Friday, May 31, 2013

ግንቦት 24

በዚህች ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን እግዚያብሔርን ይዛ ከዮሴፍና ከሶሎሜ ጋር ወደ ግብጽ የተሰደዱበት ቀን ነው፤ ይህን ቀን ቤተክርስቲያን በደማቁ አክብራው ትውላለች፤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ቤተክርስቲያን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል።እነሆ፥ የጌታ መል...አክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ማቴ 213 በስደት የቆዩት ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ነው የእመቤታችን ስደት ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከት ነው የጣና ደሴቶችን የዋልድባ ገዳምን አክሱምና የትግራይ አውራጃዎችን፤ ድብረ ዓባይና የጎጃም ታላላቅ ገዳማትን በርካታ የኢትዮጵያ አውራጃዎችን በኪደተ እገራቸው ባርከውታል ቀድሰውታል።፤የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ አለ ነብዩ ዕንባቆም፤ ዕንባቆም 37 ነብዩ ምን ማለቱ ነው ? መቼ ነው የኢትዮጰያ ድንኳኖች የተጨነቁት ? እመቤታችን በስደት ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣም እይደል። ግን ግን ስደቷ ግንቦት 24 ከሆነ ለምን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን የጽጌ ጾም ብለን ስደቷን እናስባለን ካሉ፤ይህ ሊቃውንቱ የሰሩት ስርዓት ነው፤ ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 25 በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ዘመነ ጽጌ ይባላል የአበባ የልምላሜ ወቅት ነው፤ እመቤታችን ደግሞ በአበባ ትመሰላለች አበባ የፍሬ እናት ነው፡፡ እመቤታችንም የተባረከ ፍሬ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርሰቶስን ያስገኘች አማናዊቷ አበባ ናት፡ ስለዚህም ይህን የስደቷን ወራት በዘመነ ጽጌ ባሉት 40 ቀናት ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን ታስቦ እንዲውል
የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስርዓትን ሰሩ።
 እግርሽ ጨረቃን የሚጫማ
 
በአሸዋ ስትሮጪ እግርሽ ደማ

ውቅያኖሶቹ ግራ ቀኙ የሚሰፈሩት በእፍኙ

ለእርሱ ለእርሱ ለዝናብ ጌታ ውኃ ነሱ።

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን

Wednesday, May 29, 2013

ግንቦት 21



 ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መልአክትን አስከትላ ትገለጽላቸው ነበር፤እስላምም ክርስቲያንም በግልጽ ይመለከቷት ነበር። ከየአገሩ ያሉ ሰዎች ይሰበሰባሉ ድንኳን ተክለው ሰቀላ ሰርተው አጎበር ጥለው ይከትማሉ ፤ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተ...ከታታይ ቀናት ሳታቋርጥ ትገለጽላቸው ነበር፤ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አዳም አባታችንን አሳይን ይሏታል ገሚሱ ነብዩ ዳዊትን ገሚሱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሳይን ይሏታል አንዳንዱም ከዚህ ቀደም የሞተ ዘመዱን እንድታሳየው ይጠይቃታል፤እርሷም ለሁሉም ፍቃዳቸውን ትፈጽምላቸው ነበር፤አዳምን ስትጠራው ከሔዋን ጋር ዳዊትን ስትጠራው ከበገናው ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ስትጠራው ከጸአዳ ፈረሱ ጋር ነው። ወይ ግሩም ታዲያ ይህ በዚያ ደጉ ዘመን ነበር፤አሁን ግን ኃጢያታችን ሲበዛ በረድኤት ካልሆነ በገሃድስ ተገልጻ አትታይም ለበቁ ካልሆነ። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን አባ መርትያኖስ አረፈ፤ ይህም በህጻንነቱ መንኩሶ ለ 67 ዓመት በፍጹም ተጋድሎ የኖረ ነው። ይህ ገድል ትሩፋቱ በሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ እነሆ አንዲት በዝሙት ስራዋ እጅግ የምትታወቅ ሴት ዘንድ ወሬው ደረሰ፤ እርሱ እኮ የሴት ፊት ስላላየ ነው እንጂ በፍትዎት ይወድቃል ከክብሩም ይዋረዳል አለቻቸው ባልንጀሮቿም የለም በፍጹም አያደርገውም አሏት፤ እኔ በዝሙት ከጣልኩት ምን ትሰጡኛላችሁ አለቻቸው ብር እንሰጥሻለን አሏት፤በዚህ ተወራርደው ሄደች፤ ሽቶ ተቀባብታ አምራ ተውባ ሄደች፤ስንክሳሩ እጅግ ውብ መልከመልካም ነበረች ይላታል፤ እስኪመሽ ከገዳሙ አቅራቢያ ቆይታ በሩን አንኳኳች የመሸቢኝ እንግዳ ነኝ አሳድረኝ ትለዋለች፤ ነፍሱ ተጨነቀች ባስገባት የዝሙት ጦር ይነሳብኛል ብተዋት እንግዳ ሆኜ መጥቼ መቼ ተቀበላችሁኝ ብሎ ይፈርድቢኛል ደግሞም አውሬ ይበላታል ብሎ አሰበ፤ባስገባት ይሻለኛል ብሎ አስገባት የተቀበችው ሽቶ ዝሙት የሚቀሰቅስ ነው፤ ቀረበችው፤አባቴ በዚህ ማንም አያየንም አብረን እንተኛ አለችው፤እሳት እያነደደ ነበርና እሺ ምን ችግር አለው እዚህ አሳት ላይ ምንጣፍሽን አንጥፊና እንተኛለን አላት፤ አንድም እግሩን ወደ እሳቱ ማገደው ይላል አይንህ ብታሰናክልህ ካንተ አውጥተህ ጣላት አይደል የሚለው መጽሐፉ፤ ደነገጠች ምንድን ነው አባቴ አለችው፤ ይህ ያስደንቅሻልን የገሃነም እሳትን ታዲያ እንዴት ልትችይው ነው አላት እግሩ ስር ወድቃ ይቅር በለኝ አለችው እርሱም ሌሊቱን ሙሉ ሲያስተምራት አደረ፤ ሲነጋ አልተመለሰችም አመንኩሰኝ ከዚህ በኃላ ወደ ዓለም አልመለስም አለችው አመነኮሳት ከደናግል ገዳም ወስዶ ለእመምኔቷ አደራ ሰጣት፤የሚገርመው ይህች እናት ከብቃቷ የተነሳ የመፈወስ ሀብት ተሰጣት ብዙ በሽተኞች ወደርሷ እየመጡ ይፈወሱ ነበር፤ አባ መርትያኖስ ግን ድጋሚ ሌላ ሴት መጥታ እንዳትፈትነው ሰው የማይደርስበት ከባህር መካከል ባለች ደሴት ብቻውን መኖር ጀመረ፤ ከብዙ ዘመን በኃላ መርከብ ተሰብሮ ብዙዎች ሲሞቱ አንዲት ሴት በመርከቡ ስባሪ ተጣብቃ እርሱ ካለበት ደሴት ደረሰች ባያት ጊዜ ደነገጠ አደነቀም ከእርሷ ጋር በአንድነት ስለመኖሩም አዘነ፤ ይምትበላውን ሰጥቷት የምትለብሰውን አዘጋጅቶላት ሲያበቃ ተወርውሮ ወደ ባህሩ ገባ ዓሳ አንበሪም ተሸክሞ ወደ የብስ አደረሰው ከዚህ በኃላ በአንድ ቦታ ላለመቀመጥ ወስኖ በ108 አገሮች የሚገኙ ታላላቅ ገዳሞችን ዞረ በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን በክብር አረፈ፤ እመቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፤ እኛንም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

