Friday, April 26, 2013

ሆሣዕና





ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መገቢያ ዋዜማ ነው። ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ስም በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።


አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’’ ዘካ.9፣9። በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር። ሲመጣም ‘ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት።’’ በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል። 2ኛ ነገ. 9፣13 ። የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር - በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ.117፣26 በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይታደላል። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. 21፣1-17)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር.11፣1-10)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ.19፣29-38)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ.12፣12-15) ወንጌላት ይነበባሉ ። ታዲያ አኛ ይህን ዐቢይ በዓል የምናከብረው እንዴት ነው? በነቢያቱ ከላይ እንደተገለጠው በወንጌላቱም አንደተፈጸመው እርሱ ወደ እኛ የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው? ሲመጣስ ምን እናድርግ? የእግዚአብሔርን መምጫ ጊዜ ማሰብና መዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው? ምክንያቱም በዓሉ ከምንም በላይ የሚጠቅመን ለእኛ ነውና ። ስለዚህ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልንተገብረው ይገባል። 


ለጌታ የማያስፈልግ ፍጥረት የለም ይልቁንም የክብር ዘውድ አድረጎ በመልኩ የፈጠረው ሰው ያስፈልገዋል።ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ማንም የለም።እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ዓላማና ዐቅድ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ሥራ ልንሠራ ይገባል።አህያ በሰው ሰውኛ ሲታይ የንቀትና የውርደት ሲመስል ይችላል ።





የአህያን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን 


1. በለዓም በሥጋዊ ገንዘብ መንፈሳዊ ዓይኑ ታውሮ እግዚአብሔር ያልረገማቸውን እስራኤላውያንን ሊራገም ሲሄድ እስራኤላውያንን እንዳይራገም ለመንገር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ በሚሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ ሳለ ከበለዓም ይልቅ ያየችው የበለዓም አህያ ነበረች ። አህያይቱም መልአኩን አክብራ መንገዱን እንደለቀቀችለት ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ዘኅ.22፣23። 


2. በትንቢተ ኢሳያስ 1፣3 ‘ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጪ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እሥራኤል ግን አላወቀም’’ እንደተባለው ጌታ በተወለደ ጊዜ ትንቢቱን ምሳሌውን የሚያውቁ እሥራኤላውያን ባላወቁ ባለተቀበሉ ሰዓት በዚያ በብርድ ወራት እናቱ የምታለብሰው ልብስ አጥታ ቅጠል አልብሳው በነበረ ጊዜ ለጌታ ሙቀት የገበሩለት እረኞቻቸውን ተከትለው የመጡ ከበቶች ላሞችና አህዮች ናቸው። ‘ወአስተማወቅዎ አድግ ወላህም’’ እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም።። 


3. በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንስሳት ይለቅ ጌታን ለመሸከም ለከብር የተሸከመችው አህያ ናት። ጌታን የተሸከመችው አህያ ከዚያ በፊት ያላየችውና ያልተደረገላት ክብር ተደርጉላታል። አህያ ከዚህ በፊት ለኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ሂጂ እያልን በዱላ እንደበድባት ነበር፡ ነውም። ነገር ግን በሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በንጣፍ ላይ ተራምዳለች ። 


ስለዚህ ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ እንዲቀመጥባት ልብስም አንደ ተጎዘጎዘላት እኛም ጌታ በፀጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጢአትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትና ልንጎዘጎዝ ይገባል።ጌታ በኛ ላይ በፀጋው ሲያድር በእርሱና በቅዱሳኑ ዘንድ ያለን ክብርና ፀጋ ታላቅ ነው። በነገር ሁሉ መከናወን ይሆንልናል።ክርስቶስን በመሸከሟ የአህያይቱ ታሪክ እንደተለወጠ ሁሉ በክርስቶስ ማደሪያነታችን ያለፈው መጥፎ ታሪካችን ይለወጣል።እንግዲህ በእለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ በዝማሬ እንደ ንጉሰ እንደተቀበሉት እኛም ሀሴትን አድርገን ‘ሆሣዕና እምርት እንተ አቡነ ዳዊት…’’ በማለት እናመሰግናለን። ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን።አሜን።






1 comment: