Monday, April 12, 2021

ሚያዝያ 5

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

ሚያዝያ 5-ጌታን በኪሩቤል ላይ እንዳለ በራእይ ያየውና ስለእመቤታችንም ዘላለማዊ ደንግልና ትንቢት የተናገረው ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሕዝቅኤል በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ 

+ የደብረ ዓሣው ታላቁ አባት አባ ዮሐኒ ልደታቸው ነው፡፡

+  የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ አካሏ የሆነ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ልደቱ ነው፡፡

+ አፍላሚ፣ ታዖድራ፣ ዋስለዲስ እና መነኩሴው አርሳኒ መታሰቢያ በዓላቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል፡- ይኽም ቅዱስ ነቢይ ሕዝቅኤል ካህንም ነቢይም ሆኖ ሲያገለግል ንጉሥ ናቡከደነጾር የእስራኤልን ልጆችን በማረካቸው ጊዜ እርሱም ተማርኮ ወደ ባቢሎን ሔደ፡፡ በባቢሎን አገርም ሳለ ትንቢትን የሚናገር ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከክብርት እመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ስለመወለዱ እርሷም አምላክን ከወለደች በኋላ ለዘላለም በድንግልና ጸንታ እንደምትኖር ትንቢት ተናገረ፡፡ ‹‹እኔ ወደ ምሥራቅ ስመለከት የተዘጋች ደጅ አየሁ፣ ይህቺ በር ተዘግታ ትኖራለች አትከፈትም፣ የሚገባባት የለም፣ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደተዘጋች ይገባባታልና ከእርሱ በቀር የሚገባም የሚወጣም የለም አለኝ›› በማለት ተናገረ፡፡

የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልናዋን መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ የተገለጸለት ድንቅ ምስጢር ሲገልጽ "ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር፤ እግዚአብሔርም ይኽ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፤ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" በማለት የዘላለማዊ ድንግልናዋን ነገር ተናግራል (ሕዝ ፵፬፥፩-)፡፡ ይኸውም መቅደስ የቅድስት ድንግል ማርያም፤ በር የድንግልናዋ፤ መቈለፊያው የማኅተመ ድንግልናዋ ምሳሌ፤ አምላክ ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት ሲወጣ ማየቱ እንበለ ዘርዕ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን፤ "አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" ብሎ መናገሩ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀንዋ የተሸከመቺው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ማኅተመ ድንግልናዋ የማይለወጥ ዘላለማዊት ድንግል መኾኗን ሲገልጽለት ነው፡፡ ለነቢዩ ሕዝቅኤል የተገለጸለትን ይኽነን አስደናቂ ምስጢር ሊቁ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ዘእንዚናዙ ሲተረጒም "ከመ ኆኅት ዘርእየ ሕዝቅኤል ነቢይ ዘኢቦአ ውስቴታ ብእሲ ዘእንበለ አምላከ እስራኤል ቦአ ውስቴታ ወወጽአ እንዘ ኢይትረኀው ኆኅት ኢታስተማስሉኬ አብዳን ፅንሳ ለእግዝእትነ ማርያም ወወሊዶታ ከመ ኲሎን አንስት ሐሰ ላቲ ለእግዝእትነ ማርያም አላ ፀንሰቶ ለቃለ እግዚአብሔር ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ ወወለደቶ ዘእንበለ ፃዕር ወሕማም ወኢያእመረት ወኢተዐውቃ ፍጹመ ሕማመ ወሊድ ወበእንተዝ ፅንሳ ይትነከር ወኀይለ ዕበየ ወሊዶታ ኢይትነገር ወከመዝ ወለደት ዘኢይረክቦ መኑሂ ክዋኔሁ ወኢተነሥተ ማኅተመ ድንግልናሃ" (ከእስራኤል ፈጣሪ በቀር ሰው እንዳልገባበት ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዳያት ደጃፍ ማኅተመ ድንግልዋ ሳይለወጥ በኅቱም ድንግልናዋ ተፀንሶ ተወለደ፤ እናንት አላዋቆች የእመቤታችን የማርያምን ፅንሷንና መውለዷን እንደ ሌሎች ሴቶች ኹሉ አታስመስሉ፤ ለእመቤታችን ለማርያም በፅንስና በወሊድ በሌሎች ሴቶች መመሰል አይገባትም፤ የእግዚአብሔር ቃልን ያለወንድ ዘር ፀነሰቺው፤ ያለ ጭንቅና ያለምጥም ወለደቺው እንጂ፤ በመውለድ ጊዜ የሚኾን ምጥ ፈጽሞ አላገኛትም፤ ስለዚኽ መፅነሷ በጣም ይደነቃል፤ የመውለዷ ምስጢር ኀይልም አይመረመርም፤ ማንም ማን ባሕርዩን የማያውቀው ርሱን ወለደችው፤ ማኅተመ ድንግልናዋም አልተለወጠም) በማለት የወላዲተ አምላክ ምሳሌ ስለኾነቺው ነቢዩ ሕዝቅኤል ስላያት የተዘጋች ደጃፍ በስፋትና በጥልቀት አስተምሯል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ እንዚራ የተባለው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት የረቡዕ ውዳሴ ማርያም መጽሐፉ ላይ "ሕዝቅኤል ነቢይ ኮነ ስምዐ በእንቲአሃ ወይቤ ርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦአ ዘእንበለ እግዚአ ኀያላን ቦአ ውስቴታ ወወፅአ" (ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለርሷ መሰከረ ድንቅ በኾነ ታላቅ ቊልፍ የተዘጋች ደጅ በምሥራቅ አየኊ አለ፤ ከኀያላን ጌታ በቀር ወደርሷ ገብቶ የወጣ የለም) "ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ እንተ ወለደት ለነ መድኅነ እምድኅረ ወለደት ኪያሁ ነበረት በድንግልና ከመ ትካት" (ደጃፍም የተባለች መድኀኒታችንን የወለደች ድንግል ናት፤ ርሱን ከወለደች በኋላ እንደቀድሞው በድንግልና ኖራለች) በማለት አምላክን ከመውለዷ በፊት ድንግል፤ ከወለደችውም በኋላ ድንግል መኾኗ ነቢዩ ሕዝቅኤል ባያት ራእይ አስቀድሞ የተገለጸ መኾኑን መስክሯል፡፡ ይኽ የእመቤታችን ጣዕመ ውዳሴዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም በድጋሚ በድርሳኑ ላይ "Ezekiel, born in the captivity... " (በምርኮ የተወለደው ሕዝቅኤል የዳዊት ሴት ልጅ የኾነችውን ድንግል በትንቢት ዐይን አይቶ ነበር፤ እንዲኹም ከእግዚአብሔር በተላከው የርሱ ራእይ ውስጥ የድንግልናዋን አምሳል ገለጸ፤ በከለዳውያን ምድር ትንቢት የማርያምን አምሳል አሳየ፤ ርሷንም በነቢያት መጻሕፍት አስቀመጣት፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም የርሷን ታሪክ አስጠበቀ፤ ስለዚኽም ማንም ሰው ይኽነን በማንበብ ሊረዳ ይችላልና፤ በሩ በጥብቅ ተዘግቶ እንደሚኖር "እግዚአብሔር ገብቶታል ተዘግቶ ይኖራል" በማለት ጌታ ለነቢዩ በካህናት ጉባኤ መኻከል ገልጾለታልና) ሲል ጌታ አስቀድሞ ስለ እናቱ ዘላለማዊ ድንግልና በሕዝቅኤል ዐድሮ ማናገሩን ገልጾታል፡፡

 

ዳግመኛም ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል ስለ ክርስትና ጥምቀት ትንቢት ሲናገር ‹‹በንጹሕ ውኃ እረጫችኋለሁ ከኃጢአታችሁም ከእርኩሰታችሁም ሁሉ ትነጻላችሁ፡፡ አዲስ ልብስ እሰጣችኋለሁ፣ አዲስ ዕውቀትንም አሳድርባችኋለሁ፡፡ ድንቁርና ያለበትንም ልብ ከሰውነታችሁ አርቄ ዕውቀት ልብ እሰጣችኋለሁ›› አለ፡፡ የጥምቀት ልጆችም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚሆኑ ተናገረ፡፡