ግንቦት 17


በዚህች ቀን ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት አባ ኤጲፋንዮስ አረፈ። ወላጆቹ ክርስቶስን የማያምኑ አይሁዳውያን ናቸው በዛ ላይ እጅግ በጣም ድሆች ፤አባ ኤጲፋንዮስ ክርስቶስን ያመነው ክርስትናን የተቀበለው ሁለት ታአምራቶችን አይቶ ነው፤ አንደኛው እርሱ እናቱና እህቱ ርሃብ ሲጠናባቸው የአባቱን አህያ ሊሸጥ ገብያ ሄደ አህያው በጣም አስቸጋሪ ነበርና አንዱን... ገብያተኛ ጭኑን ረግጦ ይገድለዋል፤በዚያ አካባቢ አባ ፊሎንዲስ የሚባል የበቃ ባህታዊ ነበር በመስቀል አማትቦ በክርስቶስ ስም ተነስ ይለዋል የሞተው ሰው ተነሳ፤ሁለተኛ ይኸው ባህታዊ መንገድ ሲሄድ ኤጲፋንዮስ ከኃላው ይከተለዋል አንድ ድሃ ቀርቦ ስመ እግዚያብሔርን ጠርቶ ምጽዋት ይጠይቀዋል የሚሰጠው ነገር ቢያጣ የለበሰውን ልብስ ( አጽፍ ) አውልቆ ሲሰጠው ወዲያውኑ ብርህት ልብስ ( አጽፍ ) ከሰማይ ሲወርድለት አየ፤ ከዚህ በኃላ ነው ኤጲፋንዮስ ቀርቦ አባቴ የሞተውን ሰው ያስነሳህበት አሀን ደግሞ ይህ ደሃ የክርስቶስን ስም ቢጠራብህ ልብስህን ስትሰጠው ከሰማይ ሌላ ልብስ የወረደለህ የኔ ዘመዶች ሩቅ ብእሲ ብለው ሰቅለው የገደሉት ክርስቶስ ነውን አለው አዎን ይለዋል አጥምቀኝ አለው አጠመቀው እንዳንተ መነኩሴ መሆን እፈልጋለሁ ይለዋል ካልክስ ብሎ ከሰው ተለይቶ በገዳም የሚኖር የበቃ አባት ነበር ኤላርዮስ ይባላል ወደ እርሱ ይልከዋል አመነኮሰው በተጋድሎም መኖር ጀመረ ትምህርት ታአምራቱም በተለያዩ አገሮች ተሰማ መናፍቃንን ተከራክሮም የሚረታ ሆነ ድውያንን የመፈወስ አጋንንትን የማውጣት ስልጣን ተሰጠው፤ ደግነቱን የተመለከቱ አባቶች የቆጵሮስ ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾመውታል በዚህ በሹመቱ ወራት ብዙ ድርሳናትን ተግሳጻትን ጽፏል፤ አንድ ቅዳሴም ደርሷል ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ የሚባል ይህ ቅዳሴ በተለይ በክረምት ወራት ቤተክርስቲያን የሚያዝወትሩ ከሆነ ደጋግመው ይሰሙታል ስለ ደመናት ስለ ነጎድጓድ ስለ ዝናብ በስፋት ይናገራል፤ ለጸሎተ ሐሙስም ይቀደሳል። ያ ደገኛ የተዋህዶ ኩራት ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ የድሃይቱን መበለት ርስት የነጠቀችውን ንግስት አውዶክስያን ከቤተክርስቲያን እንዳትገባ፤ እንዳትቆርብ፤ ከምዕመናን ጋር እንዳትገናኝ አውግዞ ሲለያት ለአባ ኤጲፋንዮስ መልዕክት ትልክበታለች ዮሐንስ አፈወርቅ ከግዝቱ ካልፈታኝ የአባቶቼን ዘመን እመልሳለሁ አብያተ ጣኦታት እንዲከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ክርስቲያኖች እንዲሰደዱ አዋጅ አስነግራለሁ አለችው አባ ኤጲፋንዮስ ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ሄዶ እንዲህ ብላለች ሴትዮዋ ሰይጣን አድሮባታል ከማድረግ ወደ ኃላ አትልም ከግዝቷ ፍታት ይለዋል፤ እርሷ የአባቶቿን ዘመን ብትመልስ እኔስ ብሆን ልጆቼስ ምዕመናን ቢሆኑስ እንደአባቶቻችን በሰማዕትነት መሞት ያቅተናልን፤ ያሻትን ታድርግ ለእርሷ ይብስባታል ከግዝቷ አልፈታትም ይለዋል፤ከዚህ በኃላ አባ ኤጲፋንዮስ ዮሐንስን ተሰናብቶ ወደ አገሩ ሊመለስ ሲል አገርህ አትደርስም ከመንገድ አንበሳ ሰብሮህ ትሞታለህ ይለዋል፤ አባ ኤጲፋንዮስም አንተም እንጂ መቼ መሞት ይቀርልሃል በደሴተ አጥራክያ ተግዘህ ተንገላተህ ትሞታለህ ይለዋል፤ አሁን ሁለቱ ተጣልተው አይደለም ክብራቸውን ሲገልጽ እንጂ አንዱ የአንዱ ሞት ተገልጾለት እንዲህ ተናገሩ፤ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለውም አባ ኤጲፋንዮስ መንገድ ላይ አንበሳ ገድሎታል ይህም ግንቦት 17 ቀን ነው ለ 40 ቀን አልተቀበረም የሚገርም መአዛ ግን ከስጋው ይወጣ ነበር ብዙ ድውያንም ተፈውሰዋል፤ዮሐንስ አፈወርቅም ንግስቲቱ በግዞት አሰቃይታ ገድላዋለች ይህም ግንቦት 12 ቀን ነው፤ ዮሐንስ አፈወርቅ ጠፍቶ የነበረውን የዮሐንስን ራእይ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ድጋሚ የጻፈው በዚህ በደሴተ አጥራክያ በግዞት ሳለ ነው። ከዮሐንስ ራእይ ውስጥ የዮሐንስ አፈወርቅ ቃል የሆነው ይህ ብቻ ነው “ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።” ዮሐ 22፤19። ከአባቶቻችን በረከት ያሳትፈን።

Thursday, May 23, 2013

ጻድቁ አቡነ አረጋዊ



እኚህ አባት ከተሰሐቱ ቅዱሳን (ከሮምና ኤሽያ ከመጡት ከ9 ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበር፡፡ እናታቸው ንገሰተ እደና ትባላለች፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳዊ ሲማሩ አድገው ወደ እሰከነድረያ ኮብልለው ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውነ አውቀው መዓርገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡
ንጉስ የሆኑ ቤታቸው የሞቀ ቤተ ሰቦቻቸውነ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አበምኔቱም ወደዚህች የሕየወት መንገድ ስለመራሀን ብፁህ አረጋዊ መባል ይገባሃልብለዋቸዋል፡፡ አረጋዊ የተባሉት ከዚያ ወዲህ ነው፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ መዐረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል። በገዳመ ዳውናስ 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሶ ሲያስተምሩየሀገራችንን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ480 ዓ.ም ከአባ ፍሪሚናጦስ ቦ|ላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በክነፉ ተሸክሞ አክሱ አድርሷቸዋል፡፡ ተመልሶ ሄደው ስለ ኢትዮጵያ ቅድስት ሀገር መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበውመነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱ ሁሉ ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ480 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ራሳቸውን ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡ አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀመዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረመንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደረሱ፡፡ ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር 90/91፡11-16 ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡
ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላች ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላ ግን ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡ ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ለሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት (የገዳም አባት ወይም አለቃ) ሾመውላቸው ጥቅምት አሥራ አራት ቀን በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ እንደሄኖክ እንደ ኤልያስ ተሰውሯል፡፡

በረከታቸው፣ ቃልኪዳናቸው፣ አማላጅነታቸው በሁላችን ይደር አሜን።

Sunday, May 19, 2013

ግንቦት 12







የአባታቸንና የኢትዮጵያ ፀሀይ የፃድቁ የተክለሀይማኖት ዐፅመ ፍልሰት ክብረ በዓል ግንቦት ፲፪ ከደብረ አሰቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ አጽማቸው የፈለሰበት(ፍልሰተ አጽም) በዓለ ንግስናቸው ይከበራል። ይህም ማለት አባታችን 29 ዓመት ቆመው ሲጸልዩ 7ቱን ዓመት ደግሞ ባንድ እግራቸው የጸለዩና አፅማቸው በደብረ አስቦ ከተቀበረበት ወጥቶ አሁን ደብረ ሊባኖስ ገዳም የተሰራበት ቦታ ጋር የፈለሰበት ታላቅ በዓል በተለይ በደብረ ሊባኖስ በታላቅ ሀይማኖታዊ ስርዓት ይከበራል። ካህናት፣መዘምራን ሊቃውንት ሌሊቱን በማህሌት፣ጠዋት በቅዳሴ፣በወረብና፣በዝማሬ፣በስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣መነኮሳት፣ካህናት፣ዲያቆናትና ከዋክብተ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

የፃድቁ የአባታችን የተክለሀይማኖት በረከት በሁላችን ላይ ይደር፤ አገራችን ኢትዮጵያን ደግሞ ከክፉ ይጠብቃት፤ አሜን!!!