Thursday, January 30, 2014

ጥር 24

╬╬╬ ጥር 24 የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለሐይማኖት ስባረ አጽማቸው ነው፤ በረከታቸው ይደርብን፡፡ ╬╬╬

የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል፡፡ መዝ 34፣19

ጥር 24 የኢትዮያዊው ጻድቅ ብጹእ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ስባረ አፅማቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በታላቅ ድምቀት አክብራ የምትውልበት ታላቅ ቀን ነው።አባታችን ኢትዮጵያዊው ፃድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለ22 ዓመታት ደብረ ሊባኖስ በሚገኘው ደብረ አሰቦ ዋሻ ውስጥ ሲፀልዩ ከመቆም ብዛትም እግራቸውን አጥተዋል። ለዓመታት ከቆሙበት ሳይቀመጡ ከፊት ከኋላ ከጐን እና ከጐን ምንም ሳይደገፉ በአንድ ቦታ በመወሰን ለ22 ዓመታት ደብረ ሊባኖስ በሚገኘው ደብረ አስቦ ዋሻ ውስጥ ሲፀልዩ ከመቆም ብዛትም እግራቸውን አጥተዋል። ከዚያም ለ7 ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ፀሎታቸውን ቀጠሉ። ስለ ክብራቸውም ከእግዚአብሔር ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። በአጠቃላይ ለ29 ዓመታት በጸሎት ቆይተዋል። 
ዕረፍታቸውም በተወለዱ በ99 ዓመት ሲሆን ቀኑም ነሐሴ 24 ቀን ነው። 
በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው አባታችን በየዓመቱ ነሐሴ 24 ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን ታህሳስ 24 ቀን በዓለ ልደታቸውን ዛሬ ጥር 24 ደግሞ ስባረ አፅማቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች።የአባታችን የፃድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ጸሎታቸው እና አማላጅነታቸው ቤተክርስቲያናችንን አገራችንን ኢትዮጵያን እና እኛን ህዝቦቿን ከፈተና ይጠብቀን ዘንድ በቃልኪዳናቸው ያስቧት አሜን!!!

LIKE OUR PAGE >>>

ጥር 23

"ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁና፤" 1ኛ ጢሞ 1፤ 1 ይህን መልዕክት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ቅዱስ ጢሞቲዎስ የላከለት ነው። ዛሬ ጥር 23 ቀን የዚህ የከበረ ሐዋርያ የጢሞቲዎስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ አገሩ ልስጥራን ፤ አባቱ ኮከብ ቆጣሪ እናቱ አይሁዳዊት ነበሩ በኃላ በቅዱስ ጳውሎስ ስብከት አምነው ተጠምቀዋል ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቲዎስን ባየው ጊዜ ወደደው የእግዚያብሔር ጸጋ በላዩ ላይ ነበርና ይላል ሐዋ 16፤ 1 አስከትሎታል ብዙ አገርም አብሮት ዞሮ አስተምሯል ታላቅ መከራ ብዙ ሐዘን ደርሶበታል በኃላም ብቃቱን አይቶ በኤፌሶን ኤጲስ ቆጶስ አድርጎ ሾሞታል በዚያም ብዙዎችን ወደ ቀናች ኃይማኖት መልሷል በመጨረሻም በዛሬዋ ዕለት በሰማእትነት አርፏል። በረከቱ ይደርብን።


LIKE OUR PAGE >>>

ጥር 22


ጥር 22 የቅዱስ ኡራኤል በዓለ ሲመቱ ነው፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን የመነኮሳት አባት ታላቁ ጻድቅ አባ እንጦንስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ ይህ አባት ወላጆቹ በሀብት የከበሩ ነበሩ እነርሱ ሲሞቱ ንብረቱን በሙሉ ለድሆች መጽውቶ አናምስት አናምርት አካይስት አቃርብት ካሉበት፤ ነቀዐ ማይ ልምላሜ እጽ ከሌለበት ፤ ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በርሃ ገባ በዚያም በተጋድሎ መኖር ጀመረ ሰይጣናት በዘንዶ በጊንጥ እጅግ በሚያስፈሩ አውሬዎች እየተመሰሉ ያስፈራሩት ጀመር “አባቱ አዳም ከገባበት እገባለሁ ብሎ ነው እኮ ከዚህ የመጣው” እያሉ ይስቁበት ይሳለቁበት ነበር እየደበደቡ ስቃይ አጸኑበት እርሱ ግን በትህትና እናንተ ብዙ እኔ አንድ እናንተ ኃያላን እኔ ደካማ እናንተ ረቂቃን እኔ ግዙፍ በአምላኬ ኃይል ካልሆነ እንዴት እችላቹዋለሁ እያለ በትህትና ተዋጋቸው ነገር ግን መከራውን መቋቋም ሲያቅተው በቃ ወደ ከተማ ልመለስ ብሎ አንድ እግሩን ከውስጥ አንድ እግሩን ከውጭ አድርጎ ሲያወጣ ሲያወርድ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የሰሌን ቆብ አድርጎ የሰሌን ልብስ ለብሶ የሰሌን መቋሚያ ይዞ ከበሩ ፊት ለፊት ጸሎት ሲያደርግ አየ የዚህን መልአክ ፍጻሜውን ሳላይማ አልሄድም ብሎ ቆመ መልአኩ መጀመሪያ ለሥላሴ አንድ ስግደት ሰገደ ከዚያም ጸሎት አደረሰ ወንጌል አነበበ በመጨረሻም አንድ አቡነ ዘበሰማያት ብሎ ሦስት ጊዜ ሰገደ እንደዚህ እያደረገ 12 አቡነዘበሰማያትን አድርሶ 36 ጊዜ ሰገደ በእያንዳንዱ ሶስት ሶስት ጊዜ፤ ከዚያም ቁጭ ብሎ የያዘውን ሰሌን መታታት (መስፋት) ጀመረ፤በ 3፤ በ 6፤ በ 9 እና በ 11 ሰዓትም እንደዚሁ እያደረገ አሳየውና እንጦንስ ከሚመጣብህ ከሰይጣን ጾር ለመዳን እኔ እንዳደረግሁት ዘወትር አድርግ ብሎ ስርዓተ ምንኩስናን አስተምሮት ከእርሱ ተሰውሯል፤አባ እንጦንስም መልአኩ እንዳሳየው ጸሎት እያደረገ ሰሌን እየሰፋ በተጋድሎ ኖሯል፤ ከእለታት በአንዱ ቀን ከአባ ጳውሊ ጋር ተገናኝተው መጨዋወት ጀመሩ ይህን ቆብ ማን ሰጠህ ይልዋል ከእግዚያብሔር ነው የተቀበልኩት አለው፤ አባ ጳውሊ አደነቀ “ይልቅስ እስኪ ከኔ በኃላ እንደዚህ ዓይነት ቆብ የሚያደርግ መኖር አለመኖሩን ወደ እግዚያብሔር ጸልይሊኝ ይለዋል፤ አባ ጳውሊ ሲጸልይ ነጫጭ ርግቦችን ያያል ደስ አለው ከአንተ በኃላ ያንተን ፈለግ የሚከተሉ ልጆችህ ይነሳሉ ይለዋል እስኪ እባክህን ደግመህ ጸልይሊኝ ሁሉም የኔ ልጆች ናቸውን ይለዋል ሲጸልይ አንዳንድ ጥቁር ነገር የተቀላቀለባቸውን ያያል ገረመው ሁሉም ጻድቃን አይደሉም ጽድቅና ኃጢያትን የሚቀላቅሉም አሉበት ይለዋል፤ ለሶስተኛ ጊዜ ቢጸልይ ጥቋቁር ቁራዎችን ይመለከታል ድምጹን አሰምቶ ያለቅሳል ምነው ይለዋል በኃለኛው ዘመን የሚነሱት መነኮሳት ሹመት ሽልማት ፈላጊ፤ ገንዘብን የሚወዱ፤ ፍቅር የሌላቸው ትዕቢተኞች ናቸው በፈረስ በበቅሎ ነው የሚሄዱት፤ከመኳንንት ጋር ቁጭ ብለው ኃጢያትን የሚዶልቱ ናቸው አለው እስኪ እባክህን በንስሃ ይጠራቸው እንደሆነ ጠይቅሊኝ ይለዋል ይዚህ መልስ አልመጣለትም ይላል መጽሐፈ መነኮሳት 2ኛው ወይንም ፊሊክስዩስ፤በነገራችን ላይ በፈረስና በብቅሎ ነው የሚሄዱት ያለው ያኔ በ 3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስለሆነ ነው ለዚህ ዘመን ስንመነዝረው ሐመርና ኮብራ መሆኑም አይደል። አባ እንጦንስ የእረፍት ቀኑ ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶለታል ጥር በባተ በ 22ኛው ቀን አርፏል። ከመልአኩ ቅዱስ ኡራኤል ከአባ እንጦንስ በረከታቸውን ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ጥር 21

“ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ”
ጥር 21 በዓለ አስተርእዮ (የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት)

እንኳን ለዚህች ታላቅ በዓሏ አደረሰን፡፡
ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበት ዕለት ነው፡፡
ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ትርጉሙ ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡ በማለት አደነቀ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
... የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሁድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላዕክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁミ አለችው፡፡ በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅስስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ ባባ ይዘወት ወደ ጌሰማኒ ሲስደት አይተው ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለም ብሎ ኑ እናቃጥላት ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፡፡ የታዘዘው መላእክት መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ድኖለታል፡፡ ከዚህ ቦሃላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ በእጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡
አንድም በዓሉ-፡ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነት ተወልዶና ማንነቱ በይፋ ታውቆ በተገለጠበት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር የ“አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል፡፡ አስቀድመው አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ ተበትነው ነበርና በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሁሉም ደመናን ጠቅሰው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መርቶ አመጣቸው እንጂ ለምን እንደመጡ አያውቁም ነበር፡፡ እመቤታችንም ለምን እንደመጡ ጠየቀቻቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ሆይ! የመምጣታችን ምሥጢርማ እኛ አንቺን እንጠይቅ እንጂ አንቺም እኛን ትጠይቃለሽን? ሁላችንም ለምን እንደመጣን አናውቅም፡፡ ለምሳሌ እኔ አስቀድሜ በአንጾክያ ነበርኩኝ አሁን ግን እነሆ እዚህ ነኝ፡፡ ለምን እንደመጣሁኝ ግን አላውቅም” አላት፡፡ እርሷም ሁሉም በአጠገቧ በተሰበሰቡ ጊዜ የሚሆነውን ነገር አስቀድማ ከልጇ ከወዳጇ አውቃ ተዘጋጅታ ነበርና ለምን እንደመጡ (ዕረፍተ ሥጋዋን ለማየት እንደሆነ) ነገረቻቸው፡፡ ሌሊቱንም በሙሉ በጸሎትና በማኅሌት ደግሞም በዝማሬ ሲያመሰግኑ አደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የተወደደችው እናት በረከቷን አሳድራባቸው በሰላም አንቀላፋች፡፡ ነፍሷም በዐብይ ዕልልታና በታላቅ ምስጋና በመላእክት እጅ ወደ አምላኳ ሄደች፡፡ ኋላ ሐዋርያቱ ዮሐንስን ሲያገኙት፡- “እመቤታችን እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ዐርፋለች” አላቸው፡፡ የቀሩት ሐዋርያት “ዮሐንስ ያን ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ አይቶ እኛስ ሳናይ እንዴት እንቀራለን?! አቤቱ ለእኛም ቸርነትህን አድርግልን” ብለው በነሐሴ መባቻ በአንድነት ሆነው ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርብ የአንድ ሳምንት ጾምና ጸሎት ጀመሩ፡፡ በሁለተኛው ሱባዔ ማብቂያ ዕለት ነሐሴ 14 ቀን እሑድ የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ መልአኩ ከገነት አምጥቶ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ልመናቸው ስለ ተፈጸመላቸው ፈጣሪያቸውን በጸሎት አመስግነው በዚያችው ዕለተ እሑድ ቅዱስ ሥጋዋን ወስደው ቀብረውታል፡፡ እርሷም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ማክሰኞ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ- እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘው ይህ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይታ የመነሣቷ እውነታ ነው፡፡ የአዛኚቱ ድንግል አማለጅነትና በረከት አይለየን፡፡ ሁላችንም ባለንበት ይህ ታላቅ በዓሏን እያሰብን ጸልየን የበረከቷ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡ መልካም በዓል !!


LIKE OUR PAGE >>>

ጥር 15

ጥር 15 ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀኑ ጥር 15 ሐሙስ ከሌሊቱ 6 ሰዓት የሶስት ዓመቱ ህጻን ቅዱስ ቂርቆስ በሰይፍ አንገቱ ተቆርጦ በሰማዕትነት አረፈ በበነጋው ዓርብ ጥር 16 ቀን እናቱ እየሉጣም በተመሳሳይ በሰማዕትነት አረፈች። እነዚህ ሰማዕታት ከመሞታቸው በፊት ብዙ መከራ ተቀብለዋል ከአገር አገር ተሰደዋል፤ ከተቀበሉት መከራዎች የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ፈጠኖ ደራሽነቱን አማላጅነቱን ያየንበት ሐምሌ 19 ከእሳት ያዳነበት ቀን አንዱ ነው። በአገራችን ኢትዮጰያ በሰማዕቱ ቂርቆስ ስም በርካታ ገዳማትና አብያተክርስቲያናት አሉ ከነዚህም የጣና ቂርቆስ ገዳም ዋንኛው ነው፤ በዚህ ገዳም ታቦተ ጽዮን ለረጅም ዘመን አርፋበታለች፤ የኦሪት መስዋትም ይሰዋበት ነበር፤ በአዲስ አበባ ለገሃር ባቡር ጣቢያ አካባቢ የሚገኘውን ቤተክርስቲያን የተከሉት ደገኛው ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ናቸው የተከሉበት ምክንያትም አዲስ አበባ ተስቦ በሽታ ገብቶ ህዝቡን እየጨረሰ ነበር፤ ታዲያ ምን ይሻላል ብለው ሽማግሌዎችን ሲያማክሩ፤ ጃንሆይ “ገድለ ቂርቆስ ላይ እንዲህ የሚል ቃል ኪዳን አለ ቤተክርስቲያንህ ባለበት ቦታ ርሃብ ቸነፈር ፈጽሞ አይደርስም ይላል የሰማዕቱን ታቦት ቢያስመጡ ቤቱንም ቢሰሩለት ይህ ሁሉ መከራ ይወገዳል አሏቸው፤ የሽማግሌዎቹን ምክር ሰምተው አሁን ያለውን ቤተክርስቲያኑን አነጹ ታቦቱንም አስገቡ በዚህም በሽታው ወረርሺኙ ቀንሶላቸዋል ይላል፤በዚህ ቤተክርስቲያን እና ታቦተ ባለበት ቤተክርስቲያን ዛሬ ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። ከቅዱስ ቂርቆስ ከእናቱ እየሉጣም በረከታቸውን ያድለን።

LIKE OUR PAGE >>>

ጥር 13 -- ዕረፍቱ ለአቡነ ዘርዓ ብሩክ


እንኳን ለጻድቁ አባታችን አቡነ ዘርዓ ብሩክ የእረፍት በዓል አደረሳችሁ አደረሰን ከጻድቁ አባታችን ረድኤት በረከት ያሳድርብን አሜን !!!

የጻድቁ አባታችን የአቡነ ዘርዓ ብሩክ አባት እና እናት የተባረኩ ከቅዱሳን ወገን የሚሆኑ ነበሩ። የአባታቸው ስምም ቅዱስ ደመ ክርስቶስ ሲባል እናታቸው ደግሞ ቅድስት ማርያም ሞገሳ ትባላለች። ጻድቁ አባታችን ገና በእናታቸው ማህጸን እያሉ ነበር ብዙ ተአምራት የሚያደርጉት እግዚአብሔር መርጧቸዋልና። በኋላም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ8ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በነሐሴ 27 ጻድቁ አባታችን ተወለዱ። በ40ኛ ቀናቸውም ተጠምቀው በካህናት አፍ "ጸጋ ክርስቶስ" ተባሉ ከዛም ቤተሰቦቻቸው በጥሩ እድገት አሳደጉአቸው። 7 አመትም በሞላቸው ግዜ "በልጅነቴ የዚን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ" ብለው ቢጸልዩ ዓይናቸው ታውሯል። 
ቤተሰቦቻቸውም ጠቢቡ ሰሎሞን "የእግዚአብሔር ቃል ነውርን ይሸፍናል" እዳለው ትምህርት ሊያስተምሩአቸው አስተማሪ ጋር ቢወስዱአቸው ታመው ተመልሰዋል የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለምና። ነገር ግን የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ፈጣሪ አምላክ ራሱ ገልጾላቸዋል:: ክህነትን እስከ ጵጵስና እራሱ መድሃኔ ዓለም ክርስቶስ ሰጥቷቸዋል። 12 አመትም በሞላቸው ግዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ አይናቸው በርቶላቸው ታላላቅ ተጋድሎን ማድረግ ጀመሩ።

በእግዚአብሔር ዘንድ ጵጵስና እንደተሾሙ 

የሃጥያት ማሰርያን ያስሩና ይፈቱ ዘንድ ጵጵስናን በሾማቸው ግዜ እግዚአብሔር ያወጣላቸው ሁለተኛ ስም "ዘርዓ ብሩክ" ይባል ነበር። 3ኛውም ስማቸው ደግሞ "ጸጋ እየሱስ" ይባላል:: ጻድቁ አባታችን በዚህ አለም በህይወተ ሥጋ ሳሉ አቡቀለምሲስ እንደሚባል እንደ ዮሃንስ ወልደነጎድጉአድ እግዚአብሔር እሱ ወዳለበት ወደ ሰማይ አውጥቶ በገነት መካከል ያኖራቸው ነበር:: እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጁ ለብጹዕ አባታችን ዘርዓ ብሩክ በጎ ነገር እንዳደረገለትና ያለ ድምጽ የሰማይ ደጆችን አልፎ የእሳት ባህርን ተሻግሮ ፈራሽ በስባሽ ሲሆን እንደ ህያዋን መላእክት በፍጥነት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ከአድማስ እስከ አድማስ ይደርስ ዘንድ 12 ክንፍን ሰጣቸው። መላእክትም ለሌሎች ቅዱሳን ያልተሰጠ ይህንን ስልጣን አይተው ለምድራዊ ሰው ይህ ነገር እንዴት ይቻላል? እያሉ አደነቁ።ከዛም በኋላ ጻድቁ አባታችን ከፈጣሪ ዘንድ የመላእክትን አስኬማ፣ የሾህ አክሊል አምሳያ የሆነውን መንፈሳዊ ቆብን,ሰማያዊ ቅናትን እና የደረት ልብስን(ስጋ ማርያም) ተቀብሎ በጾም እና በጸሎት በልመና እና በስግደት እግዚአብሄርን ሲያገለግል ኖረ። ከዛም በላይ ወንጌልን እጅግ ብዙ በማስተማር ደከመ።

ከኢትዮጵያም አልፎ ግብጽ ድረስ ገባ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሐንስን አገኘውና እርስ በርስ ሰላምታን ተለዋውጠው እጅ ተነሳሱ ከዛም ተመልሶ ወደ ሃገሩ መጣ ከዛም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመላለሰ ወንጌልን አስተማረ እጅግ ስጋን በሚያስጨንቅ ትጋትም የኢትዮጵያን ህዝብ ማርልኝ እያለ እያለቀሰ ይጸልይ ነበር።

አቡነ ዘርዓ ብሩክ "ዓባይ" እና "ግሽ ዓባይ" የሚሉ ስሞች እንዳወጡ 

አንድ ቀን አባታችን የንጉስ ጭፍሮች ሲያሳድዷቸው ግዮን ደረሱ። እንደደረሱባቸው ሲያውቁ ዳዊታቸውንና ለወንጌል ስብከት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 7 መጻሕፍት ሁሉ ለግዮን ወንዝ አደራ ሰጡዋት። ከ5 አመት በኋላ ሲመለሱ " ኦ ግዮን ግሥኢ መፃሕፍትየ -- ግዮን ሆይ መጻሕፍቴን ግሺ መልሺልኝ " (ግሽ ዓባይ -- የሚባልም ከዚህ የተነሳ ነው።) ቢሉአት አንድም የውሃ ጠብታ ሳይኖርባት ዳዊታቸውን ብትመልስላቸው ለደቀ መዝሙራቸው ዘሩፋኤል አሳዩት ሁለቱም የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ። ከዛም በኋላ ግዮንን ባረክዋትና "ይኩን ፈውስ ዓብይ በውስቴትኪ -- በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ" አሉ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ መካኖች ይወልዱ፣ ድዉዮች ይድኑ ጀመር "ወእም አሜሃ ተሰምየት ዓባይ ይእቲ ፈለግ -- ከዛ ጊዜ ጀምሮ ይህች ዓባይ ተብላ ተጠራች።" እስካሁንም በዚሁ ስም የሚጠራው ከዚ በመነሳት ነው:: ከዚህም ሌላ ጻድቁ አባታችን በዚሁ ወንዝ አካባቢ ለ 30 አመት ሲጸልዩ ፈጣሪ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ እጅግ ልዩ የሆነ ቃል ኪዳን ሰቶአቸዋል።

ዕረፍታቸው 

በስተመጨረሻም የሚያርፉበት እለት በደረሰ ሰአት መልአከ ሞት መቶ እስኪደነግጥ እና ወደ ኋላው እስኪያፈገፍግ ድረስ ነው ነው እግዚአብሔር ጸጋውንና ክብሩን ያበዛላቸው: በስተመጨረሻም ጥር በገባ በ13 ቀን በ482 አመታቸው ስጋቸው ከነፍሳቸው ተለይታ ገነትን ወርሰዋል::

ምንጭ: ገድለ አቡነ ዘርዓ ብሩክ 
የጻድቁ አባታችን ገድለ ዜና እንኳን በዚች በምታህል ጽሁፍ አይደለም የገድላቸውም መጽሃፍም አልበቃውም እንደው እግዚአብሔር አምላክ ከበረከታቸው እንዲያሳትፈን ነው እንጂ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
ወለወላዲቱ ድንግል 
ወለመስቀሉ ክቡር

Tuesday, January 21, 2014

ቃና ዘገሊላ


‹‹ቃና ዘገሊላ›› ምንድነው?

ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡

የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡

በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ›› ‹‹የጌታ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐ 2÷1) እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጉ ላይ ታድማ ነበር፡፡ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ሥርዓት ስላልሆነ፤ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሰርጉ ታድመዋል፡፡ ይህም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ (ተገቢ ስላልሆነ) ነው፡፡ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረ ባማረ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አስተናባሪዎቹ በጭንቀት ባሕር ሰጥመው ምን እንደሚያደርጉ ግራ በገባቸው በጠበባቸው ጊዜ የችግር ጊዜ ደራሽ የኃዘን ጊዜ አፅናኝ የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረ በፀጋ የተሞላች ናትና (ሉቃ 1÷28) ማንም ሳይነግራት የልቦናቸውን ጭንቀት አይታ፣ ጎዶሎአቸውን ተመልክታ ወደ ልጃ_ ወደ ወዳጃ_ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹ወይንኬ አልቦሙ›› ‹‹ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል›› አለችው፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለሊቀ ምርፋቅ (ለአሳዳሪው) እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል አንተ ግን መልካሙን እስከ አሁን አቆይተሃል›› አለው፡፡ ወይኑም በሰው እጅ ያይደለ በሠማያዊው አባት የተዘጋጀ ስለነበር ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር፡፡

‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?››

ይህንን የጌታችንን ንግግር ብዙዎች በዘመናችን ሲሣሣቱበት ይታያል ፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ይህንን የተናገረው እናቱን ሊያቃልል ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ይህን አረፍተ ነገር መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተናጠል ስንመለከት ‹‹አንቺ ሴት›› ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› (ዘፍ 2÷23) በመሆኑም ጌታ አንቺ ሴት ማለቱ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ መንሣቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ዐረፍተ ነገር የንቀት ስለመሰለን ብቻ ‘ የዳቦ መልክ የያዘ ድንጋይ፤ ዳቦ ነው እንደማይባል’ የንቀት ንግግር ነው ልንል አይገባም፡፡ ጌታም እንዲህ ሲል ውኃውን ወይን አድርግላቸው ብትይኝ አላደርግም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጽፎ እንደሚገኘው በዕብራውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡ለአብነት ይሆን ዘንድ ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡-
የሰራፕታዋ ሴት በ 1ነገ 17÷18 ላይ እንደምናገኘው ልጇ በሞተባት ጊዜ ኤልያስን በሐዘን በለቅሶ እንዲህ ብላ ነበር ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› ትወልጃለሽ ብለህ የወለድኩት ልጅ ምን በድዬህ ምንስ አስከፍቼህ ሞተብኝ? ስትል ነው እንጂ አባባሏ የንቀት ወይም የማቃለል አይደለም፡፡
በጌርጌሴኖን አንድ አጋንንት ያደረበት ሰው ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› አለው፡፡ እውነት ይህ ቃል የንቀት ይመስላልን? የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ብሎ አምላክነቱን እየመሰከረ ሊያቃልለው ይችላልን? ደግሞስ ላለመጥፋት ፍፁም የሚፈልግ ሰው ሊያድነው ሥልጣን ያለውን ሊንቅ ይችላልን? አይችልም፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው ምን አጠፋሁ ስለምን ልታጠፋኝ ወደድክ በማለት መፍራት መራዱን ነው፡፡ (ሉቃ 8÷28-29)

ስለሆነም ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የንቀት አለመሆኑን ከሁለቱ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን፡፡ እመቤታችን እና ጌታ በንግግር አልተቃረኑም ንግግራቸው የፍቅር ነበር፡፡ ንግግራቸው የመግባባት ስለነበር ነው ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ካላት በኋላ ዘወር ብላ አገልጋዮቹን የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ያለችው፡፡

‹‹ጊዜዬ አልደረሰም››

ጌታ ይህን ቃል የተናገረው ስለ ብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ጊዜዬ አልደረሰም ማለቱ፡-
እግዚአብሔር ነገሮችን የሚያከናውንበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በመሆኑም ይህን ተአምር የምፈፅምበት ጊዜዬ አልደረሰም ሲል ነው፡፡
ጋኖቹ ውስጥ የቀረ ወይን ስለነበረ ባለው ላይ አበርክቶ እንጂ ውኃውን ወደ ወይን አልለወጠውም እንዳይሉ ወይኑ ከጋኑ ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ ድረስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡
ይሁዳ ከሠርግ ቤት ወጣ ብሎ ነበርና ወደ ሠርግ ቤቱ እሰኪመለስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡ ይሁዳ በቃና የገለጠውን ምስጢር ለእኔ ስላላሣየኝ ተከፍቼበት ከተአምራቱ ቢያጎድለኝ በሞቱ ገባሁበት፤ ሸጥኩት እንዳይል ምክንያት ለማሳጣት እንዲህ አድርጓል፡፡
እውነተኛ የሕይወት ወይን የሆነውን ደሜን የምሠጥበት ጊዜ ገና ነው ሲል፡፡

የድንግል ማርያም አማላጅነት በገሊላ ቃና

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ቤት ሣለ የወይኑን ማለቅ የማይመለከት ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእናቱን የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሊገልጥ ስለወይኑ ማለቅ እስክትነግረው ድረስ አንዳች ነገር አላደረገም፡፡ ኋላ ግን የጭንቀት አማላጅ ድንግል ማርያም ስለ ወይኑ አሰበች ልጇ ወዳጇን ለመነች፡፡ እርሱም የእናቱን ልመና ተቀብሎ ተአምራቱን ፈፀመ፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሣይነግሯት በልብ ያለውን የምታውቅ የምትመረምር እናት ናትና የሠርጉ አስተናባሪዎች ይሄ ጎደለ ሣይሏት የልቦናቸውን ሐዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን ሞልታለች፡፡ ያስጨነቃቸውንም አርቃለች፡፡ በችግራቸው ደርሳላቸዋለች፡፡ ታዲያ ሳይነግሯት የልቡናን አይታ ከማለደች ስሟን ጠርተው ለሚለምኗትም እንዴት አብልጣ አታማልድ?

ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷን በረከቷን ያሳድርብን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ ፦ በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት መማማሪያ ገጽ

ገሀድ, ከተራ

ገሀድ ምንድን ነው?

ገሃድ የቃሉ ትርጉም መገለጥ መታየት ነው፡፡ በጥምቀት መገለጥ መባሉ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ 30 ዓመት እድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲህ ሰው የሆነበት፣ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኃላ በ 30 ዓመት እድሜው በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ይሰቀላል ይሞታል ይነሳል ብለው የተናገሩለት መሲሕ እርሱ መሆኑ ተገልጦአልና እንዲሁም ሦስቱ አካላት በአንድ ጊዜ ታይተዋልና ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠለት በመሆኑ ገሃድ ይባላል፡፡(ማቴ 3፡13-17)

ይህን በማሰብ ይምንጾመው ጾም “የገሃድ ጾም” ይባላል፡፡ ቀኑም ጥር 10 ቀን ለ 11 አጥቢያ ነው፡፡ስለዚህ ጥር 10 ቀን ከ ሰባቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው የገሀድ ጾም ነው ማለት ነው!

ከተራ ምንድን ነው?

ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡

• በበዓለ ጥምቀት የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በዋዜማው የመኼዱ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቱ የጌታችን፣ምሳሌ ሲኾን ካህናቱ የመጥምቁ ዮሐንስ ምሳሌ ሲኾን መዘምራኑና ሕዝቡ ደግሞ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ሕዝቦች ምሳሌዎች ናቸው፡፡

• በባሕረ ጥምቀቱ ላይ በሚንሳፈፍ ነገር መብራት መደረጉ በርግብ አምሳል ለወረደው መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡

"የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት። " ኢያሱ 3:3

Friday, January 17, 2014

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ



ጥምቀት


ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል) አንዱና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐ. 3፥5 ላይ ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡

የጥምቀት አመጣጥ

የምሥጢረ ጥምቀት መስራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር፡፡
‹‹አሮንንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ›› /ዘፀ. 29፥4/
‹‹ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፣ በውኃም አጠባቸው፡፡›› /ዘሌ. 8፥6/
በብሉይ ኪዳን ዘመን የጥምቀት ምሳሌዎች

1. አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 14፥17/

2. ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡

3. ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 5፥14 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡

4. የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 6፥13 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 3፥20/

5. እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 14፥15/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 10፥1/

6. ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 17፥9/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 2፥11/

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?

1. ሚሥጢርን ለመግለጥ፡- ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ሚስጢረ ሥላሴ ግልፅ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/

2. ትንቢቱን ለመፈፀም፡- በመዝ 46/77/፤16 ላይ “አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈፀም ተጠመቀ፡፡

3. አርአያ ሊሆነን፡- ተጠምቆ እንድንጠመቅ አደረገን ሥርዓትን ሠራልን ቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረን አሁንም አርአያ ምሳሌ ሆነን፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌን ከእኔ ተማሩ ያለን፡፡ /ማቴ 11፤29/ ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/

4. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡- አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተፃፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡” ያለው ቆላ 2፤14

ጌታችን መች ተጠመቀ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/

ጌታችን ስለምን በ30 ዓመት ተጠመቀ?

በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/

ጌታችን በዮሐንስ እጅ ለምን ተጠመቀ?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡

ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን በማን ስም አጠመቀው?

ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ ‹‹ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?›› ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡

ዮሐንስ ጌታን ሲያጠምቀው እጁን ለምን አልጫነበትም?

- ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡
- መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል

ጌታችን ጥምቀቱን ለምን በዮርዳኖስ አደረገው?

በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ. 113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/

ጌታችን ለምን በሌሊት ተጠመቀ?

በኃጢአት ጨለማ ስለነበረ ሕዝብ የጽድቅ ብርሃን እንዲወጣለትና በጨለማ የሚመስል ኦሪት ይኖር ስለነበረ ለሕዝብ ብርሃን የሆነ ወንጌል መገለጡን ለማሳየት ነው፡፡ ኢሳ. 9፥2

- አንድም ጌታ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ትንሣኤው እንዲሁም ምጽአቱ በሌሊት ነው፡፡ ይኽም የሆነበት ምክንያት፡- ሌሊቱን ተከትሎ የሚመጣው ብርሃን በመሆኑ ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት የመሸጋገራችን ምሳሌ ነው፡፡

- አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የሚወርድ ነውና በጌታ ላይ የወረደው ርግብ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ባሉ ነበር፡፡ በሌሊት ርግብ የለም ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለምን ጌታ ከውኃ ከወጣ በኋላ ወረደ?

ሀ. ዮሐንስን ያከብሩት ነበርና መንፈስ ቅዱስ የወረደው ለዮሐንስ እንጂ ለጌታ አይደለም ይሉ ነበርና ምክንያቱን ጌታ ውኃ ውስጥ እያለ ከዮሐንስ አልተለየም ነበርና፡፡

ለ. ውኃን የሚባርክ መልአክ እንዳለ ያውቁ ነበርና ውኃውን ለመባረክ አንጂ ለጌታ አይደለም እንዳይባል፡፡

ሐ. ማረፊያ ያጣች ርግብ በባሕር ስትበር አረፈችበት ባሉ ነበርና ሐሳባቸውን በሙሉ ያጠፋ ዘንድ ከውኃ ውስጥ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥር 7


ጥር 7 አጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ

በዚህች ቀን ቅድስት ሥላሴ በኃጢያት የተገነባውን የሰናኦር ግንብ ያፈረሱበት አንድነታቸውንና ሶስትነታቸውን በግልጽ ያሳዩበት ቀን ነው፤ ሙሉ ታሪኩ ዘፍጥረት 11 ፤1 ላይ ይገኛል፤ እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው። እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ። ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ ይላል። ( “እግዝያብሔርም አለ” አንድነታቸውን ሲያጠይቅ ኑ እንውረድ ሶስትነታቸውን፤) ሥላሴ በስም አአካል በግብር ሶስት ናቸው፤የስም ሶስትነታቸው እንደምን ነው ቢሉ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፤ የግብር ሶስትነታቸውስ እንደምን ነው ቢሉ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ፤የአካል ሶስትነታቸውስ እንዴት ነው ቢሉ ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመሆኑ የሥላሴ ገጽ አካል ፊት እንደ ሰው ነውን ቢሉ አዎን እንደ ሰው ነው ነገር ግን የሰው ውሱን ጠባብ ፈራሽና በስባሽ ነው የሥላሴ ግን እንዲህ አይደለም በሰማይና በምድር በአየርና በእመቅ የመላ ረቂቅ ህያው ባህርይ ነው ኢሳ 66 ፤ 1። የሥላሴ አንድነታቸው በመለኮት በፈቃድ በስልጣን በምክር ወዘተ በመሳሰሉት ነው። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን

Tuesday, January 14, 2014

ጥር 6

ጥር 6 ከጌታችን እየሱስ ከርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱና የመጀመሪው ነው፤ ግዝረተ ክርስቶስ ይባላል፤ ሉቃ 1 ፡ 21 “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እመቤታችን ወደ ግዘረት ቤት ወሰደችው፤ ገራዡ ምላጩን ይዞ ቀረበ ነገር ግን ምላጩ እጁ ላይ ሳላ ውሃ ሆኖ ፈሰሰ፤ ጌታችንም በተአምራት የተገረዘ ሆኖ ተገኘ ይላል፤ ምነዋ ቢባል ጌታችን ደሙ የሚፈሰው ስጋውም የሚቆረሰው አንዴ በእለተ ዐረብ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን የሰውን ስርዓት ሁሉ ጠብቋል፤ እራሱ እንደተናገረው እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። ማቴ 5 ፡ 17 አምላክ ነኝና እለቱን ተጸንሼ እለቱን ልወለድ አላለም 9 ወር ከ 5 ቀን ቆይቶ ተወለደ እንጂ እንደ ህጻናትም ዋይ ዋይ እያለም አለቀሰ፤ ደግሞም እየው በዛሬዋ ዕለትም ተገረዘ፤ የሚገርም ነው፡፡ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው፤ ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነበር በአማናዊው ጥምቀት ተተክቷል፡፡ እርሱ የጥበበኞች ፈጣሪ ሲሆን ፊደል ሊቆጥር ወደ ቄስ ትምህርት ቤት የኔታ መምህሩ ጋር ሄዷል፤ መምህሩ አሌፍ በል አለው ጌታም አሌፍ አለ፤ አሌፍ ማለት የዕብራይስጥ ሆሄ ነው እኛ ሀ ሁ ሂ ሃ … እንደምንለው እነሱ ደግሞ አሌፍ ቤት ጋሜል ዳሌጥ ሄ ዋው ዛይ … ይላሉ፤ አናም ፊደል መቁጠር ጀመረ አሌፍ በል አለው አሌፍ አለ ቤት በል አለው መጀመሪያ የአሌፍን ትርጉም ንገረኝ እንጂ አለው መምህሩ ተናዶ እኔ የምልህን ዝም ብለክ በል አለው ጌታችንም መልሶ የአሌፍን ትርጉም ሳላውቅ ዘልዬ ቤት አልልም አለው ሂድ ወላጅ ይዘህ ና አለው እመቤታችንን ይዞ ሄደ እኔ ልጅሽን ማስተማር አልችልም ይዘሽሊኝ ሂጂ አላት መምህሩ የአሌፍን ትርጉም ስለማያውቀው ነው፤ ሀ ማለት ሀለዎተ እግዚብሔር መሆኑን ስንቶች መምህራኖች ነግረውን ይሆን ለዚያም ነው እኮ “” ሀሌታዋ ሀ ”” የምንለው አጋ-ጣሚ ሆኖ ዛሬ የታላቁ አባት የኖህ እረፍቱ ነው፤ “”ሐመሩ ሐ”” የምንለው ስያሜውን ያገኘው ከዚሁ ከኖህ መርከብ ነው፤ ሐመር ማለት መርከብ ማለትም አይደል፡ ይህም የእመቤታችን አንድም የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፤ ጎበዝ መምህራን ፊደል ሲያስቆጥሩ ትርጉሙን ጭምር እየተናገሩ ታሪኩን እያነሱ እያወሱ ያስተምሩ ነበር፤ ያ መምህር ግን ትርጉሙን አያውቅም ነበርና ጌታን ወላጅ አምጣ አለው፤ ልጅሽን ማስተማር አልችልም ከአቅሜ በላይ ነው አለ፤ ሰፊ ታሪኩ ታምረ እየሱስ ላይ ይገኛል፡፡ ሌላው በዛሬዋ ቀን ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ወደ ብሔረ ሕያዋን የተወሰደበት ቀን ነው፤ የዚህ ነብይ ልደቱ ታህሳስ 1 ቀን ነው፤ አዲስ አበባ አንጦጦ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ አለ ዛሬ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ከበዓሉ በረከት ያደሳትፈን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥር 4

