በባሪያው እጅ ተጠመቀ ተብዬ ትሕትናዬ ይነገራልና› አለው፡፡ ይህንንም ሲናገረው ዮሐንስ ተወው፡፡ ዮሐንስም እንዲህ አለው፡- ‹የአብ ስም በአንተው አለ፣ የወልድ ስም አንተው ነህ፣ የመንፈስ ቅዱስም ስም በአንተው ሕልው ሆኖ አለ፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፣ አንተን ግን በማን ስም አጠምቃለሁ?› አለው፡፡ ጌታም ዮሐንስን እንዲህ እያልክ አጥምቀኝ አለው፡- ‹እንደ መልከጼዴቅ ሹመት የዓለሙ ካህን፣ ብርሃንን የምትገልጽ፣ የአብ የባሕርይ ልጅ፣ አቤቱ ይቅር በለን፣ የዓለምን ኃጢአት የምታስወግደው የእግዚአብሔር በግ ይቅር በለን እያልክ አጥምቀኝ› አለው፡፡ ያንጊዜ ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥር ዐሥራ አንድ ቀን ከሌሊቱ በአሥር ሰዓት አጠመቀው፡፡››
ከበዓሉ ረድኤት ይክፈለን!
(ምንጭ፡- ሚጣቅ አማኑኤል ያሳተመው የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ገድል)
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰን!
LIKE OUR
PAGE
https://www.facebook.com/tewadhdohaimanotachin
https://www.youtube.com/watch?v=3fnWuuHj5ZM
No comments:
Post a Comment