ካህናቱም ሕዝቡን ማስተማራቸውን ስለተው ገሥጾዋቸዋል፡፡ ‹‹…ካላስተማራችኋቸውና ካላነቃችኋቸው እግዚአብሔር የሰዎቹን ነፍስ ከእናንተ ይፈልጋል›› እያለ ካህናቱን ገሥጾዋቸዋል፡፡ ዳግመኛም ነቢዩ ነፍስ በዕለተ ትንሣኤ ከሥጋ ጋር ተዋሕዳ ለፍርድ እንደምትቀርብ ትንቢት ተናገረ፡፡ ትንቢቶቹም ብዙ ናቸው፡፡

እግዚአብሔርም በነቢዩ በቅዱስ ሕዝቅኤል እጆች ብዙ አስገራሚ ተአምራትን አድርጓል፡፡ የእስራኤልም ልጆች በባቢሎን ሳሉ ጣዖትን ባመለኩ ጊዜ ገሥጾዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አለቆቻቸው በነቢዩ ላይ በክፋት ተነሥተውበት በግፍ ገድለውታል፡፡ የትንቢቱም ዘመን 20 ዓመት ነው፡፡

የነቢዩ የቅዱስ ሕዝቅኤል ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን! 

+ + + + +

ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ አካሏ የሆነ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ልደቱ ነው፡፡ ሙሉ ታሪኩን በዓመታዊ የዕረፍት በዓሉ ዕለት ግንቦት 11 ቀን እናየዋለን፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!

 

+ + + + + 

የደብረ ዓሣው ታላቁ አባት አባ ዮሐኒ፡-  መጽሐፍ አባታቸውን ዘስዩመ ተንቤን እሁሁ ይላቸዋል፡፡ እናታቸው ደግሞ ዓመተ መንፈስ ቅዱስ የሚባሉ ደገኛ ምግብራቸው ያማሩ ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ አቡነ አሞኒ የካቲት 5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆቻቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንደጢስ በነው ጠፍተዋል፡፡ አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው፡፡

 

አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖላቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው፡፡ በደመና ተጭነው ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ እብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል፡፡ አባ ዮሐኒን ያሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡ መነሻ ታሪኩም እንዲህ ነው፡-

 

የተንቤን አውራጃ ገዥ የነበረው ሰው በዘመኑ ዐፄ ካሌብ የነበሩበት ዘመን ነበርና አብሯቸው ወደ ምድረ ኖባ ሄደው ሰባት ዓመታትን የፈጀ የጦር ዘመቻ ክርስያኖችን በሚያሠቃዩ ነገሥታት ላይ አዳሄዱ፡፡ የተንቤኑ አውራጃ ገዥም ወደ ዘመቻው ከሄደ ቆይቶ ነበርና ታናሽ ወንድሙ የገዥውን ሚስት ‹‹ወንድሜ የቀረው ሞቶ ነው እንደ ኦሪቱ ሕግ እኔው ላግበሽና ልጆቹን ላሳድግ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ባሌ ቢሞት ይነገረኝ ነበረዘመቻ የሄደው ሁሉ አልተመሰም›› ብላ እምቢ ብትለው በግድ ተገናኛት፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ዮሐኒ ተፀነሱ፡፡ በሚያዝያ 5 ቀንም ተወለዱ፡፡

 

ከዘጠኝ ወር በኋላ ማሏ ከዘመቻ መጣና ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ የአካባቢውም ሰው ወጥቶ በክብር ሲቀበለው ሚስቱ ግን ምጥ ተይዛ ታማ ስለነበር ወጥታ አልተቀበለችውም፡፡ ‹‹የት ሄደች? ምንስ ሆነች?›› ብሎ ሲጠይቅ ልጅ አይደብቅምና አንድ ሕፃን ‹‹አርግዛ ልትወልድ በምጥ ላይ ትገኛለች›› አለው፡፡ የአውራጃውም ገዥ ያለችበት ድረስ ሄዶ ቢያያት ያማረ ወንድ ልጅ ታቅፋ አገኛት፡፡ ከዚህም በኋላ ከቤቱ ምሰሶ ጋር ጥፍንግ አድርግ አስሮ እየገረፋትና እያስጨነቃት ከማን እንዳረገዘች ጠየቃት፡፡ እርሷም የወንድሙን ምሥጢር ለመጠበቅና ወንድማማቾቹን ላለማጣላት ሥቃዩን ታግሳ ዝም አለች፡፡ በዚህ ቅጽበት የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤል 40 ዓመት ሙሉ ዘግተው በበረሃ ለሚኖሩት ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸው እንደ አውሎ ነፋስ አምዘግዝጎ ወስዶ አውራጃ አገረ ገዥው ቤት አደረሳቸው፡፡

 

እንደደረሱ ዓመተ ማርያም በጽኑ ድብደባና ግርፋት እየተሠቃየች እያለ አባ አሞኒ የጸጉራቸውን አጽፍ ለብሰው ራቁታቸውን ደጇ ላይ ቆመው አየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ለባሏ ‹‹ያውና ከዚህ መነኩሴ ነው የወለድኩት›› አለቸው፡፡ አተንቤቱ አውራጃ አገረ ገዥውም አባ አሞኒን ይዞ ጽኑውን ግርፋት በወታደሮቹ አስገረፋቸው፡፡ በመቀጠልም ገና የእናቱን ወተት እንኳን ያልቀመሰውን ጨቅላ ሕፃን አንሥቶ ‹‹እንካ ልጅህን ይዘህ ጥፋ ከዚህ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡ አባ አሞኒም በዚህ ጊዜ ‹‹ ሀበኒ ሀበኒ›› አሉ፡፡ በትግርኛ እሽ ስጠኝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ሕፃኑ በኋላ ላይ ‹‹አባ ዮሐኒ›› የተባሉት፡፡ አባ አሞኒም ሕፃኑን ተረክበው ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ ሥር ሄደው ልጁን ከወይራ ዛፍ ሥር አስተኝተው ‹‹አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ኃጢአቴን ተመራምረህ ይህንን ሕፃን የሰጠኸኝ አላጠባው ጡት የለኝ አላበላው እህል የለኝ›› ብለው የጨቅላው ሕፃን ነገር እጅግ ቢያስጨንቃቸው ምርር ብለው አለቀሱ፡፡ ጸሎታቸውንም እንደጨረሱ ተራራውን በመስቀል ምልክት ቢባርኩት በተራራው መሐል ላይ እንደመደብ ያለ አልጋ በተአምራት ተሠርቶ አገኙት፡፡ ሕፃኑንም ከዚያ አስተኝተው ድጋሚ ጸሎት ሲጀምሩ ቶራ (ሰሳ) መጥታ እግርና እግሯን አንፈራጣ ሕፃኑን አጠባችውና ሄደች፡፡

 

አባ አሞኒም በዚህ ደስ ተሰኝተው ሕፃኑን ‹‹የምግብህ ነገር ከተያዘ ግዴለም›› ብለው ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ አድረው መለስ ቢሉ ዳግመኛም ሕፃኑን የታዘዘ ንስር አሞራ በክንፎቹ ጋርዶ አልብሶትና አቅፎት እንዳደረ ተመለከቱ፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ተኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ቀን ቀን ቶራዋ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራው አልብሶት እያደረ ሕፃኑ ሦስት ዓመት ሆነው፡፡ አባ አሞኒም ከሰባት ዓመቱ ጀምረው እስከ 12 ዓመቱ ድረስ ፊደል፣ ንባብ ከነትርጓሜው፣ ብሉይንና ሐዲስን፣ ምግባር ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስያንን ሁሉ አስተማሩት፡፡

 

አባ አሞኒ ልጃቸው አድጎ 12 ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዓሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን ‹‹አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድናቸው? እንደእኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?›› አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም ‹‹አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ›› አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው ‹‹በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?›› ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡

ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡

 

አባ ዮሐኒ 20 ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ 40 በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና ‹‹አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ብሎሃል›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው ‹‹በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ›› አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው ‹‹አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ›› ብለው ነግረዋቸው በዛሬዋ ዕለት ኅዳር 5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡

 

አባ አሞኒ ካረፉ 12 ዓመት በኋላ የአባ ዮሐኒ ወላጅ እናታቸው የልጇን ነገር ስታጠና ኖራ ነበርና አሁን ባሏም ስለሞተ አባ አሞኒም ስላረፉ ልጇን ልታይ 32 ዓመት በኋላ መጣች፡፡ ቀሚስ ለብሳ ፀጉሯን ተሠርታ በሴትነቷ ልጇ ካለበት ቦታ በመሄድ ማነጋገር እንደማትችል ስላወቀች ፀጉሯን ተላጭታ የወንድ ልብስ ቁምጣ ለብሳ በሁለመናዋ ወንድ መስላ ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ አመራች፡፡ እዚያም እንደደረሰች በቅዱሳን ሥርዓት መሥረት ሦስት ጊዜ ‹‹አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን›› አለች፡፡ ሰይጣን ይህን ስም ሲሰማ 40 ክንድ ይርቃል፡፡ የደብረ ዳሞ መነኮሳት እንደ ሰላምታ መለዋወጫ ይጠቀሙበታል፡፡ አባ ዮሐኒም ይህን ድምጽ ከውጭ በሰሙ ጊዜ ‹‹አንተ ማነህ?›› አሉ፡፡ እርሷም ‹‹ዓመተ መንፈስ ቅዱስ ነኝ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም አንድም ድምፁዋ ወትሮ ከሚያውቁት ድምፅ ስተለየባቸው ደግሞም ትዝ ሲላቸው እነዚያ እንስራ አዝለው ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ሆነው ውኃ ቀድተው ሲሄዱ በመነገድ ያዩአቸው ሴቶች ድምፅ ሆነባቸው፡፡ ደግሞም ‹‹ወልደ እከሌ፣ ክንፈ እከሌ›› ሲባል እንጂ ‹‹ዓመተ፣ ወለተ›› ሲባል ሰምተው አያውቁም ነበርና አባታቸው አባ አሞኒ የነገሯቸው ትዝ አላቸው፡፡ በዚያውም ቅጽበት የሚጽፉባትን ብዕር ጆሮአቸው ላይ እንደሰኩ 500 ሜትር ርዝመት ካለው ትልቅ ተራራ ላይ ራሳቸውን ቁልቁል ወረወሩ፡፡ ነገር ግን መሬት ሳይደርሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአየር ላይ እንዳሉ ተቀበላቸው፡፡ ብዕራቸው ግን መሬት ላይ ወድቃ ሸምበቆ ሆነች፡፡ ወዲያውም አባ ዮሐኒ ክንፍ አውጥተው ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ጎን ለጎን ሆነው በዛሬው ዕለት ኅዳር 5 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ይዟቸው ገባ፡፡

 

ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው?›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን/›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡  

 

ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ደብረ ዓሣ ተመልሶ መጥቶ ለአባ አበይዶ ተገለጠላቸውና አባ ዮሐኒን ብሔረ ሕያዋን እንዳስገባው ነገራቸው፡፡ በመጀመሪያ ሄኖክና ኤልያስ አላስገባ ብለው እንደነበርና በኋላም መልአኩ ራሱ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን ከነገራቸው በኋላ በምስጋና እንደተቀበሉት ለአባ አበይዶ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን እንዲጽፉትና እንዲያስተምሩበት ለአባ አበይዶ አዘዛቸውና ዐረገ፡፡ አባ አበይዶም አባ ዮሐኒ ከገደሉ ተወርውረው ሲወደቁ አንድ ደስ የሚል ወንድ ሲቀበለው አይተው ነበርና አሁን መልአኩ ሲነግራቸው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አባ አበይዶም በመልአኩ በታዘዙት መሠረት የአባ ዮሐኒን ገድል ጻፉት፡፡

የአባ ዮሐኒ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!

 

kegdedlat andebet yetewesede                                                                    

Telegram: https://t.me/tewhahdohaimanotachin  

 LIKE OUR PAGE https://www.facebook.coBm/tewadhdohaimanotachin