ጥር 4 በዚህች ቀን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሞትን ሳይቀምስ የተሰወረበት ቀን ነው፤ ዮሐ 21 ፤ 20። ቅዱስ ዮሐንስ ብዙ ስሞች አሉት ፍቁረ እግዚ፤ታኦሎጎስ ( ነባቤ መለኮት ማለት ነው በአማርኛው ደግሞ ስለመለኮት የሚናገር ማለት ነው፤ ከአባቶቹ ነብያት ከወንድሞቹ ሐዋርያት መካከል እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሚስጥረ ስላሴን አምልቶ አስፍቶ የተናገረ የለም፤ሌላ ስሙ አቡቀለምሲስ ይባላል ባለ ራዕይ የራዕይ አባት ማለት ነው፤ቁጽረ ገጽም ይባላ የጌታችንን ስቃዩን ካየ በኃላ ፊቱ ሳይፈታ 70 ዓመት ሙሉ አልቅሷል፤ ከመስቀል ስር ያልተለየው ብቸኛው ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ ነው፤ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ በእንድ ቤት ልጅ ሆኗት 15 ዓመት የኖረ ይህ ሐዋርያ ነው፤ መልኩ ጌታችንን ይመስል ነበር፤ ለዚህም ነው ይሁዳ ጌታን በመሳም ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠው መልካቸው ስለሚመሳሰል ተሳስተው ዮሐንስን እንዳይዙት፤ ስለዚህ ሐዋርያት ስንቱን እንናገር ብዙ መከራ ተቀብሏል ነገር ግን እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ደሙ ፈሶ በሰማዕትነት አይደለም የሞተው፤ በ 90 ዓመቱ በዛሬዋ ቀን ከነስጋው ተሰወረ እንጂ በረከቱ ይደርብን። "በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ...ቃልም ስጋ ሆነ" ይህን ቃል ያነበበ ሰው ግን እንዴት ይስታል፤ "አቤቱ ምሳሌ ስጠኝ እንጂ ምሳሌ አታድርገኝ" የምትለዋ ጸሎት እንዴት መልካም ነች፤ ወደ ነገራችን እንመለስ፤ በነገራችን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በኤፌሶን ነው ዘመኑ መቼ ነው ቢሉ ጌታ ባረገ በ 30 ዓመቱ፤ የጻፈበት ቋንቋ ጽርዕ ይባላል፤ እናም ወንጌሉን ሲጀምር በመጀመሪያ ቃል ነበር ብሎ መጻፍ ሲጀምር ራዕይ ያያል ከዋንኞቹ መልአክት አንዱ ከትልቅ ሐይቅ ዳር ቁጭ ብሎ የሐይቁን ውኃ በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ መሬት ያፈሳል ቅዱስ ዮሐንስ ጠጋ ብሎ ምን እየሰራህ ነው ይለዋል የሐይቁን ውኃ ወደ መሬት እፍስሼ ለመጨረስ ነው ይለዋል ይህ እንዴት ይሆናል ደግሞም በእንቁላል ቅርፊት ይለዋል፤ ይህ ሐይቅ ፍጡር ነው ከረጅም ዘመን በኃላ ሊሳካሊኝ ይችላል አንተስ አለክ አይደል ቢቀዱት የማያልቀውን ቢጀምሩት የማይጨርሱትን የመለኮት ነገር የምትመራመር አለው በዚህ ጊዜ ነው የሐንስ የጀመረውን አቁሞ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ብሎ ወደ ሚስጢረ ስጋዌ የገባው ዮሐ 1፤14።

Wednesday, January 8, 2014

ጥር 1



ጥር 1 እነሆ የተባረከ ወርሃ ጥር ባተ፤ ይህ ወር ቀኑ 14 ሰዓት ሌሊቱ 10 ሰዓት ነው። በዚህ ወር ታላላቅ በዓላት ይከበራሉ ከነዚህም መካከል፤- ብርሃነ ጥምቀቱ፤ ግዝረቱ፤ ቃና ዘገሊላ፤ ቅድስት ስላሴ፤ የእመቤታችን እረፍት፤የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ፤ የዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፤የነብዩ ኤልያስ፤የቅዱስ ኡራኤል ዓመታዊ በዓላቸው ሲሆኑ ሌሎችም ታላላቅ ቅዱስን አባቶች ታስበውና ተዘክረው ይውላሉ። እነሆ ጥር 1 ቀን የቀዳሚ ሰማዕት የሊቀ ዲያቆናት የቅዱስ እስጢፋኖስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ የዚህ ሰማዕት ልደቱም በዚሁ ቀን ነው። በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ዝነኛው ገዳሙ ሃይቅ እስጢፋኖስ በመዲናችን አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚገኘው ደብሩ ከቀደምቶቹ አንዱ ነው። እስጢፋኖስ ማለት ወደብ ጸጥታ ማለት ሲሆን ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድዕት ነው፤ ለምን ቀዳሚ ሰማዕት ተባለ ከሱ በፊት ሰማዕታት የሉም ነበርን ? ቢሉ መኖርስ አሉ የእርሱ ግን ቀዳሚ መባሉ ከጌታችን እርገት በኃላ ስለ ጌታችን መውረድ መወለድ መስክሮ የሞተ የመጀመሪያው እርሱ ስለሆነ ነው፤ እሺ ለምንስ ሊቀ ዲያቆናት ተባለ ቢሉ በሐዋርያት እጅ ከተሾሙት ሰባቱ ዲያቆናት ውስጥ የሁሉም አለቃ እርሱ ስለሆነ ነው ሐዋ 6 ፤ 5። መጽሐፍ ቅዱስ ስለእስጢፋኖስ እንዲህ ሲል በእውነት መሰከረ "እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበረ...ፊቱም የመልአክ ፊት ይመስል ነበር ፤ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም ሐዋ 6፤ 8 ። እህሳ አይሀድ አማጽያን መልስ መስጠት ቢያቅታቸው ድንጋይ አነሱ ልብ አናቱን እያሉ ወገሩት፤ ቀና ብሎ ቢመለከት ቅድስት ስላሴን አየ፤ አቤቱ ይህን ኃጢያት አትቁጠርባቸው ይቅር በላቸው እያለ ነፍሱን ሰጠ። ሐዋ 7፤ 60፤ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወለደው በኢየሩሳሌም በምትገኝ ሐኖስ በተባለች ቦታ ነው:: አባቱ ስምዖን ሲባል እናቱ ደግሞ ሐና ትባላለች ነገዱ ከነገደ ብንያም ነው :: የኦሪትን ሕግና ሥርዓት ከኦሪቱ ምሁር ከገማልያል ተምሯል::በሐዋርያት ሥራ ምዕ. 6 እንደምናነበው ሕዝቡን በማዕድ ያገለግሉ ዘንድ ሰባት ዲያቆናት ተመርጠዋል ከእነዚህ መካከል ቅዱስ እስጢፋኖስ አንዱ ሲሆን ለስድስቱ ዲያቆናት ደግሞ አለቃ( ሊቀ ዲያቆን) ሆኖ ተሹሟል ይህም የሆነው በጥቅምት 17 ነው :: ቅዱስ እስጢፋኖስ በማዕድ አገልግሎት ሕዝቡን ከማገልገሉ በተጨማሪ ወንጌልን ይሰብክ ነበር ተአምራትን የማድረግ ጸጋም ተሰጥቶት ነበር በዚህም አገልግሎቱ ብዙዎችን ወደክርስትና መልሷል:: በዚህም አይሁድ በቅናት ተነሳስተው በሐሰት ከሰሱት ከከተማውም ወደ ውጭ አውጥተው ቄዳር በተባለ ቦታ በድንጋይ ወገሩት በሚወግሩትም ጊዜ ሰማያት ተከፍተው ምሥጢረ ሥላሴን (እግዚአብሔርን በሦስትነቱ ) ተመለከተ ኢየሱስ ክርስቶስንም በአብ ቀኝ ተቀምጦ አየ ለሚወግሩትም ሰዎች ከአምላኩ እንዲህ በማለት ምሕረትን ለመነ "ጌታ ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው "በመጨረሻም "ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል" ብሎ ነፍሱን ሰጠ ::የሐዋርያት ሥራ ምዕ 7 በተወለደ በ 30 ዓመቱ በ35 ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ::
ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ልደቱ ለእግዚእነ





ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ::


በቀሲስ ደመቀ አሸናፊ


በጌታችንና በአምላካችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገልን ፍፁም ሥርየትና እርቅ ግልጥ ሆኖ የተጀመረው በነገረ ልደት ነው። የጌታችን ልደት በነገረ ድኅነት ትልቅ ስፍራ የያዘና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ፍፁም ልዩ መሆኑን ያሳየ ነው። መስተፃርራን የነበሩ ሰማይና ምድር፣ ሰውና መላእክት በአንድነት ለምስጋና ታድመዋል። የእረኞች አንደበት ከመላእክት ጋር ለሰማያዊ ምስጋና ብቁ የሆነበት፤ ግዕዛን የሌላቸው እንስሳት ሰራኢ መጋቢያችን፣ በዘባነ ኪሩቤል በሰማያት የምትገለጥ አንተ ነህ ሲሉ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት፤ የምድር ነገስታት በሥልጣንህ ሽረት በመንግሥህ ህልፈት የሌለብህ የነገስታት ንጉሥ አንተ ነህ ሲሉ ወርቅን ለመንግሥቱ፣ ዕጣንን ለክህነቱ፣ ከርቤን ለህማሙ ዕጅ መንሻን ያበረከቱለት፤ ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር ያን ልዩ ክብር የዩበት፤ ይህ ልደት በእውነት ልዩ ነው።

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልንን ድንቅ የማዳን ሥራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦ "በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰዉ ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፣ ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋህዷልና ቅድምና የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ይህች ቤተልሔም መንግሥተ ሰማያትን መሰለች" አለ፤ የጌታን ልደት በተናገረበት አንቀጽ። በአባታችን በቀዳማዊ አዳም ምክንያት ያጣናትን ልጅነት ሊሰጠን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የመንግሥተ ሰማያትን የምስጋና ኑሮ በቤተልሔም ገልጧልና። ስለዚህ ነገር ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ "አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ አንቺ ከይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን ይወጣልና፤" በማለት የተነበየውም ስለዚህ ነበር ፤ ሚክ5፥2። “ወአንቲኒ በቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሃቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይውጽእ ንጉሥ ዘይርዕዮሙ ለህዝብየ እስራኤል” እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም።

ቤተልሔም ማለት ቤተ ህብስት፣ የህብስት ቤት፣ የእንጀራ ቤት ማለት ነው። ይህም ካሌብ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስት፣ ኢያሪኮን "ሃይል ዘእግዚአብሔር ኲናት ዘኢያሱ" ብለው በኢያሱ መስፍንነት ሲወርሱ ከኢያሱ የተሰጠችው ምድር፣ ኬብሮን ነበረች። ይህችም የይሁዳ ምድር በኋላም የቅዱስ ዳዊት ከተማ የሆነች ናት። አስቀድሞ ካሌብ ከብታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ከብታ አላት ትርጓሜውም የምስጋና ቤት ማለት ነው፤ ይህም ካሌብ በመንፈሰ እግዚአብሔር በዚህች ምድር የሚገለጠውን የክርስቶስ የልደቱን ነገር፣ እና የመላእክትን ምስጋና ስለተረዳ ነበር። በኋላም ካሌብ ኤፍራታ የምትባል ሚስት አገባ ቦታዋን በዚህች ሚስቱ እንደገና ኤፍራታ ብሎ ጠራት። ኤፍራታ ማለት ፀዋሪተ ፍሬ፣ ፍሬ በውስጧ ያለባት ማለት ነው። ይህችውም የእመቤታችን ምሳሌ ናት የህይወት ፍሬ ክርስቶስን ወልዳልናለችና፤ አንቲ ውእቱ ዕፅ ቡሩክ ፍሬኪኒ ፍሬ ሕይወት እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን። ቤተልሔም ይህን ስያሜዋን ያገኘችው ካሌብ ከኤፍራታ ባገኘው ልጁ በልሔም ነው፤ ልሔም ማለት ህብስት፣ እንጀራ ማለት ነው ይህም ምሳሌነቱ የጌታ ነው፤ ይኸውም አማናዊ፣ እውነተኛ የሕይወት እንጀራ፣ህብስት ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሊያድነን የመወለዱ ምሳሌ ነው። "ከሰማይ የወረደ ህያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል እኔም ስለዓለም ህይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።" እንዲል ዮሐ 6፥51።

በክርስቶስ ልደት መላእክት ባልተለመደ ሁኔታ ከሰዎች ጋር ተባብረው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ሰላምም ለሰው ልጅ በምድር እርሱ በሚፈቅደው እያሉ ንጉሥ ክርስቶስን አመሰገኑ። ሉቃ 2፥14። በሰማያት በዘባነ ኪሩቤል የሚገለጥ፤ ፍፁማን ግሩማን በሚሆኑ መላእክት፣ ሊቃነ መላእክት፣ ሥልጣናት፣ አጋእዝት የሚመሰገን ሰማያዊው ንጉሥ ዛሬ ስለእኛ ፍቅር ሲል ሊነገር በማይችል ፍፁም ትህትና ከመ ሕጻናት ታቅፎ፣ ከኀጢአት ብቻዋ በቀር የኛን ባህሪ ባህርዩ አድርጎ ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ሆኗልና።”ሕፃን ተወልዶልናልና፥ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይኾናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ኀያል አምላክ፥የዘለዓለም አባት፥የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ትኢሳ 9፥6።

ለዚህ ለክርስቶስ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ በሙሉ አፍአዊና ውሳጣዊ ህሊናችን እርሱን ዘውትር እናመስግን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ይህን ፍፁም ፍቅር ለሰው ልጅ በኀጢዓት ተዳድፈን ለነበርን መደረጉን እያሰበ በአንክሮ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው፧ወይስ ትጐበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው፤ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንኽለት፥በእጆችኽም ሥራ ላይ ሾምኸው፤ዅሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛኽለት” በማለት ይናገራል። ዕብ 2፥6።እኛም በክርስቶስ የተጠራን ሁላችን ይህን ያምላክ ፍቅር ዘወትር በልቡናችን እንድንስልና ከባልንጀሮቻችን ጋር በትህትናና በፍቅር እንድንኖር ሲመክረን፦ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለች ይህች ሃሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ትኑር፤ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከሰው ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ አልቆጠረም ነገር ግን፥የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ኾኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤” ይለናል፤ ፊል 2፥5።

ይህ የጌታ ልደት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ነው። ሁሉ በአንድነት የተሰባሰቡበት በጋራ የዘመሩበት፤ በዚይች በበረት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በሆነችው ጌታችን ከመሀል ከእናቱ ጋራ እንዲሁም አረጋዊ ዮሴፍ ከማሕበረ ጻድቃን፣ ሰማያውያን መላእክት፣ እረኞች፣ ሰባሰገል ነገሥታት፣ እንስሣትም ሳይቀሩ ባንድነት የተገኙባት የፍቅርና ያንድነት ቤት ናት። ስለዚህ እኛም የክርስቶስ አባግዓ መርዔቱ፣ የመንጋው በጎች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በፍፁም አንድነት መኖር እንዳለብን “ወንድሞች ሆይ፥ዅላችኹ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፤ ባንድ ልብና ባንድ ሃሳብም የተባበራችኹ እንድትኾኑ እንጂ መለያየት በመካከላችኹ እንዳይኾን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችዃለኹ።” የተባለውም ስለዚህ ነውና። 1ኛቆሮ 1፥10። በማለት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ያስተምረናል። የጌታችንና የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።

ታህሳስ 25


ታህሳስ 25 በዚህች ቀን አቡነ ዮሐንስ ከማ አረፈ።ይህ አባት ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ ብዙ ገድላትንና ድርሳናትን ዋቢ አድርገው፤ አገሩ ሰሜን ጎንደር እንደሆነ ትግራይ ውስጥ ሰለዋ በተባለ ቦታ ቀብጽያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን የመሰረተ አባት እንደሆነ “የኢትዮጵያ ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ” በሚል መጽሐፋቸው በስፋት ጠቅሰውታል፤ ስንክሳሩ ላይም ታሪኩ ተጽፏል። አባ ዮሐንስ ከማ ወላጆቹ ሚስት ድረውለት ነበር ነገር ግን ጫጉላቤት ሳሉ እህቴ ሆይ እኔ በድንግልና መኖር ነው የምፈልገው ይላታል እርሷም እኔም እንጂ እንዳንተው በድንግልና መኖር ነው የምፈልገው ትለዋለች፤ በአንድ አልጋ ይተኛሉ መልአከ እግዚያብሔር ክንፉን እያለበሳቸው፤ በግብር ሳይተዋወቁ ለረጅም ዘመን ኖረዋል ፤ ወቸው ጉድ እሳትን ታቅፎ የማያቃጥለው ሰው እንዳለ ያየ የሰማ ማን ነው ? አለ ደራሲው፤ ወላጆቻቸው እንዴት ነው ነገሩ ልጅ አይወልዱም ወይንስ ገና ልጆች ስለሆኑ ይሆናል እያሉ ይከራከሩ ነበር፤ በኃላ ላይ መልአከ እግዚያብሔር እየመራው አስቄጥስ ከአባ መቃርስ ገዳም አደረሰው በዚያም መነኮሰ በአባ ዮሐንስ ሐጺር ገዳምም ኖሯል፤ ኢትዮጰያ ውስጥም እንደነ አቡነ አሞጽ፤ አቡነ ቀጸላ ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ታላላቅ የቤተክርስቲያን ከዋክብት የተሰኙ ብዙ መነኮሳትን አመንኩሷል፤ ትግራይ ውስጥ ቀብጽያ በተባለ ገዳሙ ተአምራትን የምታደርግ የነሐስ መቋሚያ አለችው፤ አሁንም ድረስ አለች፤ገበሬው ነው የሚጠብቃት። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለመቋሚያ ካነሳን ዘንዳ የአቡነ ቶማስ ዘሽሬ መቋሚያ ሴት ወደ ገዳሙ ሲገባ ትጮሃለች፤ የአቡነ አካለ ክርሰቶስ መቋሚያ ደገሞ ቤተክርስቲያኑ ካልታጠነ ትሰወራለች፤ የአቡነ ተክለ አልፋ መቋሚያ ነፍሰ ያጠፋ ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲገባ ድምጽ ትሰጣለች፤ በመጽሐፍ ቅዱስም ከተመለከትን የሙሴ የአሮንና የዮሴፍ አረጋዊ በትር ገራሚ ገራሚ ተአምራትን ሰርተዋል። ጻድቁ በታህሳስ 25 ቀን አርፎ ትግራይ ውስጥ እራሱ በቆረቆረው ገዳም ተቀብሯል፤ ጎንደር ጸለምትም ትልቅ ገዳም አለው። በረከቱን ይደርብን፤

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Wednesday, January 1, 2014

ታህሳስ 24


ታህሳስ 24 በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክልሃይማኖት የተወለዱበት ቀን ነው። የትውልድ ቦታቸው ሸዋ ጽላልሽ አወራጃ ዞረሬ ነው፤ የአባታቸው ስም ጸጋ ዘአብ የእናታቸው ስም እግዚ ሐርያ ይባላል መካን ነበሩ ልጅ እንዲሰጣቸው ወደ እግዚያብሔር ዘወትር ይጸልዩ ነበር፤ መጋቢት 12 ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሞተሎሜ የተባለ ጣኦት አምላኪ ንጉስ አገራቸውን ወረረ መንደሩንም አጠፋ ጸጋ ዘአብ ወንዝ ውስጥ ገብቶ አመለጠ እግዚ ሐርያ ግን ተማርካ ሄደች፤ በጣም መልከ መልካም ስለነበረች ሞቶሎሜ ሊያገባት አሰበ ታላቅ ድግስም ደገሰ አገር ምድሩ ተሰብስቦ ሲዘፍን ሲጨፍር ሳለ ቅዱስ ሚካኤል ታላቅ መብረቅ ነጎድጓድ አሰማ ብ...ዙዎች ሞቱ እግዚሐርያን በክንፎ ተሸክሞ ዞረሬ ከቤተክርስቲያን ውስጥ አስቀመጣት ከባለቤቷ ጸጋ ዘአብ ጋር ተገናኙ ተቃቅፈው ተላቀሱ፤ከሁለት ቀን በኃላ መጋቢት 24 ቀን ተክልዬ ተጸነሱ በዛሬዋ ቀን 1167 ዓ/ም ተወለዱ ቀኑ አርብ ነበር፤ በተወለዱ በ3ኛ ቀናቸው እሁድ በ 3 ሰዓት “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብለው ስላሴን አመሰገኑ፤ ሁለተኛ ተአምር ከዚህ በታች ያለው ስዕል ተክልዬ የአንድ ዓመት ከመንፈቅ ህጻን እያሉ ነው፤ በድፍን ሸዋ ርሃብ ተከስቶ ነበር በተለይም በዞረሬ እግዚሐርያ አዘነች አለቀሰች ምነው እርቧት ነው ጠምቷት ነው ቢሉ የለም እርቧትስ ጠምቷትስ አይደለም የቅዱስ ሚካኤል ዝክሩ ታጎለቢኝ ብላ እንጂ፤ ህጻኑ ተክልዬ ከእናቱ ጭን ወርዶ እየዳኸ ወደ ጓዳ ሄደ አንስታ አቀፈችው እርሱ ግን አለቀሰ ዱቄት የተቀመጠበትን እንቅብ እንድትሰጠው በእጁ ጠቆማት ሊጫወትበት መስሏት ሰጠችው በትንንሽ እጆቹ እንቅቡ ላይ አማተበ ዱቄቱ ሞልቱ ፈሰሰ ዳግመኛ የቅቤ የዘይት ማስቀመጫ ማድጋዎች ላይ በተመሳሳይ አማተበ ሞልቶ ፈሰሰ ቤቱ በበረከት ተትረፈረፈ፤የቅዱስ ሚካኤልን ዝክሩን አዘከረች አገሬውን ጠርታ መገበች፤ለተቸገሩትም አብዝታ ሰጠች፤ ይህ በረከት ሁለቱም እስኪሞቱ ድረስ አላለቀም ይላል ገድላቸው። ተክልዬ በ 99 ዓመት ከ 10 ወር ከ 10 ቀን በዚህ ምድር ኖረው ነሐሴ 24 ቀን አርፈዋል። በደብረሊባኖስ ገዳማቸው የንፍሮ ውኃ አይነስውር ያበራል ድውይ ይፈውሳል ገድላቸው ሊነበብ ሲወጣ አጋንንት ተቃጠልን ይላሉ ሲገርም ምን ያህል ባለጸጎች ነን። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

ታህሳስ 23


ታህሳስ 23 በዚህች ቀን በእስራኤል ያይደለ ለእስራኤል የነገሰው ልበ አምላክ ዳዊት አረፈ፤ ለመሆኑ ዳዊት እንዴት ተወለደ ቢሉ ታሪኩ እንዲህ ነው፤- አባቱ እሴይ እናቱ ሀብሊ ይባላሉ፤ ጎረቤታቸው አንድ ጎረምሳ ነበር ሀብሊን ስትወጣ ባቷን ስትገባ ደረቷን ይመለከታት ነበር የዳዊት አባት ይህን ተመልክቶ ጠረጠረ መንገድ ልሄድ ነውና ስንቅ ሰንቂሊኝ አላት አዘጋጅታ ሰጠችው ደህና ሰንብቱ ብሎ ወጣ፤ሌሊት ተመልሶ መጣ ጎረምሳውን መስሎ ከሚስቱ ጋር አደረ አሷ አላወቀችም፤ በዚያች ሌሊት ግንኙነታቸው ዳዊት ተጸነሰ ሚያዚያ 6 አባቱ እሴይን መስሎ ተወለደ፤ ለዚህም ነው ዳዊት በመዝሙር 51 ፤ 5 ላይ "እነሆ፥ በዓመ...ፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።" ብሎ የተናገረው። ቅዱስ ዳዊት ጥቅምት 12 ቀን ነብዩ ሳሙኤል ቀብቶ ሲያነግሰው ሰባት ሀብታት ተሰጥተውታል፤ ምን ምን ናቸው ቢሉ ሀብተ መንግስት፤ ሀብተ ክህነት፤ሀብተ ኃይል፤ሀብተ በገና፤ሀብተ ፈውስ፤ ሀብተ ትንቢት እና ሀብተ መዊዕ ( የማሸነፍ ድል የማድረግ) ናቸው። አንበሳ በእርግጫ ነብርን በጡጫ ይገድል ነበር 1ሳሙ 17፤34 ሀብተ ፈውስ ያለው በገና ሲደረድር እርኩሳን አጋንንት ይርቁ ነበር በሽተኞችም ይፈወሱ ነበር፤ እግዚያብሔር እንደ ልቤ የሚሆን የእሴይ ልጅ ዳዊትን አገኘሁ ብሎ መስክሮለታል፤ ደግሞም ሰው ነውና ከኦርዮን ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር በዝሙት ወድቋል፤ ኦርዮንንም አስገድሏል፤ በዚህም ተጸጸቶ እንባው ሳር እስኪያበቅል አንሶላውን እስኪያርስ ድረስ አልቅሷል፤ እግዚያብሔርም ይቅር ብሎታል። ቅዱስ ዳዊት የደረሰው 150 መዝሙረ ዳዊት የማይዳስሰው ነገር የለም ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን በሁሉም አገልግሎቶች የምትጠቀምበት፤ እግዚያብሔር በጣም የሚወደው ጸሎት ዳዊትንና አቡነ ዘበሰማያትን ነው፤ እመቤታችን ደግሞ በጣም የምትወደው ጸሎት ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያምን ነው። ቅዱስ ዳዊት 40 ዓመት ነግሶ ታህሳስ 23 በዛሬዋ ቀን አርፏል። በረከቱ ይደርብን ከቅዱስ ጊዮርጊስም በረከት ያሳትፈን።