ደመራ
መስከረም 16 ቀን እኛ ኢትዮጵያውያን በመስቀል አደባባይ ደመራ እንሠራና ችቦ ይዘን፡
"በወንጌሉ ያመናችሁ
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ"
እያልን በታላቅ ዝማሬ ብዙ መዘምራን ከየቤተ ክርስቲያኑ (ከየአድባራታቸው) ተሰባስበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና ሕዝበ ክርስቲያን በተሰበሰቡበት በዝማሬ ይከበራል፡፡
ደመራ - ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡
የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌሊ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና ሃይማኖት በተመለሰ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡ ደርሳም ስለከበረ መስቀል ጠየቀች (መረመረች) ቦታውንም የሚያስርዳት አላገኘችም፡፡ በኋላ ስሙ ኪራኮስ የሚባል አንድ ሽማግሌ መስቀሉ ወዳለበት ወደ ጐልጐታ ኮረብታ እያሳያት «አባቶቻችን ከነዚህ ተራራዎች ውስጥ በአንዱ አይሁድ መስቀሉን እንደቀበሩት ነግረውናል» አላት፡፡ እሌኒም ለምን ቀበሩት? ብላ ጠየቀች፡፡ የጌታችን መስቀል ሙታን ሲያስነሳ፣ በሽተኛ ሲፈውስ አይተው አይሁድ በክፋትና በቅናት ተነሳስተው ነው የቀበሩት፡፡
ከዚያም የተቀበረበትን ቦታ ክርስቲያኖች እንዳያገኙት ሁሉም አይሁዶች ከየቤታቸው የሚወጣውን ቆሻሻ እንዲጥሉበት ተደረገ፡፡ የጌታችንን መስቀል የቀበሩበትን ቦታ ቆሻሻ መጣያ አደረጉት ያም ቆሻሻ ሲጠራቀም ከሁለት መቶ ዓመት በላይ አልፎት ትልቅ ተራራ ሆነ፡፡ ኪርያኮስም ንግሥት እሌኒን እንዲህ ሲል መከራት «ደመራ አስደምሪ ብዙ እጣን አስጨምረሽበት ወደ ፈጣሪ ብታመለክች የእጣኑ ጢስ መስቀሉ ያለበትን ተራራ ያመልክትሻል፡፡» አላት፡፡ እሌኒም ኪርያኮስ እንደ መከራት በመስከረም 16 ደመራ አስደምራ ብዙ እጣን አስጨምራ ወደ ፈጣሪ ብታመለክት የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ በተቀበረበት ተራራ ላይ አረፈ፡፡ ከዚያም መስከረም 17 ቀን መስቀሉን ለመፈለግ ተራራውን መቆፈር ጀመሩ፡፡
ከስድስት ወር በኋላ በመጋቢት 1ዐ ቀን መስቀሉን አግኝተውታል፡፡ መስቀሉንም አምጥተው በሞቱ ሰዎች ላይ አስቀመጡት ያን ጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ ሌሎች ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም አደረገ ንግሥት እሌኒም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል መሆኑን አውቃ ሰገደችለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡
ከክርስቶስ መስቀል አንዱ ክፍል የሆነው ግማደ መስቀሉ በኢትዮጵያ አለ.. ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ይገኛል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment