Tuesday, February 25, 2014

እንኳን ለዐቢይ ጾም አደረስን !!!





ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17 ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ወይም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡

መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾመው ለአብነት፣ ለማስተማር፣ ለአርዓያ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፣ ከሰው የሥጋ ጠባይ የሚመጣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ድል የተነሱበት ነው፡፡ እኛም ይህን እያሰብን በተለያየ መንገድ የሚመጣብንን ፈተና ለማራቅ ከዚህ ታላቅ ጾም በረከት እንድናገኝ እንጾማለን፡፡ ጸልዮ ጸልዩ፣ ጾሞ ጹሙ ብሎናል፡፡ ማቴ.6-16፡፡ ስለዚህም ትእዛዙን ለማክበር እንጾማለን፡፡

የዚህ ታላቅ ጾም ስያሜዎች፡-

1. ዐቢይ ጾም

ባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል፡፡

2. ጾመ ሁዳዴ

በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡

3. የካሳ ጾም

አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡ በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ካሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ፡፡

4. የድል ጾም

አርዕስተ ኃጣውእ /ማቴ. 4/ ድል የተነሱበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል፡፡

5. የመሸጋገሪያ ጾም

ጌታችን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሊያሸጋግረን የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል፡፡

6. ጾመ አስተምህሮ

ጌታችን የጾመው ለትምህርት ነው፡፡ እርሱ መጾም ያለበት ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ጾም ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2

7. የቀድሶተ ገዳም ጾም

ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል፡፡

8. የመዘጋጃ ጾም

ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡

ዓቢይ ጾም ስምንት ሳምንት ማለትም 55 ቀናት አሉት፡፡ ከእነዚህም ቀናት ውሰጥ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሑዶች ይገኛሉ፡፡ አሥራ አምስት ቀናት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጾሙ የሙሉ ቀናት ጾም አርባ ቀናት ብቻ ናቸዉ፡

የመጀመሪያው ሳምንት «ዘወረደ» ማለት በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ.3ዕ13፡፡ በጾምነቱ ግን ለዐቢይ ጾም መግቢያ ሆኖ ታላቅ ገድልና ድል የተገኘበት ጾመ «ሕርቃል» ተብሎ ይጠራል፡፡ ሕርቃል በ614 ዓ.ም የቢዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበትም ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ ምእመናን «ተዋግተህ አስመልስልን» አሉት፡፡ እርሱም «ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይኽንን የዕድሜ ልክ ጾም ፈርቼ እንጂ ደስ ይለኛል» ሲል መለሰላቸው፡፡ እነርሱም «የአንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ሰባ ሰማኒያ ዘመን ነው፡፡ እኛ ተካፍለን እንጾምልሃለን» ስላሉት ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነዚያ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡ መታሰቢያም እንዲሆን ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገቡት፡፡ የመጀመሪያው ሳምንት ጾሙም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ታሪኩ የመስቀል ፍቅር የተገለጠበት ታሪክ ነው፡፡

መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስፈጽመን






source : http://www.eotc-mkidusan.org/


የካቲት 16


በላዔ ሰብ በአማርኛ ሰው በላ ማለት ነው፤ ትክክለኛ ስሙ ግን ስምዖን ይባላል ቅምር በሚባል አገር የሚኖር እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ እንደ አብርሃም እንግዶችን እየተቀበለ ድሆችን እየመገበ የሚኖር ጻድቅ ነበር፤ ሰይጣን በዚህ ስራው ቀናበት ሊፈትነውም በሦስት አረጋዊ ሽማግሌዎች ስላሴ ነን ብሎ ተገለጠለት ልክ እንደ አብርሃም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ይመጣል እንዳለ፤ እርሱም ሥላሴ መስለውት ተቀበላቸው ተንከባከባቸውም፤ ምግብ አቀረበላቸው ምግብ አንበላም የምንጠይቅህን ግን ትፈጽምልን ዘንድ ቃል ግባልን አሉት ቃል ገባላቸው እንግዲያውስ የምትወደን ከሆነ አንድያ ልጅህን ሰዋልን አሉት፤ መጀመሪያ ደነገጠ ኃላ አብርሃም ልጁን ሊሰዋ አልነበረምን እኔንም ሊፈትኑኝ ይሆናል ብሎ ለማረድ ተዘጋጀ፤ተው የሚለው ድምጽ አልሰማም፤ አረደው አወራረደው ይዞላቸው ቀረበ፤ መጀመሪያ ቅመስልን አሉት ቀመሰው ወዲያው እነዚያ ሰዎች ተሰወሩበት እርሱም አህምሮውን ሳተ ተቅበዘበዘ ከዚያ በኃላ ምግብ አላሰኘውም የሰው ስጋ እንጂ መጀመሪያ ቤተሰቦቹን በላ ከዚያም ጓደኞቹን ጦርና የውኃ መንቀል ይዞ ከቤቱ ወጣ ያገኘውን ሰው እየገደለ ይበላል የበላቸው ሰው ቁጥር 78 ደረሰ፤ በመንገድ ተቀምጦ የሚለምን በደዌ የተመታ አንድ ደሃ አገኘ ሊበላው ወደ እርሱ ተጠጋ ግን ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፤ ደሃውም “ስለ እግዚያብሔር ከያዝከው ውኃ አጠጣኝ” አለው “ዝም በል ደሃ” ብሎት አለፈ፤ “ኸረ በውኃ ጥም ልሞት ነው ስለ ጻድቃን ስለ ቅዱሳን” አለው አሁንም ዝም ብሎት ሄደ ለሦስተኛ ጊዜ “ስለ አዛኝቷ ስለ እምዬ ማርያም” አለው፤ ሰውነቱን አንዳች ነገር ወረረው “አሁን የጠራከውን ስም እስኪ ድገመው ስለ ማን አልከኝ” አለው፤ ስለ አዛኝቷ ስለ እመቤቴ ማርያም አለው፤ ይህቺስ ደግ እንደሆነች በምልጃዋም ከሲኦል እንደምታወጣ ህጻን እያለው እናትና አባቴ ይነግሩኝ ነበር፤ በል እንካ አለው እጁን ዘረጋለት ጥርኝ ውኃ ጠብ አደረገለት ወደ ጉሮሮው አልወረደም የተሰነጠቀ እጁ ውስጥ ገባ እንጂ፤ በለዔ ሰብ ከዚያች ደቂቃ በኃላ አዕምሮው ተመለሰለት እንዲህም አለ “በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቼ ስለ ኃጢያቴ አለቅሳለሁ ስጋዬ ከአጥንቴ እስኪጣበቅ እጾማለሁ ወዮሊኝ ወዮታም አለቢኝ አለ፤ ወደ ዋሻ ገባ ምግብ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ 21 ቀን ኖሮ በርሃብ ሞተ ይላል ተአምረ ማርያም። ጨለማ የለበሱ ሰይጣናት እያስፈራሩ እያስደነገጡ ነፍሱን ወደ ሲኦል ሊወስዷት መጡ፤ እመቤታችን ፈጥና በመካከላቸው ተገኘች፤ ልጄ ወዳጄ ይህችን ነፍስ ማርሊኝ አለችው እናቴ ሆይ 78 ነፍሳትን የበላ እንዴት ይማራል አላት፤ የካቲት 16 ቀን በጎለጎታ የገባህልኝ ቃል ኪዳን አስብ ስምሽን የጠራ መታሰቢያሽን ያደረገን እምርልሻለው ብለኸኝ የለምን አለችው፤ እርሱም እስኪ ይህቺን ነፍስ በሚዛን አስቀምጧት አለ ቢያስቀምጧት ጥርኝ ውኃው መዝኖ ተገኘ፤ ስላቺ ስል ምሬታለው ሰባት ቀን ሲኦልን አስጎብኝታችሁ ወደ ገነት አግቧት አላቸው። ቦታሽ እዚህ ነበር እያሉ ሲኦልን አስጎብኝተው ወደ ገነት አገቧት። ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን። ተአምረ ማርያም

የካቲት 15

በዚህች ቀን የበራክዩ ልጅ ነብዩ ዘካርያስ አረፈ፤ ቁጥሩ ከደቂቀ ነብያት ነው፤ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ዘካ 1210 የወጉትን ያዩታል አለ፤ ዳግመኛም ስለ ሆሳህና እንዲህ አለ "ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤" ዘካ 99 ስለደብረዘይት ዳግም ምጽአትም ተናግሯል ዘካ 145 ይሁዳ ክርስቶስን 30 ብር እንደሚሸጠው ዘካ 1112 ይህ ነብይ ደግሞ ስለ ጾም እንዲህ ሲል ተናግሯል "የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአራ...ተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።" ዘካ 819 ሌሎች ብዙ ትንቢቶችን ተናገረ፤ ትንቢት የሚናገርበት ወራት ሲፈጸም የካቲት 15 በዛሬዋ ቀን አንቀላፋ በአባቶቹ ነብያት መቃብርም ቀበሩት። በረከቱ ይደርብን።
"በአሕዛብም መካከል ብዘራቸው እንኳ በሩቅ አገር ሳሉ ያስቡኛል፥ ከልጆቻቸውም ጋር በሕይወት ይኖራሉ፥ ይመለሱማል።" ዘካ 109 አሜን በስደት ያሉ ኢትዮጰያውያን ወገኖቻችንን ይመልስልን።

የካቲት 13



በዚህች ቀን መልካም ስም አጠራር ጣፋጭ ዜና ያለው 2ኛው አውሳብዮስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ ይህ አባት ሌሊት ሌሊት ከሚስቱ ጋር ባህር ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ አራት ስግደት በየቀኑ ይሰገዳሉ አብዝተው ይጾሙ ይጸልዩም ነበር። የንጉሱ ሚስት በዝሙት በፈተነችው ጊዜ አይሆንም አላት ዘፍ 39 12 ለንጉሱ አስገድዶ ሊደፍረኝ ነበር ስትል ነገረችው እርሱ ተናዶ ጽኑ ስቃይ አጸናበት ቅዱስ ኡራኤል ነጥቆ ወደ ሰማይ አወጣው በዚያም 14 ዓመት ኖረ 2 ቆሮ 122 ዳግመኛ ወደ ምድር ተመልሶ 40 ዓመት ወንጌልን ሰበከ ሰማኒያ አምስት አረማውያንን ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሷል። ይህ አባት በቅድስና ኖሮ በዛሬዋ ዕለት አርፏል በረከቱ ይደርብን።