ስለምን ቤተክርስቲያን እንሳለማለን ? ስለምን እንሰግዳለን?
ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተክርስቲያን አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፡፡
ሁልጊዜም እንደምንለው ቤተክርስቲያናችን ሁሉን በማስረጃ ታደርጋለች እንጂ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት በተረት አይደለም አሁንም በዚህ ርዕስ ዙሪያ ጥያቄ ለሚያነሱ ይህንን ምላሽ እንሰጣለን ነገር ግን ስለመማማር ነው እንጂ ስለክርክር አይደለም፡፡
እኛ ኦርቶዶክሳውያን በሕንጻ ቤተ እግዚአብሔር ተገኝተን እንሳለማለን፣እንሰግዳለን ይኸውም ለባለቤቱ ያለንን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ እንጂ የምናመልከው ማንን እንደሆነ እናውቃለን፡፡
የመሳለማችን ወይም የመስገዳችን ምስጢር በቤተ እግዚአብሔር ፊት ስለሆነ የምንሰግደው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሕንጻው ወይም ለድንጋዩ አይደለም ይህንንም በማስረጃ እናስረዳለን፡-
"ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳን ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር ሕዝቡም ሁሉ ተነስቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር፡፡"(ዘፀ. 33፡10)
እንግዲህ ለድንኳን አንሰግድም አላሉም በዛ ቤት፣ በዛ ድንኳን ለከበረው ለእግዚአብሔር ሰገዱ እንጂ
"ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወረደ የሚቃጠለውን መስዋዕትና ሌላ መስዋዕቱን በላ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ፡፡ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም፡፡ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የእግዚአብሔርም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ፡፡ እርሱ መልካም ነውና ምህረቱም ለዘላለም ነውና ብለው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡"(2ኛ ዜና.7፡1-3)
በግልጽ እንደተረዳን ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ናትና በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን እንሰግዳለን፡፡
"ዳዊትም ከምድር ተነስቶ ታጠበ ተቀባም ልብሱንም ለወጠ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ፡፡"(2ኛ ሳሙ.12፡20)
ከቅዱስ ዳዊትም እንደተማርነው እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ እንደፈቃዱ ሆነ ብለን በተቀበልን ጊዜ ተነስተን፣ ለቤተክርስቲያን የሚገባ ልብስ ለብሰን ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ ልንሳለምና ልንሰግድ ይገባል፡፡
" እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤት እገባለሁ አንተንም በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ፡፡"(መዝ. 5፡7)
"የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፡፡"(መዝ. 28(29)፡2)
ታዲያ ይህ የቅድስና ስፍራ ቅድስት ቤተክርስቲያን አይደለምን ዳግመኛም እንዲህ ተናገረን፡-
"በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፡፡"(መዝ. 95(96)፡9 )
" በመላዕክት ፊት እዘምርልሃለሁ ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፡፡"(መዝ. 137(138)፡2)
እነግዲህ በዚህ ቃል ውስጥ ቅዱስ መቅደሱ ቤተክርስቲያን መሆኗን እንዴት መረዳት ያቅተናል?
" አለቃውም በስተውጭ ባለው በር በደጀ ሰላሙ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደህንነቱን መስዋዕት ያቅርቡ እርሱም በበሩ መድረክ ይስገድ፡፡"(ሕዝ.46፡1-2)
ከደጅ መባችንን ስናቀርብ በበሩ ላይ ተደፍተን የምንሰግደው ይህን መመሪያ አድርገን ነው ለቤተክርስቲያንም መስገዳችን በውስጡ ላደረ ለእግዚአብሔር መንፈስ መስገዳችን ነው፡፡
መናፍቃኑ ቤተክርስቲያን አያስፈልግም የእኛ ሰውነት ራሱ ቤተክርስቲያን ነው ይላሉ።??
እኛም እግዚአብሔር በሕንፅው ብቻ ይወሰናል አላልንም የአምልኮቱ ቤት ነዉ አልን እንጂ።እኛም ማድሪያዎቹ ነን!
ነገር ግን እንርሱ ስለሚቃወሙት ቤተመቅደስ ጌታ በወንጌል ላይ እንዲህ አለ፤-
"ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል "(ማቴ. 21:13 , ማር.11:17)
እንዲሁም እግዚአብሔር ኣምላክ አስቀድሞ ለሙሴ በመካክላችሁ አድር ዘንድ ቤተ ምቅደስ ስሩልኝ ስላለ በቤተ መቅደስ ተሰብስበን አምልኮ መፈፅም ስህተት አይድለም::
”በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ”(ዘጸ.25:8 )
” ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው”(ዘፍ.28:16)
አንዳንድ ሰዎች ቤተክርስቲያንን በእጃችን እያበስን ስንሳለም ሊገርማቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እንደሆነ አድርገው ሊቆጥሩ ይችላሉ?
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦
"ከድንኳኑ ጀምረህ በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳትን በሙሉ ቅብዓ ቅዱስ ወይም ሜሮን ቀባና ቀድሳቸው እነሱን የነካም ቅዱስ ይሆናል።" (ዘጸ.30:22)
እኛም የቤተክርስቲያንን ዘርፍ በእምነት የምንዳስሰው በዚህ ምክንያት ነው። 12 አመት ሙሉ ትደክም የነበረችው ሴት እምከመ ገሰስኩ ጽንፈ ልብሱ አሀዩ /በእምነት ሆኜ የልብሱን ዘርፍ ብዳስስ እፈወሳለሁ/ ብላ እንደዳነችው እኛም በእምነት የቤተክርስቲያንን ዘርፍ ብንዳስስ እንፈወሳለን። ጌታ የቤተክርስቲያን ራስ ነውና የልብሱ ዘርፍም ቤተክርስቲያን ናትና!!! ኤፌ.1:22
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ” እንደሚል የሐዋ. 20:28
ከሁሉ በላይ ደግሞ የቤተክርስቲያንን መኖር የምትቃወሙ ሆይ እግዚአብሔር ለእርሷ የገባውን ይህንን ታላቅ ቃል ስለምን አታስተውሉም የሰጣትን ክብር ስለምን ዘነጋችሁት?
"በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤ በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ፡፡"(1ኛነገ.9፡3 )
* እነሆ በመንገድ እየሄድህ ሳለ ቤተክርስቲያንን ብታያት ሰላምታ ትሰጣት ዘንድ ስለምን ታፍራለህ?
ወዳጄ እምነታችን አኮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው! ሰላምታ ለቤተክርስትያን መስጠት ከሐዋርያት የተማርነው ነው፡፡ማስረጃ የሚጠይቀንም ቢኖር እነሆ:-
"ወደ ቂሳሪያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ፡፡" (የሐዋርያት ሥራ 18፡22)
እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ያደረገውን እናደርግ ዘንድ ስለምን እናፍራለን? እርሱ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ ብሎ ያስተማረን አይደለምን?
ለሁላችን ማስተዋልን ያድለን አሜን!!!
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ፡፡
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl