Monday, June 9, 2014

እንኳን ለጌታችን ለመድሐኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የእርገት በዓል አደረሳችሁ !!!



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አ፩ዱ አምላክ አሜን

“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)
ዕርገት

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ
የትንሣኤያችን በኩር የሆነው ጌታ በመቃብሩ ቦታ
- ለማርያም መቅደላዊት እና ለሌሎችም ሴቶች (ማቴ 28÷1 የሐዋ 2÷1)፡፡
- ለኤማውስ መንገደኞች( ሉቃ 24÷13)
- ለደቀማዛሙርቱ በተዘጋ ቤት (ዮሐ 20÷8)
- በጥብርያዶስ ባህር ለደቀመዛሙርቱ ዮሐ 21÷4 
ሥርዓትን እያስተማረ አልፎ አልፎም በግልጥ እየታየ ፍርሐታቸውን እያስወገደ አይሁድ እንደሚሉት ሥጋውንም ደቀመዛሙርቱ እንዳልሰረቁት ይልቁንም በሞት ላይ ሥልጣንኑን አሳይቶ መቃብሩን ባዶ አድርጐ በትንሣኤው አለት ላይ ያቆመን፣ ሞት በእርሱ እንደተሸነፈ የማይታየው እየታየ፣ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ዘላለማዊ ጌታ የማይዳሰሰው እየተዳሰሰ ለ40 ቀናት ያክል ቆይቶ ተከታዮቹን ሐዋርያትን ወደቢታንያ አወጣቸው፡፡ እያዩት በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ፡፡ እንዲህ ተብሎ በነብዩ ዳዊት እንደተፃፈው፡- “ዐረገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ” እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ፣ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፣ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ (መዝ 46÷5)

አምላካችን ወደሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀመዛሙርቱን ምን አዘዛቸው?

1. ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡ (ሉቃ 24÷48) ደቀመዛሙርቱ ያዩትንና የሰሙትን ሞትን አሸንፎ የተነሣውን ጌታ ለዓለም ሁሉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የዓላውያንን ነገሥታት፣ የቄሳሮችን ዛቻና ማስፈራሪያ አንዳችም ሳይፈሩ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ ድረስ ሁሉን እያጡና መከራ እየተቀበሉ፣ እየታሰሩና እየተገረፉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ በኋላ ስሙን አትጥሩና በስሙም አታስተምሩ እያሏቸው በሸንጐ ፊት ሲያቆሟቸው፣ ሲገርፏቸው ደስ እያላቸው ከሸንጐ ፊት ይወጡ ነበር፡፡ (የሐዋ 5÷40)፡፡ ስለ ስሙ ምስክር መሆን መነቀፍና መታሰር፣ መደብደብ እንዴት ደስ ይላል!፡፡ እኛም እንደ ደቀመዛሙርቱ ማንንም ሳንፈራ አፋችንን ሞልተን ስለ ስሙ እየመሰከርን ሁሉን ብናጣም ሞታችንን በሞቱ ድል የነሣልንን የሚቃወመንን ጠላታችንን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያስወገደልንን፣ እረፍትና ሰላም የሰጠንን፣ ጨለማውን ገፎ ብርሐንን ያጐናፀፈንን፣ ያለፈውን ታሪካችንን በነበር ላስቀረልን ምስክሮች እንሁን፡፡

2. አጽናኙን እልክላችኋለሁ (ዮሐ 15÷26)፡-
- በአህዛብና በዓላውያን ነገሥታት ፊት ሲቆሙ እውነትን እንዲናገሩ የሚያፅናና ኃይል፣
- ከተዘጋ ቤት ወደ ሠገነት እንዲቆሙ የሚያደርግ ኃይል፣
- ልበ ሙሉ ሆነው ከጥርጥር ወደ ፍፁም እምነት፣ ከፍርሃት ወደ ድፍረት እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ አጽናኝ ኃይል እልክላችኋለሁ፡፡
ይህ ኃይል በዘመናችን በጣም ስለሚያስፈልገን በፍፁም መዘንጋት የለብንም፡፡ እውነትን ለመናገርና ለመመስከር፣ ፍርሐታችን እንዲወገድልን ከፈለግን ይህንን ኃይል ዓለም ሳይሆን የሚሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን አውቀን ጌታ ሆይ እኔን ልጅህ ያንተን ኃይል አጥቼ ደክሜያለሁ፣ ከእኔ የሆነ ኃይል ምንም የለምና ከእኔ አትራቅ፡፡
- ባስልኤልንና ኤልያብን በጥበብ መንፈስ የሞላህ (ዘፀ36÷2)
- ሶምሶንን በጾርዓና በኤሽታኦል ያነቃቃህ (መሳ 14÷18)
- ለደቀመዛሙርቱ ኃይልህን ልከህ 71 ቋንቋ የገለጥክ፣ በየዘመናቱ የተመረጡ አገልጋዮችህ ያፅናናህ፣ የእውነትን ቃል እየላክ ያበረታታህ እኛም እንድንበረታ ኃይልህን ከአርያም ላክልን፣

3. በኢየሩሳሌም ቆዩ (ሉቃ 24÷49)፡- ደቀመዛሙርቱ ከቢታንያ ወደ
ኢየሩሳሌም ተመልሰው በአንድ ልብ ሆነው በኢየሩሳሌም ቀዩ፡፡ በመቆየታቸውም
ሰማያዊ ኃይል አገኙ፡፡
እኛ ሰማያዊ ኃይል ለማግኘት የት እንቆይ?
- በኢየሩሳሌም ቤተክስቲያን መቆየት ያስፈልገናል፣
- በአንድ ልብ ሆነን በቤታችን፣ በአገልግሎታችን፣ በዘር፣ በጐሣ ሳንከፋፈል ይኸ እንዲህ ነው፣ ያ ደግሞ እንዲህ ነው ሳንል ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን የወጣንም እንመለስ፣
- ሰዎች ባይመቹንም፣ ክፉዎች ልባችንንን ቢያቆስሉንም፣ ሰዎች እንጂ ያልተመቹን ክርስቶስና ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ይመቹናል፡፡ ስለዚህም ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን አንውጣ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየበላንና እየጠጣን፣ እያገለገልን፣ ያደግንባት የእኛ ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያናችን ብናዝን የምንጽናናባት፣ አእምሮአችን የሚያርፍባት፣ ሰላም የምናገኝባት ኢየሩሳሌም ቤትክርስቷያናችን ናት፡፡

ማጠቃለያ

አምላካችን የማዳን ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለተከታዮቹ ደቀመዛሙርት ምስክሮቼ ናችሁ፡፡ አጽናኙን እልክላችኋለሁ፡፡ “አንትሙ ንበሩ በሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ሃይለ እማርያም፡፡ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ አዘዛቸው፡፡

በመጨረሻም ወደሰማይ ሲያርግ እጆችንም አንስቶ ባረካቸው፡፡ (ሉቃ 24÷51)
በብሉይ ኪዳን ተፅፎ እንደምናገኘው፡- አባታችን አብርሃምን ባርኮ ያበዛ(ዘፍ12÷1)፣ ያዕቆብን በያቦቅ ወንዝ ሲባረክ ያደረ (ዘፍ35÷9)፣ ያቤጽን ባርኮ ሀገሩን ያሰፋ(1ኛ ዜና 4÷9)፣ አምስቱን እንጀራ፣ ሁለቱን ዓሣ አብዝቶ የባረከ ጌታ ዛሬም በኑሯችን አብዝቶ የሚባርከን፣ ሥራችንን እንድንሠራ በበረከት ያጣነውን ደስታ የሚመልስልን፣ ባርኮ በበረከት ወደሚያትረፈርፍልን፣ ጉድለትን ሳይሆን ሙላትን፣ ማጣት ሳይሆን በረከትን ወደሚሰጠን ደቀመዛሙርቱ ዓይኖቻቸውንም ወደላይ ትኩር ብለው እንደተመለከቱት እንደሐዋርያት ማየት ይጠበቅብናል፡፡ እውነት ነው እርሱን ማየት ከሁሉም ይበልጣልና ወደሰማይ ያረገውን ጌታ አይናችንን አንስተን እንይ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል

LIKE OUR PAGE >>>

No comments:

Post a Comment