Wednesday, January 30, 2013

ጥር 23


  "ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁና፤" 1ኛ ጢሞ 1፤ 1 ይህን መልዕክት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ቅዱስ ጢሞቲዎስ የላከለት ነው። ዛሬ ጥር 23 ቀን የዚህ የከበረ ሐዋርያ የጢሞቲዎስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ አገሩ ልስጥራን ፤ አባቱ ኮከብ ቆጣሪ እናቱ አይሁዳዊት ነበሩ በኃላ በቅዱስ ጳውሎስ ስብከት አምነው ተጠምቀዋል ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቲዎስን ባየው ጊዜ ወደደው የእግዚያብሔር ጸጋ በላዩ ላይ ነበርና ይላል ሐዋ 16፤ 1 አስከትሎታል ብዙ አገርም አብሮት ዞሮ አስተምሯል ታላቅ መከራ ብዙ ሐዘን ደርሶበታል በኃላም ብቃቱን አይቶ በኤፌሶን ኤጲስ ቆጶስ አድርጎ ሾሞታል በዚያም ብዙዎችን ወደ ቀናች ኃይማኖት መልሷል በመጨረሻም በዛሬዋ ዕለት በሰማእትነት አርፏል። በረከቱ ይደርብን።

ጥር 22



የቅዱስ ኡራኤል በዓለ ሲመቱ ነው፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን የመነኮሳት አባት ታላቁ ጻድቅ አባ እንጦንስ  የእረፍት ቀኑ ነው፤ ይህ አባት ወላጆቹ በሀብት የከበሩ ነበሩ እነርሱ ሲሞቱ ንብረቱን በሙሉ ለድሆች መጽውቶ አናምስት አናምርት አካይስት አቃርብት ካሉበት፤ ነቀዐ ማይ ልምላሜ እጽ  ከሌለበት ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በርሃ ገባ በዚያም በተጋድሎ  መኖር ጀመረ ሰይጣናት  በዘንዶ በጊንጥ እጅግ በሚያስፈሩ አውሬዎች እየተመሰሉ ያስፈራሩት ጀመርአባቱ አዳም ከገባበት እገባለሁ ብሎ ነው እኮ ከዚህ የመጣውእያሉ ይስቁበት ይሳለቁበት ነበር እየደበደቡ ስቃይ አጸኑበት እርሱ ግን በትህትና እናንተ ብዙ እኔ አንድ እናንተ ኃያላን እኔ ደካማ እናንተ ረቂቃን እኔ ግዙፍ በአምላኬ ኃይል ካልሆነ እንዴት እችላቹዋለሁ እያለ በትህትና ተዋጋቸው ነገር ግን መከራውን መቋቋም ሲያቅተው በቃ ወደ ከተማ ልመለስ ብሎ አንድ እግሩን ከውስጥ አንድ እግሩን ከውጭ አድርጎ ሲያወጣ ሲያወርድ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የሰሌን ቆብ አድርጎ የሰሌን ልብስ ለብሶ የሰሌን መቋሚያ ይዞ ከበሩ ፊት ለፊት ጸሎት ሲያደርግ አየ የዚህን መልአክ ፍጻሜውን ሳላይማ አልሄድም ብሎ ቆመ መልአኩ መጀመሪያ ለሥላሴ አንድ ስግደት ሰገደ ከዚያም ጸሎት አደረሰ ወንጌል አነበበ በመጨረሻም አንድ አቡነ ዘበሰማያት ብሎ ሦስት ጊዜ ሰገደ እንደዚህ እያደረገ 12 አቡነዘበሰማያትን አድርሶ 36 ጊዜ ሰገደ በእያንዳንዱ ሶስት ሶስት ጊዜ፤ ከዚያም ቁጭ ብሎ የያዘውን ሰሌን መታታት (መስፋት) ጀመረ፤በ 3 6 9 እና 11 ሰዓትም እንደዚሁ እያደረገ አሳየውና እንጦንስ ከሚመጣብህ ከሰይጣን ጾር ለመዳን እኔ እንዳደረግሁት ዘወትር አድርግ ብሎ ስርዓተ ምንኩስናን አስተምሮት ከእርሱ ተሰውሯል፤አባ እንጦንስም መልአኩ እንዳሳየው  ጸሎት እያደረገ ሰሌን እየሰፋ በተጋድሎ ኖሯል፤ ከእለታት በአንዱ ቀን ከአባ ጳውሊ ጋር ተገናኝተው መጨዋወት ጀመሩ ይህን ቆብ ማን ሰጠህ ይልዋል ከእግዚያብሔር ነው የተቀበልኩት አለው፤ አባ ጳውሊ አደነቀይልቅስ እስኪ ከኔ በኃላ እንደዚህ ዓይነት ቆብ የሚያደርግ መኖር አለመኖሩን ወደ እግዚያብሔር ጸልይሊኝ ይለዋል፤ አባ ጳውሊ ሲጸልይ ነጫጭ ርግቦችን ያያል ደስ አለው ከአንተ በኃላ ያንተን ፈለግ የሚከተሉ ልጆችህ ይነሳሉ ይለዋል እስኪ እባክህን ደግመህ ጸልይሊኝ ሁሉም የኔ ልጆች ናቸውን ይለዋል ሲጸልይ አንዳንድ ጥቁር ነገር የተቀላቀለባቸውን ያያል ገረመው ሁሉም ጻድቃን አይደሉም ጽድቅና ኃጢያትን የሚቀላቅሉም አሉበት ይለዋል፤ ለሶስተኛ ጊዜ ቢጸልይ ጥቋቁር ቁራዎችን ይመለከታል ድምጹን አሰምቶ ያለቅሳል ምነው ይለዋል በኃለኛው ዘመን የሚነሱት መነኮሳት ሹመት ሽልማት ፈላጊ፤ ገንዘብን የሚወዱ፤ ፍቅር የሌላቸው ትዕቢተኞች ናቸው  በፈረስ በበቅሎ ነው የሚሄዱት፤ከመኳንንት ጋር ቁጭ ብለው ኃጢያትን የሚዶልቱ ናቸው አለው  እስኪ እባክህን በንስሃ ይጠራቸው እንደሆነ ጠይቅሊኝ ይለዋል ይዚህ መልስ አልመጣለትም ይላል መጽሐፈ መነኮሳት 2ኛው ወይንም ፊሊክስዩስ፤በነገራችን ላይ በፈረስና በብቅሎ ነው የሚሄዱት ያለው ያኔ 3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስለሆነ ነው ለዚህ ዘመን ስንመነዝረው ሐመርና ኮብራ መሆኑም አይደል። አባ እንጦንስ የእረፍት ቀኑ ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶለታል ጥር በባተ 22ኛው ቀን አርፏል። ከመልአኩ ቅዱስ ኡራኤል ከአባ እንጦንስ በረከታቸውን ያሳትፈን።

 

Tuesday, January 29, 2013

ጥር 21 የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት

“ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ”
ጥር 21 በዓለ አስተርእዮ (የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት)
እንኳን ለዚህች ታላቅ በዓሏ አደረሰን፡፡ 

ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበት ዕለት ነው፡፡
ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ትርጉሙ ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡ በማለት አደነቀ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
... የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሁድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላዕክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁミ አለችው፡፡ በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅስስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ ባባ ይዘወት ወደ ጌሰማኒ ሲስደት አይተው ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለም ብሎ ኑ እናቃጥላት ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፡፡ የታዘዘው መላእክት መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ድኖለታል፡፡ ከዚህ ቦሃላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ በእጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡
አንድም በዓሉ-፡ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነት ተወልዶና ማንነቱ በይፋ ታውቆ በተገለጠበት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር የ“አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል፡፡ አስቀድመው አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ ተበትነው ነበርና በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሁሉም ደመናን ጠቅሰው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መርቶ አመጣቸው እንጂ ለምን እንደመጡ አያውቁም ነበር፡፡ እመቤታችንም ለምን እንደመጡ ጠየቀቻቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ሆይ! የመምጣታችን ምሥጢርማ እኛ አንቺን እንጠይቅ እንጂ አንቺም እኛን ትጠይቃለሽን? ሁላችንም ለምን እንደመጣን አናውቅም፡፡ ለምሳሌ እኔ አስቀድሜ በአንጾክያ ነበርኩኝ አሁን ግን እነሆ እዚህ ነኝ፡፡ ለምን እንደመጣሁኝ ግን አላውቅም” አላት፡፡ እርሷም ሁሉም በአጠገቧ በተሰበሰቡ ጊዜ የሚሆነውን ነገር አስቀድማ ከልጇ ከወዳጇ አውቃ ተዘጋጅታ ነበርና ለምን እንደመጡ (ዕረፍተ ሥጋዋን ለማየት እንደሆነ) ነገረቻቸው፡፡ ሌሊቱንም በሙሉ በጸሎትና በማኅሌት ደግሞም በዝማሬ ሲያመሰግኑ አደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የተወደደችው እናት በረከቷን አሳድራባቸው በሰላም አንቀላፋች፡፡ ነፍሷም በዐብይ ዕልልታና በታላቅ ምስጋና በመላእክት እጅ ወደ አምላኳ ሄደች፡፡ ኋላ ሐዋርያቱ ዮሐንስን ሲያገኙት፡- “እመቤታችን እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ዐርፋለች” አላቸው፡፡ የቀሩት ሐዋርያት “ዮሐንስ ያን ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ አይቶ እኛስ ሳናይ እንዴት እንቀራለን?! አቤቱ ለእኛም ቸርነትህን አድርግልን” ብለው በነሐሴ መባቻ በአንድነት ሆነው ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርብ የአንድ ሳምንት ጾምና ጸሎት ጀመሩ፡፡ በሁለተኛው ሱባዔ ማብቂያ ዕለት ነሐሴ 14 ቀን እሑድ የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ መልአኩ ከገነት አምጥቶ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ልመናቸው ስለ ተፈጸመላቸው ፈጣሪያቸውን በጸሎት አመስግነው በዚያችው ዕለተ እሑድ ቅዱስ ሥጋዋን ወስደው ቀብረውታል፡፡ እርሷም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ማክሰኞ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ- እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘው ይህ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይታ የመነሣቷ እውነታ ነው፡፡ የአዛኚቱ ድንግል አማለጅነትና በረከት አይለየን፡፡ ሁላችንም ባለንበት ይህ ታላቅ በዓሏን እያሰብን ጸልየን የበረከቷ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡ መልካም በዓል !!

Friday, January 25, 2013

ጥር 18 የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ

…ዳግመኛም ያ ከሃዲ ንጉስ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንዱ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ፤በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ ፤ ከዚህም በኃላ እንደመጭመቂያ ሆኖ ከተሰራ የስቃይ መሳሪያ ላይ አወጡት ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት እንዲጨምቁት አዘዘ፤አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት ነፍሱ ከስጋው ተለየች የሰማእቱን ሰጋ አቃጠሉት ፈጩት አመድም ሆነ በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ላይ በነፋስ ዘሩት ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ነው ወታደሮቹ የታዘዙትን  ፈጽመው  ተመለሱ። ያንጊዜም መብረቅ ነጎድጓድ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ምድርም ከመሰረቷ እስክትናወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በብሩ ደመና ወረደ በተራራውም ላይ ተቀመጠ አራቱን የምድር ነፋሳት የሰማእቱን ስጋ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው ከሞትም አስነሳው ኃይሉን አሳደረበት ባርኮትም ወደ ሰማይ አረገ፤ ከዚህ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሮጠ ወታደሮቹን ተከተላቸው ወንድሞቼ ቆዩኝ ከናንተ ጋር ልሂድ እያለ ተጣራ የነዚህ የወታደሮች ቁጥር አራት ነው ስማቸው ህልቶን፤አግሎሲስ፤ሶሪስና አስፎሪስ ነው፤ ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፤ በኃላም በሰማእትነት ሞተዋል፤ ይህ የሆነው ጥር 18 በዛሬዋ ቀን ነው ይህንንም ቀን " ዝርዎተ አጽሙ " ስትል ቤተክርስቲያን ሰማእቱን አዘክራ ትውላለች፤ በስሙ በታነጹለት አብያተክርስቲያናት በሙሉ ታቦተ ህጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። አራዳ ጊዮርጊስን የተከሉት ደጉ ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ናቸው ታዲያ የዚህን ታላቅ ደብር መሰረቱን ሲጥሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ከሚገኝበት ቦታ አፈሩን በመርከብ አጓጉዘው በበቀሎ በፈረስ አስጭነው መሰረት አድርገውታል፤ይህንን ከአባቶቻችን የሰማነው ነው፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።
 ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ምዕራፍ  6 ፤  15 - 18

Tuesday, January 22, 2013

ጥር 15


 

ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀኑ ጥር 15 ሐሙስ ከሌሊቱ 6 ሰዓት የሶስት ዓመቱ ህጻን ቅዱስ ቂርቆስ በሰይፍ አንገቱ ተቆርጦ በሰማዕትነት አረፈ በበነጋው ዓርብ ጥር 16 ቀን እናቱ እየሉጣም በተመሳሳይ በሰማዕትነት አረፈች። እነዚህ ሰማዕታት ከመሞታቸው በፊት ብዙ መከራ ተቀብለዋል ከአገር አገር ተሰደዋል፤ ከተቀበሉት  መከራዎች የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ፈጠኖ ደራሽነቱን አማላጅነቱን ያየንበት ሐምሌ 19 ከእሳት ያዳነበት ቀን አንዱ ነው። በአገራችን ኢትዮጰያ በሰማዕቱ ቂርቆስ ስም በርካታ ገዳማትና አብያተክርስቲያናት አሉ ከነዚህም የጣና ቂርቆስ ገዳም ዋንኛው ነው፤ በዚህ ገዳም ታቦተ ጽዮን ለረጅም ዘመን አርፋበታለች፤ የኦሪት መስዋትም ይሰዋበት ነበር፤ በአዲስ አበባ ለገሃር ባቡር ጣቢያ አካባቢ የሚገኘውን ቤተክርስቲያን የተከሉት ደገኛው ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ናቸው የተከሉበት ምክንያትም  አዲስ አበባ ተስቦ በሽታ ገብቶ ህዝቡን እየጨረሰ ነበር፤ ታዲያ ምን ይሻላል ብለው ሽማግሌዎችን ሲያማክሩ፤ ጃንሆይገድለ ቂርቆስ ላይ እንዲህ የሚል ቃል ኪዳን አለ ቤተክርስቲያንህ ባለበት ቦታ ርሃብ ቸነፈር ፈጽሞ አይደርስም ይላል የሰማዕቱን ታቦት ቢያስመጡ ቤቱንም ቢሰሩለት ይህ ሁሉ መከራ ይወገዳል አሏቸው፤ የሽማግሌዎቹን ምክር ሰምተው አሁን ያለውን ቤተክርስቲያኑን አነጹ ታቦቱንም አስገቡ በዚህም በሽታው ወረርሺኙ ቀንሶላቸዋል ይላል፤በዚህ ቤተክርስቲያን ዛሬ ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። ከቅዱስ ቂርቆስ ከእናቱ እየሉጣም በረከታቸውን ያድለን።