Tuesday, February 18, 2014

የካቲት 8

የካቲት 8 በዚህች ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የአይሁድን ህግ ሊፈጽም ከሁለት የርግብ ጫጩቶች ጋር ወደ ምኩራብ የገባበት ቀን ነው። ሉቃ 2፤22 የአረጋዊ ስምኦንን ታሪክ እዚህ ጋር ያመጡታል። በጥሊሞስ የሚባል ኃያል ንጉስ ነበር ይላል ከገናንነቱ የተነሳ ዓለምን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ የገዛ፤ “ስሜ ዝንት ዓለም እንዲታወስ ምን ልስራ” አለ፤ አማካሪዎቹ “46ቱን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን አስተርጉም” አሉት 70 የአይሁድ ሊቃውንትን ሰብስቦ ከዕብራይስጥ ቋንቋ ወደ ጽርዕ ቋንቋ እንዲተረጉሙ አደረገ ከ 70 ሊቃውንት አንዱ ስምኦን ነበር ትንቢተ ኢሳይያስን እንዲተረጉም ደረሰው፤ ሲተረጉም ኢሳ 7፤14 ድንግል በድንግልና ትጸንሳለች ከሚለው ደረሰ፤ እንዴት ድንግል ትጸንሳለች ይህንን ብጽፍ ንጉሱ ከፍ ብሎ አንገቴን ዝቅ ብሎ ባቴን ይቆርጠኝ የለምን ብሎ “ድንግል” የሚለውን “ሴት” አለው እንቅልፉን ተኝቶ ሲነቃ ሴት የሚለው ተፍቆ “ድንግል” ተብሎ ተጽፎ ያገኛል አሁንም ሰርዞ “ሴት” ብሎ ይጽፋል እስከ ሦስት ጊዜ እንዲሁ ሆነ፤ በሶስተኛው ሊያጠፋው ሲል መልአኩ ተገልጾ አታጥፋው ይህን ሳታይ አትሞትም ብሎታል፤ሉቃ 2፤26 ይህንን ተስፋ ሲጠባበቅ 500 ዓመት በምኩራብ ከአልጋ ተጣብቆ ኖረ። በዛሬዋ ቀን ግን ያ የተነገረው ተስፋ ተፈጸመ ድንግል በድልግልና ወልዳ አየ ማየት ብቻ አይደለም ህጻን የሆነውን እግዚያብሔር በእጁ ታቀፈው እንዲህም አለ “አይኖቼ ማዳንህን አይተዋል ባሪያህን በሰላም አሰናብተው” ሉቃ 2፤30። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን የገዳመ ሲሐቱ አባ ኤልያስ አረፈ፤ የበቃ ባህታዊ ነው ከዕለታት በአንዱ ቀን ንጉስ ቴዎዶስዮስ አንድ የሚያረጋጋኝ አባት ላኩልኝ ብሎ ወደ ገዳመ ሲሐት መልእክት ይልካል አባቶችም የበቃ አባት ነው ብለው አባ ኤልያስ ይልኩታል፤ ንጉሱ እንዲህ ይለዋል በገድል ነብዩ ኤልያስን እንደምትመስል መነኮሳቱ ነገሩኝ አለው፤ አባ ኤልያስም ቆፍጠን ብሎ ንጉስ ይቅርታ ያድርጉልኝ ነብዩ ኤልያስ ስለደግነቱ ቁራዎች ምግቡን ያመጡለት ነበር (1ኛ ነገ 17፤6) እኔ ግን ምግቤን በጸሐይ ላይ ባሰጣው ቁራ ይዞት ይሄዳል አለው፤ ንጉሱ ሰምቶ ከቃሉ ጣዕም ከአንደበቱ ቅልጥፍና የተነሳ አደነቀ ይላል፤ ይህ አባት ወደ ገዳሙ እስኪመለስ ከንጉሱ ማዕድ ምንም ምን አልቀመሰም በተጋድሎ ኖሮ በዛሬዋ ቀን አርፏል፤ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን የከበረች እመቤት ቅድስት አመተ ክርስቶስ አረፈች አገሯ ቊስጥንጥንያ ነው፤ባሏ መስፍን ነበር ሲሞት ገንዘቧን ሁሉ ለድሆች ሰጥታ በአንድ ጥልቅ ዋሻ ውስጥ 11 ዓመት በተጋድሎ ኖረች ዘወትር በሰርክ አዕዋፍ የእፅዋት ፍሬ ያመጡላት ነበር፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ የንጉሱ ግብር ሰብሳቢ በዘመናችን ቋንቋ ግብር የሚተምን ሲዘዋወር ከአንድ ገዳም ይደርሳል ብዙ የእጽዋት ፍሬ ያለበት ዛፍ ያገኛል ይህ የማን ነው ብሎ አበምኔቱን ይጠይቀዋል እኛ አናውቅም አዕዋፍ ዘወትር ከነቅርንጫፉ እየቆረጡ ሲበሩ እንመለከታለን ራሳቸው ግን አይበሉትም ይህ ሁሌም ያስደንቀናል አሉት፤ አዕዋፉ የሚበሩበትን አቅጣጫ ተከትለው ጉዞ ጀመሩ ከብዙ ድካም በኋላ ወለተ ክርስቶስ ካለችበት ዋሻ ደረሱ ገብተው በረከቷን ተቀበሉ ለአበምኔቱ ታሪኳን ነገረችው እርሱም ጻፈው በበነጋው አረፈች በታላቅ ክብር በብዙ ዝማሬ ቀበሯት፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከቅዱሳኑ በረከት ያሳርፈን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

የካቲት 5

የካቲት 5 በዚህች ቀን አስቀድሞ ኃጢያተኛ የነበረው አባ ዕብሎይ አረፈ። ይህ አባት ከኃጢያት ስራ ምንም የቀረው የለም ማመንዘር መስረቅ መግደል የዘወትር ተግባሩ ነበር፤ ከሁሉም የከፋው ግን ከዕለታት በአንዱ ቀን አንዲት ሴት የመውለጃዋ ቀን ደርሶ ስታምጥ አየ ሰይጣን በልቡ ክፉ ሐሳብ ጨመረበት ህጻኑ እንዴት እንደተኛ ለመመልከት የሴቲቱን ጸጉር ይዞ ከምድር ጣላት በሾተልም ሆዷን ቀደደው ተሰቃይታ በፃር ሞተች ህፃኑም አልቆየም እናቱን ተከተላት፤ ከዚህ በኃላ የሰራውን ስራ አስቦ ደነገጠ አዘነ መራራ ለቅሶም አለቀሰ በትሩን ብቻ ይዞ ወደ በርሃ ሮጠ እራሱን የሚያስጠጋበት ዋሻ አልፈለገም ከአራዊት ጋር የሚኖር ሆ...ነ እንጂ ቅጠል እየበላ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር እየተፈራረቀበት 40 ዓመት እያለቀሰ ጽኑ ገድል ተጋደለ ሰውነቱ ጥላሸት መሰለ ቆዳው ከአጥንቱ ተጣበቀ፤ የጌታ ቃል መጣለት እንዲህ የሚል "ስለሴቲቱ ደም እግዚያብሔር ይቅር ብሎሃል ጽና በርታም" አለው የበለጠ የሚጋደል ሆነ ከአንድ ዓመት በኃላ 70 ዓመት ሙሉ የሰው ፊት ሳያይ ዘግቶ የኖረ ባህታዊ ወደርሱ ላከለት የሆነውን ነገር ሁሉ ነገረው አይዞህ እግዚያብሔር ይቅር ብሎሃል ነገ የጌታ መልአክ የክርስቶስን ስጋና ደም ሊያቀብልህ ይመጣል ተዘጋጅ አለው፤ እንዳለውም እሁድ ሰንበት ጠዋት የጌታ መልአክ በመነኩሴ አምሳል ስጋ ወደሙን ይዞ ተገለጸ ከዚያ ቀድም እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ነፍስን የሚያለመልም ጣፋጭ መዓዛ ሸተተው ስጋ ወደሙን ተቀበለ ጠቁሮ የነበረ ሰውነቱ ጸአዳ መሰለ እንደ ፀሐይም አበራ በበነጋው የካቲት 5 መልአክት ነፍሱን ተሸክመው እየዘመሩ ወደ አርያም በረሩ፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ከዚህ በኃላ መልአኩ ለዚያ ባህታዊ "ሰው ከእግዚያብሔር ምህረት ተስፋ እንዳይቆርጥ በኃጢያት ለወደቁ አለኝታ ይሆን ዘንድ የአባ ዕብሎይን ገድሉን ጽፈሕ ለመነኮሳቱ ስጣቸው" አለው፤ እንደተባለውም አደረገ። እየው እኛም ሰማነው አነበብነው መሐሪነትህን እንናገራለን ይቅርባይነትህንም እንመሰክራለን፤ እንዲህ እያልን "ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና" መዝ 16፤9 ከጻድቁ በረከት ያሳትፈን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Sunday, February 9, 2014

የነነዌ ሰዎች የንስሐ ምስክሮች

የነነዌ ጾም ከሰባቱ የቤተክርስቲያን አጽዋማት አንዱና የዐቢይ ጾም ማዘጋጃ ደወል ነው፡፡ ይህ የነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ በቤተክርስቲያናችን በጣም ታላቅ ዋጋ ያለውና የራሱ መዝሙር የሚዘመርለት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት ታላቅ መታሰቢያ ያለው ታሪክ ነው፡፡ ራሱ ጌታችንም የነዌ ሰዎችን የንስሐ ታሪክ በመጥቀስ አይሁድን ገስጾበታል፤ በፍርድ ቀንም በዚያ ትውልድ ዘንድ እንደሚፈርዱበት ተናግሯል፡፡ ይህም የሆነበት የነነዌ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ የንስሐ ታሪክ ስላላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስደሳች የንስሐ ታሪክ በጾመ ነነዌ ከሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት አንጻር ለመመርመር እንሞከራለን፡፡
ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ሁሉ ንስሐ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ በዚህ ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች ባለቡት ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን ሁሉ የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም ጊዜ በተለየ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስባቸው የጾም ወቅቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ታላቁና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዐቢይ ጾም ከእያንዳንዱ ምእመን ልቦና የንስሐ ፍሬን ትፈልጋለች፤ ያለትንሣኤ ልቦና /ንስሐ/ የክርስቶስን ትንሣኤ በእውነትና በደስታ ማክበር አይቻልምና፡፡ ለመሆኑ ከንስሐ የሚያሰናክሉን ነገሮች ምን ምን ናቸው? የነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለዚህ ምን ያስተምረናል?
1. ቅንጦትን መውደድ
ምንም እንኳን በደፈናው ገንዘብ የኃጢአት ምንጭ ነው ባንልም እንደ ወንጌል ትእዛዝ በክርስቲያናዊ መንገድ ካልተያዘ ግን እግዚአብሔርን ሊያስረሳና የኃጢአት ማስፈጸሚያና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜም ገንዘብና ባለጸግነት ከእግዚአብሔር በመለየታችን ያጣነውን ሰላምና ደስታ ለማግኘት ተስፋ የምንጥልበት ጣኦት ሆኖ ሊቀየር ይችላል፡፡ በሀብታችን በምናገኘው ጊዜያዊ ደስታና ሰላም ዘላለማዊውንና ፍጹምን የእግዚአብሔር ስጦታ መፈለግ፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን መናፈቅ ልናቆም እንችላለን፡፡ በዚህ መልኩ ብልጽግና ከንስሐ የሚያሰናክል ወጥመድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር ሀብት እንኳ ቢሰጠን ለተቸገረ በመመጽወት፣ ልጆቻችን በክርስቲያናዊ መንገድ በማሳደግ፣ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በማፋጠን የእውነተኛ ደስታና የጽድቅ መንገድ እንድናደርገው እንጂ እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍሳችንን ጥሪዋን በማደናቀፍና ጩኸቷን በማፈን በሥጋ ድሎት ውስጥ የምንደበቅበት መሣሪያ እንድናደረገው አይደለም፡፡ ለ«ታላቂቷ ከተማ» ነነዌም የጥፋት መንገድ የሆናት በብልጽገናዋና በታላቅነቷ እግዚአብሔርን ረስታ የኃጢአት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክ ውስጥ ገንዘብ ለዮናስ ከእግዚአብሔር የመከለያ መሣሪያ ሲሆን እናገኘዋልን፡፡ «. .. ከእግዚአብሔርም ፊት ኮብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ /ወደ መርከቧ/ ገባ» እንዲል /ዮና፤1-3/፡፡
በዚህ ሰዓት ለዮናስ ገንዘብ ባይኖረው ይሻል ነበር፡፡ እኛም ቢሆን ከንስሐ የሚመልስ፣ ለኃጢአት መሣሪያ የሚሆን ሀብት ከሚኖረን በድኅነት ብንኖር ይሻለናል፡፡ ምንም እንኳ በቤተክርስቲያናችን ትውፊት ዐቢይ ጾም አብዝተን የምንጸልይበት፣ በጾም በስግደትና በምጽዋት ልናሳልፈው የሚገባ ወቅት ቢሆንም ፤ አሁን አሁን ግን ገንዘብ ማግበስበሻ እየሆነ እንደሆነ እናያለን፡፡ በመሠረቱ በጾም ወቅት ከሆዳችን የምንቀንሰው ገንዘብ እንድናጠራቅመው ሳይሆን እንድንመጸወተው የሚገባ ነው፡፡ ለማጠራቀምማ የማያምኑ ሰዎችስ ምግብ ይቀንሱ የለ? ለዚህ ነው በነነዌ ጾም በመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት «አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሀብታችሁ ተበላሽቷል፣ ልብሳችሁም በብል ተበልቷ፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል፡፡ ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል፡፡ እነሆ እርሻሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፣የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቷል፡፡ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል፡፡» በማለት አስፈሪ ተግሳጽ የሚያስተላልፈው፡፡ ስለዚህ በዐቢይ ጾም አብዝተን የምንመጸውትበት፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ስጦታ የምንፈልግበት፣ የንስሐ ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡
2. ለኃጢአት ሌላ ተጠያቂ መፈለግ
ሌላው ከንስሐ ሲያርቀን የሚገኘው ምክንያት በሰዎች መፍረድ ነው፡፡ በሰዎች የሚፈርድ ሰው ራሱን የሚያጸድቅ ነው፡፡ ራሱን ያጸደቀ ደግሞ ንስሐ መግባትና ከኃጢአት መመለስ ዳገት ይሆንበታል፡፡ ከነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ ውስጥ ለንስሐ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ መርከበኞቹና የነነዌ ሰዎች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ዮናስ ግን ከታሪኩ መጀመሪያ እስከ መጨረሻዋ ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር ያጉረመርም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከእግዚአብሔር መኮብለሉና የነነዌ ሰዎችን ድኅነት መቃወሙን እንደ ስህተት እንጂ እንደራሱ ስህተት አለመቁ ጠሩ ነው፡፡ ለዚህ ነበር ከእግዚአብሔር ኮብልሎ ሲሔድ እንኳ ምንም ዓይነት ጭንቀት ሳይሰማው «በከባድ እንቅልፍ» ተኝቶ የነበረው /ዮና.1-5/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ኃጢአት እግዚአብሔርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በራሳቸው ከመፍረድ ይልቅ በሰዎች መፍረድ ይጀምራሉ፤ ወይም የኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔርን አድርገው ይገኛሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ የራሱን ክብር ፈላጊነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት የኃጢአቱ ምክንያት ማድረጉ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህም ለብዙ ጊዜ ከንስሐ እንዳዘገየው ከታሪኩ እንማራለን፡፡ በተቃራኒው ለንስሐ ቅርብ የሆኑት መርከበኞች በዮናስ ላይ ለመፍረድ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስናይ ቀድሞውኑ በዮናስ አለመታዘዝ ምክንያም ቢሆን እግዚአብሔር ወደ ንስሐ ሊመልሳቸው የፈለገ ይህን አይቶ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
በጾመ ነነዌ የመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ጳዉሎስ መልእክትም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡- «ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፣ የምታመካኘው የለህም በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኮንናለህና፡፡ አንተም ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና፡፡ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለንና፡፡ . . . ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ስታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ»/ሮሜ.2-1-5/፡፡ በተቃራኒው ግን በሰው ላይ ከመፍረድ በራሳቸው ላይ መፍረድን የሚመርጡ ሰዎች ለንስሐ ቅርብ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ቀን ማክሰኞ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም የሚያብራራው ይህንኑ ነው/1ቆሮ.4-1/፡፡
3. የእግዚአብሔርን ተግሳጽ አለመቀበል
በነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ሰዎችን ሲገስጽ እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ዮናስን በማዕበል፣ ወደባሕር እንዲወረወር በማድረግ፣ አሳ አንበሪ እንዲውጠው በማድረግ እግዚአብሔር ወደ ትክክለኛ መንገዱ ሊመልሰው ቢጥርም በዚህ ሁሉ ሊመለስ አልቻለም፤ ከአሳ አንበሪ አፍ ወጥቶ ሔዶ ቢሰብክም እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው ግን በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ጀምሯልና፡፡ ድሮም ቢሆን በፍርሃት እንጂ ስህተቱን ተቀብሎ አልነበረም ወደ ነነዌ ሔዶ የሰበከው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ነፋስ፣ አሳ አንበሪ፣ ትል፣ ፀሐይ/ እንዴት እንደሚታዘዙለት እርሱ ግን ታላቅ ነቢይ ሲሆን አልታዘዝም ማለቱን በማሳየትም ገስጾታል፡፡ በመጨረሻም ለንስሐ በቅቷል፡፡ መርከበኞቹም በመርከባቸው ላይ የተነሣው ማዕበል ተግሳጽ ሆኗቸው ወደ ንስሐ ተልሰዋል፡፡ ከዘላለም ሕይወት እንዳንለይ አጥብቆ የሚፈልገው እግዚአብሔር ልዩ ልዩ መከራዎችንም በማምጣት ወደ ንስሐ እንድንመለስ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ተግሳጽ ግን በትክክለኛ ወይም በተሳሳተ መንገድ መልስ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ ካወቅንባቸውና ከተጠቀምንባቸው ችግሮችና መከራዎች ወደንስሐ የሚመሩ መንገዶች ናቸው፡፡ የነነዌ ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ በነነዌ ጾም በቅዳሴ የሚነበቡት የሚከተሉት ምንባባትም በአጽንኦት የሚገልጹት ይህንኑ ነው፡፡
ምስባክ:- «ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ፡፡
እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል
የእኔ ስዕለት ለሕይወቴ አምላክ ነው፡፡» /መዝ.41-7-8/
መልእክት:- «. . . ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል. . .» /ሐዋ.14-22/፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሳዛኙ ነገር ሰው ካለፈ ሕይወቱ አለመማሩ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክም የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተሳፈረበትን መርከብ ካናወጠ፣ ዮናስ በአሳ አንበሪ እንዲዋጥ ካደረገ በኋላ እንኳ እግዚአብሔር በነነዌ ሰዎች ላይ ያሳየው ምሕረት ዮናስ ሞትን እስኪመኝ ድረስ እንዲያዝንና በእግዚአብሔር ላይ እንዲያጉረመርም አድርጎታልና፡፡ በእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ተግሳጻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢመጣም ከኃጢአት ባለመመለስ ከዮናስ ያልተለየ መልስ ነው የምንሰጠው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ራሳችንን የምናይበት፣ በሕይወታችን ያደረጋቸውን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንመረምርበት፣ በውስጣችን ያደፈጡትን አውሬዎች የምናድንበት የተረጋጋና ሰፋ ያለ ጊዜ ስለሌለን ነው፡፡ ይህን አጥብቃ የተረዳችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መንገድ የሚጠራንን የእግዚአብሔር ድምፅ የምናዳምጥበት፣ በመልካም ምክንያቶች የተሸፈኑ ነገር ግን መልካም ያልሆኑና መልካም ልንሠራበት የምንችለውን የሕይወት ጊዜዎችን የሚያቃጥሉ ከንቱ ምኞቶቻችን፣ የማይጨበጡና የማይደረስባቸው «ክፉ ተስፋዎቻችን» ሁሉ የምንመረምርበት፣ መልካሟንና እውነተኛዋን ነገር ግን አስቸጋሪዋንና ጠባቧን የሕይወት መንገዳችን አጉልተን «የምናስምርበት» ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥታናለች፤ ይህም ዐቢይ ጾም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበትም የዚህን አስቸጋሪና አወናባጅ ዓለም በድል የተወጡ ሰዎች የሚያዩትን የዘለዓለማዊን ሕይወት «ቀብድ» የትንሣኤውን ብርሃን እናያለን፡፡ ዐቢይ ጾምን እንደሚገባ ያላሳለፈ ክርስቲያን ግን የትንሣኤን ድግስ በልቶ ሆዱን ይሞላ እንደሆነ እንጂ የትንሣኤን ታላቅ ደስታ መቅመስ አይችልም፡፡ ስለዚህም ዐቢይ ጾም ለክርስቲያን ታላቅ ስጦታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለጾም በጻፉት መጽሐፋቸው «በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ማለት ይከብዳል» በማለት የጻፉት፡፡
4. ክፉ እኔነት
በዮናስ ታሪክ ውስጥ ከብዙ የዮናስ ስህተቶች ጀርባ የነበረውና ንስሐውን ያዘገየበት ታላቁ መሰናከል ክፉ እኔነት ነው፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የነነዌ ሰዎችን ድኀነት ሳይሆን የራሱን ክብር እንዲመለከት ያደረገው በዮናስ ሕይወት ውስጥ በጥልቅ የተተከለ ክፉ እኔነቱ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ ታሪክ ውስጥ በርግጥም ዮናስ ስለራሱ እንጂ ስለሰዎች ሲያስብ አልታየም፡፡ ነቢዩ ዮናስ «እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ከምባል የነነዌ ሰዎች መጥፋት ይሻላል»«የዮናስ አምላክ ቃሉን ይቀይራል ከምባል የነነዌ ሰዎች ይጥፉ» ብሎ ያስብ እንጂ እግዚአብሔር ግን አላለም፡፡ አመድና ትቢያ የሆነው የሰው ልጅ ስለክብሩ ሲጨነቅ ክብር የባሕሪዩ የሆነ ሩህሩህ አምላክ ግን ማንም እንዲጠፋ አልፈቀደም፡፡
በርግጥ የነነዌ ሰዎች በመዳናቸው የዮናስም የእግዚአብሔርም ቃለ አልታበለም፡፡ ዮናስ «ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች» ብሎ ሰበከ፡፡ አመጸኛዋ ነነዌ ግን በቁጣ እሳት ከመጥፋቷ በፊት በንስሐ ራሷን አዋረደች፡፡ በዚያን ጊዜ ነነዌ በንስሐ አዲስ ፍጥረት የሆነች፣ እግዚአብሔር የሚያጠፋት ሳትሆን የሚወዳት ሌላ ነነዌ ሆነች፡፡ ዮናስ ሆይ በንስሐ የታደሰችው ነነዌ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ እንደማያጠፋስ ለምን አላሰብክም? ታላቁ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆይ ንስሐ የገባችዋን ነነዌን ማጥፋት አምላክህን አያስነቅፈውምን? በነቢዩ በዮናስ ውስጥ ያለው እኔነቱ በርግጥም እግዚአብሔርንም፣ የነነዌ ሰዎችንም እንዳያስብ መጋረጃ ሆኖበት ነበር፡፡
በነቢዩ በዮናስ ሕይወት ወስጥ ክፉ እኔነቱ በዚህ መልክ ቢገለጥም፣ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ግን በተለያየ መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን «እኔ ቅዱስ ነኝ» የማለት ክፉ እኔነት ተጠናውቶናል፡፡ ኃጢአታችን ለንስሐ አባታችንና ለጓደኞቻችን ስንናገር እንኳ «ኃጢአትን የመናገር ቅድስና» እንጂ ኃጢአተኝነታችን አይሰማንም፡፡ «እኔ ርኩስ ነኝ» ስንልም ራስን በፈቃድ ኃጢአተኛ የማድረግ «ቅድስና» እንጂ ልባዊ የሆነ ንስሐ አይሰማንም፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ «እኔ አዋቂ ነኝ» የማለት ክፉ እኔነት ይዞናል፡፡ «እኔ እኮ ምንም አላውቅም» ብለን ስንናገር እንኳን በልባችን ራስን ዝቅ ማድረግን «እያስተማርን» ነው በፍቅር ከተሰባሰቡ መንፈሳውያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል እንኳን «ወርቃማ መንፈሳዊ ምክሮችን» ለመለገስ እንጂ መች ፍቅርን 'ከታናናሾቻችን' ለመማር እንቀመጣለንና፡፡ በዚህም በባዶነታችን እንኖራለን፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን «ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች መድኃኒት አያስፈልጋቸውም» ብሏል፡፡ ሕመምተኞች መሆናችን አውቀን በንስሐ ብንቀርብ መድኃንኒት ይሆነናል፤ ራሳችንን አጽድቀንና «ቅዱስ ነኝ» ብለን በውሸት የጤንነት ስሜት መድኃኒት መፈለግ ከተውን ግን ከነኃጢአታችን እንሞታለን፡፡ ጌታችን ለእውራን ብርሃን፣ ዕውቀት ለሌላቸው ሰማያዊ ጥበብን የሚሰጥ ራሱ የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ራሳችን በአዋቂዎች ተራ ከመደብን መምህር አልፎን ይሔዳል፡፡ ጌታ አለማወቃቸውን ያወቁትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ጥበብን የሚፈልጉትን ሲያስተምር እንጂ «ምሁራንን» ሊያስተምር አልመጣምና፡፡ በኃጢአት መኖር እንደ ሀሞት መሮት፣ እንደጨለማ ከብዶት ከልቡ የሚጮኽን ተነሣሒ ለመቀደስ፣ እግዚአብሔር የዕውቀት ምንጭ የሕሊና ብርሃን መሆኑን አውቀው ከጥልቅ ከልቦናቸው ዕውቀትን የሚፈልጉትን ለማስተማር መጥቷልና እንደዚሁ ካልሆንን ከዚህ ጸጋ ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡
ይህን ሁሉ የሕይወታችን ውጥንቅጥ እንመረምርበት ዘንድ ታላቁ የቤተክርስቲያን ስጦታ ዐቢይ ጾም እነሆ፡፡
የእውነተኛ ንስሐ ውጤቶች በነነዌ ሰዎች ታሪክ
5. የዘላለም ሕይወት ተስፋ
ነነዌ የጥፋት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጣት ከተማ ናት፡፡ በሌላ አነጋገር ነነዌ ሞታ የተነሣች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ነቢዩ ዮናስም ወደ ባሕር ከተጣለ፣ በአሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ካደረ በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጠው ሰው ነው፡፡ መርከበኞችም መርከባቸው በማዕበል ከተመታች በኋላ፣ ማዕበሉ ካሸነፋቸው በኋላ በእግዚአብሔር ምሕረት ሌላ የመኖር ተስፋ የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የነነዌ ታሪክ የተስፋ ታሪክ ነው፡፡
ንስሐም በኃጢአት ከሞቱ በኋላ እንደገና የመኖር ተስፋ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትን ተስፋ ማድረግ ይከብዳቸዋል፤ ለዚህም ምክንያቱ በንስሐ አለመኖራቸው ነው፡፡ ሰው ያላየውን ነገር እንዴት ይናፍቃል? የማያውቀውን ነገርስ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? በንስሐ የሚኖር ሰው ግን የዘለዓለም ሕይወት ቀብድ የሆነ ትንሣኤ ልቦናን ይነሣልና የዘለዓለም ሕይወትን በተስፋ ይናፈቃሉ፡፡ ዐቢይ ጾምንም በንስሐና ራስን በመመርመር ያሳለፈ ሰው በትንሣኤው ትንሣኤን ይቀምሳልና ዘለዓለማዊውን ትንሣኤ በተሰፋ ይናፍቃል፡፡
በነነዌ ጾም የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባትም ይህን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡-
«. . . ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም፡፡» /ሮሜ.5-4-5/፡፡
«እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ፡፡» /ይሁዳ.1-20/፡፡
6. በእግዚአብሔር ዘንድ መከበር
በንስሐ የተመለሰችው ነነዌ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ከብራለች፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በማይገቡ ዘንድ በትውልዱ ሁሉ ምስክር ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ «የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም «ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ» እንዲል /ሉቃ.11-32/፡፡ የነቢዩ የዮናስ ታሪክም እንደዚሁ ነው፡፡ የንስሐ ሰባኪ የሆነው ራሱም ከብዙ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኋላ በንስሐ የተመለሰው ዮናስ የክርስቶስ ምልክት እንዲሆን እግዚአብሔር መፍቀዱ እግዚአብሔር ለተነሳሕያን የሚሰውን ክብር ያሳያል፡፡
ምንም እንኳን በዚህ ምድር ያለን ሰዎች የተነሣሕያንን ክብር ባናውቅም በሰማይ ያሉ መላእክት ግን በአንድ ኃጢአተኛ ንስሐ መግባት ታላቅ ደስታ ማድረጋቸው የንስሐን ክብር ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው ለንስሐ የተዘጋጀ ልብን በማየት እግዚአብሔር አስቀድሞ ነነዌን «ታላቂቷ ከተማ» ብሎ የጠራት /ዮናስ.1-2/፡፡ ተነሣሕያን የእግዚአብሔር ይቅርታና ፍቅር የሚገለጥባቸው ሰዎች ናቸውና በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ዘንድ የከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡
7. የእግዚአብሔርን ኃይል ማየት
በነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔር ኃያልነት በግልጥ ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ኃያልነትም በትዕግሥቱ፣ በፍቅሩ፣ ፍጥረትን በመግዛቱ፣ ለሰው ልጆች በሰጠው ድንቅ ነፃነት ወዘተ ተገልጧል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንዲትም ነፍስ ሳትጠፋ ሁሉም ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያሳየው የትዕግሥቱ ኃያልነት እንዴት ድንቅ ነው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምር ዘንድ ነቢይ የሆነው ዮናስ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቶ ሲኮበልል በሔደበት ሁሉ እየተከተለ በተለያየ መንገድ ወደ መንገዱ እንዲመለስ ይሠራ ነበር፡፡ ምናልባትም ሰው ዮናስን ይህን ያህል አይታገሰውም፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን 'የመምከር' ዕድል ቢሰጠን «ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ፤ ከነዚህ ድንጋዮት እንኳ ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት ትችላለህ፡፡ ለምን ዮናስን ትለምነዋለህ? ተወው ሌላ ነቢይ ወደ ነነዌ ላክ፡፡ ዮናስን ርግፍ አድርገህ ተወው ከነነዌ ሰዎች የራሱን ክብር አስቀድሟልና፡፡» እንል ይሆናል፡፡ በባሕሪዩ ታጋሽ የሆነው እግዚአብሔር ግን ዮናስ በንስሐ ይመለስ ዘንድ ጠብቆታል፤ በመጨረሻም ለክርስቶስ ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ነቢይ አድርጎታል፡፡

በነነዌ ታሪክ የእግዚአብሔር የፍቅሩ ታላቅነትም ተገልጧል፡፡ የእስራኤል አምላክ ይባል እንጂ ከአሕዛብ መካከል ለንስሐ የተዘጋጀ ሕዝብ ሲያይ ነቢዩን ልኮ ሕዝቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቀና ልብ ያላቸው፣ ዮናስ ሲተኛ እንኳ ለማያውቁት አምላክ ሲጸልዩ የነበሩትን መርከበኞችንም በዮናስ ምክንያት እንዲያውቁት አድርጓል፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ወደርሱ የምታይን ነፍስ፣ እርሱን የተጠማችን ልቦና አይተዋትም፡፡
በነነዌ ሰዎች ታሪክ የታየው ሌላው የእግዚአብሔር ኃይል በፍጥረቱ ላይ ያለው ሥልጣን ነው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ፀሐይ፣ ማዕበል፣ ትል፣ ዛፍ፣ አሳ አንበሪ. . . / የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለምንም ተቃውሞ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ታላቅ ስጦታ 'ነፃነትን' እናደንቃለን፡፡ ፍጥረታት የሚታዘዙለት ኃይል እግዚአብሔር በነፃነት የፈጠረው የሰው ልጅ ፈቃዱን ሲጥስ ይመለስ ዘንድ በሚታዘዙት ፍጥረታት፣ በነቢያት. . . ይናገራል እንጂ ልቦናን በኃይሉ ቀይሮ እንደፈቃዱ እንዲኖር አያደርግም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መቀየር የፈለገን ልብ መቀየር የሚችል የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ፍጥረታቱን በማዘዝ አሳይቷል፡፡
ከዚህ ታሪክ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው በንስሐ የምንኖር ከሆነ ወደዚህ ሕይወት እንደርስ ዘንድ እግዚአብሔር የታገሰባቸውን ያለፉትን የኃጢአት ዘመናት አስተውለን የእግዚአብሔርን የትዕግሥቱን ብርታት በሕይወታችን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ስለ እግዚአብሔር ታጋሽነት ሰዎች ሊነግሩን አያስፈልግም፤ በሕይወታችን አይተነዋልና፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ የሠራውን የፍቅሩን ብርታትም እናውቃለን፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ምድር ላይ ከቢሊዮኖች መካከል አንድ ብንሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በንስሐ መመለሳችን ሁሌ በእግዚአብሔር ሕሊና ውስጥ ሲታሰብ የኖረ፣ በሰማያት ካሉ ቅዱሳን ይልቅ የአንድ ኃጢአተኛ መመለስ ለሰማያትና ለእግዚአብሔር ደስታ የሚሰጥ መሆኑን ስናውቅ በርግጥም እግዚአብሔር እንዴት ሰውን ወዳጅ ነው? ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል የምትወደድ ናት? እንላለን፡፡
ከዚህ ሌላ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ሁሉን የማድረግ ሥልጣን በመታዘዝ እንዳሳዩ ሁሉ በንስሐ የተመለሰ ኃጢአተኛም የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት የሚታይበት ይሆናል፡፡ በኃጢአት የኖረን፣ አያሌ ዘመናትን በዲያብሎስ ምክር በጠማማ መንገድ የኖረን ልቦና መቀየር ከኃያሉ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ኃጢአተኛን 'ቅዱስ' ማድረግ የእግዚአብሔር የብቻው የኃያልነቱ ውጤት ነውና፡፡ ለዚህ ነው 'ተነሳሕያን' ሰማዕታት ናቸው የሚባለው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በሕይወታቸው ይመሰክራሉና፡፡ ጥንታውያን ክርስቲያኖች በደማቸው የእግዚአብሔርን ክብር መስክረው ከሆነ ለዚህ ትውልድ ደግሞ «የንስሐ» ሰማዕትነት ቀርቶለታል፡፡
በአጠቃላይ ከነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለንስሐ ብዙ እንማራለን፡፡ ለዚህም ነው ከብዙ የንስሐ ታሪኮች መርጣ ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ክብር የምታስበው፡፡ ለዚህም ነው ለታላቁ የንስሐ ወቅት ለዐቢይ ጾም ማዘጋጃ መግቢያ ያደረገችው፡፡ እኛም ከዚህ ታሪክ ተምረን፣ የተማረነውንም በንስሐ ወቅታችን /በአሁኑ ጾም/ በተግባር ልናውለው ይገባል፡፡ ለዚህም የተነሳሕያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን፡፡

በዲ/ን በረከት አዝመራው

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
source: http://www.eotc-mkidusan.org/

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl


http://www.youtube.com/watch?v=9DG_UOLUNk0&list=PL8EZ6DqhsFd7BITpIhlLo0oQgdZOVp7eN

የበርሃው መልአክ አባ ጳውሊ


የካቲት 2 በዚህች ቀን በግብጽ በርሃ ታላቅ አምድ ወደቀ፤ ይህም የባህታውያን ሁሉ አለቃቸው የሆነ አባ ጳውሊ ነው። ስርዓተ ብሕትውና በጳውሊ ስርዓተ ምንኩስና በእንጦኒ ተጀምሯል ይላል፤ ጳውሊ አባቱ ባለጸጋ ነበር ሲሞት ለታላቅ ወንድሙ በጴጥሮስ እጅ አድርጎ ኃላ አካለ መጠን ሲያደርስ ከፍለህ ስጠው ብሎት ተናዞ አረፈ፤ አባ ጳውሊ አካለ መጠን ሲደርስ “ ደረስሁ ልጅ ፈላሁ ጠጅ ” የአባቴን ገንዘብ ከፍለህ ስጠኝ አለው አይሆንም አልሰጥህም አለው ምነው ቢለው ልጅ ነህ ታጠፋዋለህ ብዬ ነው ይለዋል አላጠፋውም ስጠኝ ይለዋል ግድማ ካልኸኝ ብሎ ብዙውን አስቀርቶ ጥቂቱን፤ መልካሙን አስቀርቶ ተራ ተራውን ሰጠው አባ ጳውሊ በዚህ ተበሳጭቶ ዳኛ ጋር ሄደ በመንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት አየ አባቴ ባለጸጋ ነበር ሞተ ይሄም ባለጸጋ ነበር ሞተ እኔስ ነገ እሞት የለምን ብሎ ወደ ወንድሙ ተመልሶ ወንድሜ ገንዘቡ ላንተ ይሁን ትቼልሃለው ብሎ ከቤት ወጠ፤ መጀመሪያ ለ 3 ቀን ከመቃብር ቤት ገብቶ ጸለየ በ3ኛው ቀን ከሰማይ ግማሽ ህብስት ወረደለት፤ ገረመው፤ ፈጽሞ ሳይለዩ እንዲህ ከሆነማ ፈጽሞ ቢለዩማ እንደምን ያለ ተአምር በተደረገ ብሎ አናብስት አናምርት አካይስት አቃርብት ካሉበት ነቃዐ ማይ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት ድሩክ ለተአቅቦ ይለዋል ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በርሃ ገባ፤ የሰው ፊት ሳያይ ለ 80 ዓመት በተጋድሎ ኖሯል። ምግቡን ግማሽ ህብስት በየቀኑ የሚያመጣለት ቁራ ነበር። የእረፍቱ ቀኑ ሲደርስ ከአባ እንጦንስ ጋር በእግዚያብሔር ፈቃድ ተገናኝተው ብዙ ነገር ተጨዋወቱ በተለይም በኃለኛው ዘመን ስለሚነሱት መነኮሳትና፤ ግብጽ በሙስሊሞች እንደምትወረር ብዙ ሚስጢር አወሩ ብዙ ትንቢትም ተናገሩ፤ ይህንንም በጥቂቱ ጥር 22 ቀን ጽፈነዋል። ከዚህ በኃላ አባ ጳውሊ አስኬማ መልአክ አምጣሊኝ ብሎ ይልከዋል፤ አባ እንጦስ ወደ ገዳሙ ሄደ የ 2 ቀን ጎዳና ነው ሲመለስ በርሃው ላይ ሰማያውያን መልአክ ሰፍረውበት ሲዘምሩ ሲያመሰግኑ አየ፤ ልብን የሚመስጥ የእጣን መዓዛም አሸተተ፤ ምንድር ነው ? ብሎ አንዱን መልአክ ይጠይቀዋል አባ ጳውሊ ሞቶ ነፍሱን እያሳረግን ነው ይለዋል ይሄን አስኬማ አምጣሊኝ ብሎኝ ነበር ምን ላድርገው ? ይለዋል፤ ጸሎት አድርሰህ አድርግለት፤ ደግሞም መቃብሩን የሚቆፍሩ አንበሶች ይመጣሉ ቦታውን ለክተህ ስጣቸው አለው፤ ወደ ገዳሙ ሲገባ እጁን መስቀልያ እንደዘረጋ ሞቶ አገኘው የሚጸልይ እንጂ የሞተ አይመስልም ነበር አስኬማውን አድርጎለት ሲያበቃ ከራስጌው ቆሞ ኤልያስ ልበልህ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ልበልህ እያለ አለቀሰለት፤ ሁለት አንበሶች መቃብሩን ቆፈሩለት ገንዞ ቀበረው። 80 ዘመን ሙሉ ለብሶት የኖረው የሰሌን ልብስ ነበረችው ወስዶ ለሊቀ ጳጳሱ ለአባ አትናቴዎስ ሰጠው፤ በዚህች ልብስ አባ አትናቴዎስ ብዙ ተአምራትን ሰረቶበታል ይልቁንም ሙት አስነስቶበታል። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባ ጳውሊ በረከት ያሳትፈን። በነገራችን ላይ የዚህ አባት ገድሉ በስፋት ከመጻፉ ባሻገር ግብጻውያን ፊልም ሰርተውለታል ይህን ፊልም ማህበረ ቅዱሳን ጥሩ አድርገው ወደ አማርኛ ተርጉመውታል። የበረታ ገድሉን ያንብብ የደከመው ፊልሙን ይመልከት።

ስእሉ - አባ እንጦንስ አባ ጳውሊን ሲቀብር

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Thursday, February 6, 2014

ጥር 29

በዚህች ቀን የከበረች ቅድስት አክሳኒ አረፈች። ከሮም ከነገስታት ወገን ነች ወላጆቿ በሀብት በዘመድ የከበሩ ነበሩ፤ ከእርሷ ሌላ ግን ልጅ አልነበራቸውም፤ይህች ቅድስት በልጅነቷ የምትጋደል ሆነች በቀን በሌሊት ትጾማለች ትጸልያለች፤ወደ ደናግል ገዳም እየሄደችም ታገለግላቸው ነበር፤ የአባቷን ቤት ምግብ ትታ የመነኮሳይያቱን ደረቅ ምግብ ትመገብ ነበር፤ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ወላጆቿ ሊድሯት አሰቡ የወርቅ የብር ልብሶች፤ ጌጠችና ሽልማቶችን አዘጋጁላት፤ እርሷ ግን ወደ እናቷ ቀርባ “እማዬ ከደናግሉ ገዳም ሄጄ ተባርኬ ልመለስ እሻለሁ” አለቻት እናቷም “ቶሎ ተመለሺ ልጄ” ብላ ከሁለት አገልጋዮቿ ጋር ሰደደቻት፤ቅድ...ስት አክሳኒ አልተመለሰችም በመርከብ ተሳፍራ መጀመሪያ ወደ ደሴተ ቆጵሮስ ከዚያም ወደ እስክንድርያ ሄደች በመንገድ ላይ ሳለች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በራእይ ተገለጸላት የምትሰራውን ሁሉ ነገራት፤ እርሷም ወደ ሊቀ ጳጳሱ ቴዎፍሎስ ገባች ጸጉሯን ላጭቶ አመነኮሳት፤ ከአባቷ ቤት ይዛው ባመጣችው ወርቅ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተክርስቲያን አሳነጸችበት፤ ምንም ምን ሳትይዝ ከደናግል ገዳም ገባች፤ ከጥሬ ባቄላ በቀር እሳት የነካውን ምግብ አልተመገበችም ማቅ ለብሳ አመድ ነስንሳ በተጋድሎ ኖረች፤በዛሬዋ ቀንም በክብር አረፈች፤ በዚህ በእረፍቷ ቀን ታላቅ የብርሃን መስቀል ስጋዋ ባረፈበት ቦታ ላይ ታየ በዙሪያውም የሚያበሩ ከዋክብትና የክብር አክሊላት ነበሩ መነኮሳቱ ምን ድንቅ ነገር ነው ብለው ሲቀርቡ መሞቷን ተረዱ ገንዘው እስኪቀብሯት ድረስ መስቀሉ ያበራ ነበር ከዚያ በኃላ ተሰውሯል። “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። መዝ 84፤10 በረከቷ ይደርብን።

