በዚህች ቀን በምድር ላይ እንደ መላእክት የኖረች ታላቋ ጻድቅ
ማርያም ግብጻዊት አረፈች፡፡ ታሪኳ እንዲህ ነው፤ ትውልዷ ግብጽ ሲሆን ገና በ 12 ዓመቷ ቤተሰቦቿን ጥላ ወጣች
እስክንድርያ ከተማ ውስጥ 17 ዓመት በዘማዊነት ኖረች ብዙዎችንም አሰናከለች፤ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ እየሩሳሌም
ከሚሄዱ ምዕመናን ጋር ተቀላቅላ በመርከብ ተሳፈረች፤ነገር ግን ለጽድቅ
አይደለም በመርከብ የተሳፈሩ ምዕመናንን በዝሙት ልትጥል እንጂ፤ እየሩሳሌም ደረሱ ሁሉም የጌታን መቃብር ሊሳለም
ወደ ቤተክርስቲያኑ ገባ፤ እርሷ ግን ልትገባ ስትሞክር አንዳቸ ኃይል ወደ ኃላ ይመልሳታል እስከ ሦስተ ጊዜ ያህል
እንዲሁ ሆነባት፤ እግዚያብሔር በደሌን ቆጥሮ ነው ብላ አምርራ አለቀሰች፤ እመቤታችን ተገለጸችላት እንዲህም አለቻት
"እግዚያብሔር ይቅር እንዲልሽ ወደ ዮርዳኖስ በረሃ ሂጂ በዚያም ታላቅ እረፍትን ታገኚያለሽ " ቁራሽ ዳቦ ይዛ
ዮርዳኖስ በርሃ ገባች የሰው ፊት ሳታይ 47 ዓመት ቀን ሐሩሩ ሌሊት ቁሩ እያሰቃያት በፍጹም ተጋድሎ ኖረች፤ ሰውነቷ
ከሰል መሰለ አጥንቷ ከቆዳዋ ጋር ተጣበቀ። አንድ ቅዱስ ዞሲማስ የተባለ ታላቅ ባህታዊ ነበር በ 3 ዓመቱ ነው
ገዳም የገባው 53 ዓመት በበርሃ ኖሯል ፤ ይህ አባት እንዲህ እያለ ዘወትር ይጸልይ ነበር “ አቤቱ አምላኬ ሆይ
በዚህ በርሃ ከኔ የተሻለ የብህትውና ህይወት ያለው አባት አሳየኝ ” እግዚያብሔር ልመናውን ሰማው መልአኩን ላከለት
መርቶ ማርያም ግብጻዊት ጋር አደረሰው ወድቆ ሰገደላት ታሪኳን ሁሉ ነገረችው ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን አቀበላት
የዛሬ ዓመት እንዳትቀር ተመልሰህ ና ብላ ሸኘችው በዓመቱ ሲመለስ ሞታ አገኛት በጎኗ ተንበርክኮ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ
ገንዞም ቀበራት የቅድስት ማርያም ግብጻዊት እረፍቷ ሚያዚያ 6 ቀን 522 ዓ/ም ነው። ዛሬ ዕለቱ ሰንበት
እንደመሆኑ ከቤተክርስቲያን አስቀድሼ ስወጣ የኔቢጤዎች ስለ አርሴማ ቅድስት እያሉ ምጽዋት ይጠይቃሉ ምናለበት ስለ
ማርያም ግብጻዊት እያሉ በለመኑ ስለ ተመኘው ዳሩ እነሱ ምን ያድርጉ ማን አሰተማራቸው ማንስ ነገራቸው፤ ዋ
ይህችን የመሰለች ድንቅ እናት መታሰቢያዋ ይረሳ፤ የውኃ ቀን፤ የወዛደሮች ቀን፤የሴቶች ቀን፤ የምናምን ቀን እንኳን
አልተረሰማ አልተዘነጋም፤ እኔ ግን እላለው እናቴ ማርያም ግብጻዊት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፡፡ ከዚህ በታች ያለው
ስዕል ቅዱስ ዞሲማስ ማርያም ግብጻዊትን ሲያቆርባት ነው፡፡ የማርያም ግብጻዊት ገድል በሃይቅ እስጢፋኖስ አቡነ
እየሱስ ሞኣ ገዳም አማካኝነት ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ገብያ ላይ ይገኛል፡፡ ድንቅ ገድል ታፋጭ ታሪክ ነው፡፡
ከማርያም ግብጻዊት በረከት ያሳትፈን፡፡
No comments:
Post a Comment