LIKE OUR PAGE >>>

ጥር 28

በዚህች ቀን የማኀው ልጅ ዮሴፍ አረፈ። የዚህ ጻድቅ ወላጆቹ ሰቃልያነ ክርስቶስ አይሁዳዊ ናቸው። በልጅነቱ አባቱን ተደብቆ ከሰፈሩ ልጆች ሀጻናት ጋር የቤተክርስቲያንን መጽሐፍት አጠና ቤተክርስቲያንም እየሄደ ይቆርብ ነበር። አባቱ ይህን በሰማ ጊዜ ተቆጣ እጅና እግሩን አስሮ የእሳት ጉድጓድ ውስጥ ወረወረው የእቶኑንም በር ዘጋበት ''አባትና እናቴ ተዉኝ እግዚያብሔር ግን ተቀበለኝ” አይደል ያለው ዳዊት መዝ 27፤10። እናቱ ልጇን በጣችው ጊዜ አለቀሰች መንደሩ ሁሉ ተሸበረ፤ ከሰባት ቀን በኃላ ወደ እሳት እንደተጨመረ ተሰማ እያለቀሱ ወደ ጉድጓዱ መጡ የዮሴፍን ድምጽ ከውስጥ ሰሙት “ወንድሞቼ አታልቅሱ በ...እመቤታችን እርዳታ በህይወት አለው አላቸው፤ ሊቀ ጳጳሱ ተጠራ ካህናት መስቀል ጥና ይዘው መጡ ጸሎት አድርሰው ከጉድጓድ አወጡት፤ ከራሱ ጸጉር አንዲቷ እንኳን አልተቃጠለችም ዳን 3 ፤ 25 አባቱ ይህን ተአምር ባየ ጊዜ ሊቀ ጳጳሱ እግር ስር ወድቆ አለቀሰ በክርስቶስም አምኖ ተጠመቀ። ዮሴፍ ግን ወደ ገዳም ገባ ለ 28 ዓመት በተጋድሎ ኖረ በየሰባት ቀኑ አንዴ ነበር የሚቀምሰው፤የእረፍት ቀኑ ሲደርስ የእመቤታችን ስዕል ጋር ቆሞ ረጅም ጸሎት አደረገ፤ እመቤታችን ተገልጻ ልጄ ዮሴፍ ከ 3 ቀን በኃላ በ 3 ሰዓት ወደ እኔ እወስድሃለው አለችው በዚያው ባለችው ቀንና ሰዓት በክብር አረፈ ይህም ጥር 28 ነው። ልመናዋ ክብሯ የልጇ የወዳጇ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ከዮሴፍም በረከት ያሳትፈን። ይህ ታሪክ ስንክሳር ላይና ታምረ ማርያም ላይ ይገኛል። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን 5 ነገስታት ከአገር አገር እየተቀባበሉ መከራ ያጸኑበት የታላቁ ሰማዕት የቀሌምንጦስ የእርፍት ቀኑ ነው በረከቱ ይደርብን።
LIKE OUR PAGE >>>

Monday, February 3, 2014

ጥር 25

ጥር 25 በዚህች ቀን በገድል የተጸመደ የከበረ ጴጥሮስ አረፈ። ይህ አባት አስቀድሞ ቀራጭ ነበር ርህራሄ የሌለው ጨቃኝ ልቡ የደነደነ ኃጢያተኛ፤ ይህን ጭካኔውን አይተው "እኩይ ዘአልቦ ምህረት" የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለት ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን እንዲህ ሆነ አንድ ደሃ ምስኪን ቤቱ በራፍ ቆሞ በእንተ ስማ ለማርያም ብሎ ምጽዋት ይለምነዋል ደሃው ከፊቱ ቶሎ እንዲሄድለት እንጀራ ጠቅልሎ ይወረውርለታል፤ ምስኪኑም ተቀብሎ ወደ ማደሪያው ሄደ። በዚያች ሌሊት ተኝቶ ሳለ በህልሙ ነፍሱ ወደ ሰማይ ሄዳ ለፍርድ ቆማ ያያል በግራ በኩል ስይጣናት በቀኝ በኩል ነጫጭ የለበሱ መልአክት ቆመዋል በመካከል ሚዛን አ...ለ ሚዛኑ በግራ በኩል አዘንብሏል በቀኝ በኩል በዶ ነው፤ " ምን ይሻላል ሚዛኑ እኮ ባዶ ነው" አሉ መልአክት ከመካከላቸው አንዱ መልአክ ተነስቶ ይህቺ አንድ እንጀራ አለች እርሷን ላስቀምጣት አላቸው፤ በዚህ ሁሉ ኃጢያቶች ይህቺ ብቻ እንጀራ ምን ትሰራለች አሉት፤ ማቴ 25 ፤ 35 በዚህን ጊዜ ደንግጦ ከእንቅልፉ ነቃ አልዋለም አላደረም ሀብቱን ንብረቱ፤ ቤቱን ጥሪቱን ሁሉ ሸጦ ለድሆች ሰጠ በዚህም አላበቃም ራሱን በባርነት ሸጦ ገንዘቡን ለድሆች መጸወተ፤ በዙዎች ሲያመሰግኑት ሲያደንቁት ውዳሴ ከንቱ ፈርቶ በገዳመ አስቄጥስ ከአባ መቃርስ ገዳም ገብቶ መነኮሰ በዚያም ለብዙ ዓመት በተጋድሎ ኖሮ በዛሬዋ ዕለት በክብር አረፈ። ኃጢያተኛ ተመልሶ በህይወት እንዲኖር እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚያብሔር ይመስገን፤ እኛንም ከአባ ጴጥሮስ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl