Monday, December 30, 2013

ታህሳስ 22


ታህሳስ 22 በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ብስራተ ገብርኤል ይባላል፤ ይህም ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ ብስራቱን የነገረበት ቀን ነው፤ እንዴት ብስራቱንማ የነገራት መጋቢት 29 ቀን ካሉ ትክክል ነው፤ ብስራቱን የነገራት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው፡ ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ካሉ ምክንያቱ እንዲህ ነው፤ ምንግዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ፤ ታዲያ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ሰሩ የመጋቢት 27 ስቅለቱን ጥቅምት 27 ቀን እንዲሁም የመጋቢት 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍት ቀን ወደ ጥቅምት 5 ቀን ዞሮ እንዲከበር አደረጉ፡፡ የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅ ነው የእመቤታችንን ታአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡ የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው፡ የዚህ ታላቅ አባት እረፍቱ ታህሳስ 22 በዛሬዋ ቀን ነው፡ ከእርሱ በኃላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Friday, December 27, 2013

ታህሳስ 19


እንኩዋን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ:: ታህሳስ 19 በዚህች ቀን… ንጉሡ ናቡከደነፆር የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው ። ለወርቁ ምስል ሁሉም እንዲሰግድ እንዲንበረከክ አዘዘ ሁሉም ሰገደ ተንበረከከ ከእነዚህ ሦስት የልዑል እግዚያብሔር ብላቴናዎች በቀር ስማቸው ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎም ይባላል፤ ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሦስቱን ብላቴናዎች ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? እንግዲውስ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት ንጉስ ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ደግሞም ያድነናል! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን እንኳን አማልክትህን እንደናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት እና እሳቱ ይጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ፤ የዚያን ጊዜም እነዚህ ብላቴናዎች ከነልብሳቸው ከነመጐናጸፊያቸው ታስረው እሳት ውስጥ ተጣሉ። ናቡከደነፆር አሟሟታቸውን ሊመለከት ቆመ ወደ እሳቱም ተመለከተ አራት ሰዎችም በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ አየ ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም። ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው መለሱለት።እርሱም። እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። ይህም ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡ ናቡከደነፆር ድምጹን ከፍ አድርጎ ከእሳቱ እንዲወጡ ተጣራ የራሳቸው ጸጉር አልተቃጠለም ልብሳቸውም እንዲሁ ናቡከደነፆር ከዚህ በኃላ እንዲህ ሲል እግዚያብሔርን አመሰገነ “በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ” ትንቢተ ዳንኤል 3፡ 1- 30 ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡ 
 

Sunday, December 15, 2013

ታህሳስ 6


 በዚህች ቀን ታላቋ ሰማዕት የቅድስት አርሴማ ዓመታዊ በዓሏ ነው፤ ይህም ቅዳሴ ቤቷ የተከበረበት ነው ...በዚህም ቀን ታላላቅ ተአምራቶች ተደርገዋል፤ በተለይም ይህ ቀን በአገረ አርማንያ ልዩ ስፍራ አለው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ አስኮ ቃሎ ተራራ ላይ ግሩም ቤተክርስቲያን አላት ታዋቂው ገዳሟ ግን ወሎ ሲሪንቃ ይገኛል። መስከረም 29 በሰማዕትነት ያረፈችበት ነው፤ እነዚህን ሁለቱን ቀናት ቤተክርስቲያን በደማቁ ታከብራቸዋለች፤ሌላው በዛሬው ቀን ታላቁ አባት አብርሃም ሶርያዊው ያረፈበት ቀን ነው፤ ይህ አባት ተራራን ያፈለሰ ነው፤ ታሪኩ ወዲህ ነው አባ አብርሃም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ በነበረበት ወራት አንድ አይሁዳዊ ወደ ንጉሱ ገብቶ እንዲህ ይለዋል “እነዚህ ክርስቲያኖች የሚገርሙ ናቸው በወንጌላቸው ላይ የሰናፍጭ ቅንጣት እምነት ካላችሁ ይህንን ተራራ ተነቅለህ ወደዚያ ሂድ ብትሉት ይሆንላቹዋል ይላል፤” ይህ የሐሰት ወንጌል ነው፤ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ አንድስ እንኳን የለም ይለዋል” ንጉሱም አባ አብርሃምን አስጠርቶ “በእርግጥ ወንጌላችሁ እንዲህ ይላልን ?” ይለዋል አዋን ንጉስ ሆይ ብሎ ይመልስለታል፤ ታዲያ የክርስቲያኖች ሁሉ አባታቸው አለቃቸው አንተ ነህ እስኪ አድርግና አሳየኝ ይለዋል፤ እሺ ግን 3 ቀን ብቻ ይስጡኝ ብሎ ወጣ፤ ጨነቀው ወደ እምቤታችን ቤተክርስቲያን ገብቶ 3 ቀን 3 ሌሊት እህል ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ አለቀሰ፤ እመቤቴ አታሳፍሪኝ አላት፤ ተገለጸችለት ይህ ላንተ አይሆንም ግን ወደ ከተማ ውጣ በእንስራ ውሃ ተሸክሞ የሚሄድ ሰው ታገኛለህ፤ ስሙ ስምዖን ጫማ ሰፊ ነው፤ አንድ አይና ነው፤ አንዱን አይኑን ያጠፋው የልጄን ትዕዛዝ ለማክበር ብሎ ነው፤ ለእርሱ ይቻለዋል እርሱ የሚልህን አድርግ ትለዋለች፤ እንደተባለውም ስምዖንን ያገኘዋል፤ ነገሩን ሁሉ ይገልጽለታል፤ እሺ ለማንም ስሜንም ስራዬንም እንዳትገልጽቢኝ፤ ህዝቡን ሰብስብ እኔ በተሰወረ ቦታ ሆኜ የማሳይህን እየተመለከትክ አድርግ አንተ የምታደርገውን ደግሞ ህዝቡ ያድርግ አለው፤ ንጉሱም ሰራዊቱም ህዝቡም ይህንን ታአምር ለማየት ተሰበሰበ፤ 41 ጊዜ ኪራላይሶን ብለው ሶስት ጊዜ ሰገዱ፤ ከዚያም አባ አብርሃ ስምዖን የሚያሳየውን እየተከተለ መስቀሉን አውጥቶ ወደ ተራራው አማተበ፤ ተራራው ወደ ላይ ተነሰ፤ ታላቅ ፍርሃት ሆነ፤ ሶስት ጊዜ ተራራው ወደ ላይ እየተነሳ ይቀመጣል በተራራው ስር ከወዲያ ማዶና ከወዲህ ያሉ ሰዎች ይተያዩ ነበር ይላይ፤ ንጉሱም ህዝቡም እጹብ እጹብ አሉ ምስጉን እግዚያብሔርንም አመሰገኑ፤ ንጉሱ ክርስቲያን ሆኖ ተጠምቋል ብዙ አብያተክርስቲያናትንም አንጿል። አባ እብርሃምም ተፈርቶና ተከብሮ በቅድስናም ኖሮ በዛሬዋ እለት አርፏል። ከቅድስት አርሴማ፤ ከአባ አብርሃምና ከስምዖን ጫማ ሰፊ በረከታቸውን ያድለን። አሜን

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ታህሳስ 5

በዚህች ቀን ቅድስት አውጋንያ አረፈች፤ አገሯ እስክንድርያ ነው አባቷ አገር ገዢ ነበር ፊሊጶስ ይባላል ጣኦት አምላኪ ነው እናቷ ግን ደግ ክርስቲያን ነበረች በድብቅ ክርስትናን አስተማረቻት ስታድግ ታላላቅ መኳንንቶች አጯት እርሷ ግን ጠፍታ ወደ አባ ቴዎድሮስ ገዳም ገባች መነኮሰች ማንም ሰው እንዳያውቃት ፍጹም ወንድ መሰለች ስሟንም አባ አውጋንዮስ አሰኘች፤ አባቷ ጠፍታ መቅረቷን ባወቀ ጊዜ መሪር ለቅሶ አለቀሰ እሷን የሚመስል ጣኦት አስቀርጾ ማምለክ ጀመረ። ከአንድ ዓመት በኃላ ትጋቷን አይተው መነኮሳቱ የገዳሙ አበምኔት አድርገው ሾሟት፤ (አበምኔት ለወንድ እንደሆነ ልብ ይሏል) እግዚያብሔር በሰይጣናትና በድውያን ላይ ፍጹም ስልጣን ሰጣት ከብዙ አገር በሽተኞች እየመጡ በእጇ ይፈወሱ ነበር፤ ከእለታት አንደ ቀን ግን እንዲህ ሆነ አንዲት ሴት ቅድስት አውጋንያን ባየቻት ጊዜ ወንድ መስላት ፍጹም ወደደቻት፤ ምንኩስናህን ትተህ ባል ሆነከኝ ከኔ ጋር ኑር አለቻት፤ ሂድ አንተ ሰይጣን ብላ አባረረቻት፤ ባሳፈረቻት ጊዜ ወደ አገር ገዢው ሄዳ በዚያ ገዳም የሚኖር መነኩሴ ሊደፍረኝ ሲል አምልጬ መጣሁኝ አለችው፤ ዘፍጥረት 39 14 መኮንኑ በሰማ ጊዜ ተቆጣ ሁሉንም መነኮሳት ታስረው እንዲሰቃዩም አደረገ፤ የሞቱም አሉ፤ ቅድስት አውጋንያ ስቃያቸውን ባየች ጊዜ መኮንኑን ጌታዬ እውነቱን እነግርሃለው የምፈልገውን ነገር ግን አትከልክለኝ አለችው፤ አስማለችውም፤ ከዚያም ልጁ አውጋንያ እንደሆነች ገለጸችለት፤ አንገቷን አቅፎ አለቀሰ፤ እኔም ባንቺ አምላክ አምናለው አላት ከነቤተሰቦቹም ተጠመቀ የበቃ ታላቅ አባት እስከመሆን ደርሶ በሰማእትነት ነው የሞተው እርሷም ወደ ሮም ሄዳ የገዳም እመምኔት ሆና ለብዙ ዘመናት ለረጅም ወራት በተጋድሎ ኖራ ታህሳስ በባተ በአምስተኛው ቀን አረፈች፤ በረከቷ ይደርብን ከጻድቁ አቡዬ በረከታቸውንም ያሳትፈን።
LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Friday, December 13, 2013

ታህሳስ 4

 
በዚህች ቀን የሊቀ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም የተመሰገነ ቅዱስ እንድርያስ በሰማዕትነት አረፈ፤ የዚህ ሐዋርያ ቁጥሩ ከ 12ቱ ሐዋርያት ነው፤ ማቴ 4፤ 18 ቀድሞ በገሊላ ባህር ማዶ በቤተሳይዳ ዓሳ አጥማጅ ነበር፤ ሰውን ታጠምዳለህ ብሎ ጌታ ጠራው ተከተለው። ዓለምን ዞረው ለማስተማር ዕጣ ሲያወጡ ለቅዱስ እንድርያስ ልዳ ደረሰችው ልዳ ማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ አገር ናት፤ ሊያስተምር ወደዚያች አገር ገባ፤ ጣኦት አምላኪዎች ወሬውን ሰምተው ሊጣሉት ሾተል ይዘው ወጡ፤ ሐዋርያው እንድርያስ ግን ከፍ ካለ ቦታ ላይ ቆሞ እንዲህ ሲል ሰበከ " የአህዛብ ጣኦታት የሰው እጅ ስራ ናቸው ዓይን አላቸው አያዩም፤ ...ጆሮ አላቸው አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸቱም፤ እጅ አላቸው አይዳስሱም፤ እግር አላቸው አይሄዱም በጉሮሮአቸውም አይናገሩም የሚሰሯቸው የሚያምኑባቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሆናሉ፤ መዳን በእግዚያብሔር ነው እርሱም እየሱስ ክርስቶስ ነው እያለ ሰበከ” ከቃሉ ጣዕም ከአንደበቱን ቅልጥፍና ከነገሩ ማማር የተነሳ የወገባቸው ትጥቅ ተፈታ ሾተላቸውን ጣሉ፤ በጌታችን አምነው ተጠመቁ ይላል። ይህ ሐዋርያ በሰው ቋንቋ የምትናገር የምትላላከው እርግብ ነበረች፤ ተረፈ ኤርሚያስ 10፤24 ዘፍጥረት 8፤ 8 በነዚህ ጥቅሶች ኖህ ከርግብ ባሮክ ከንስር ጋር በሰው ቋንቋ ሲነጋገሩ ሲላላኳቸውም እናያለን፤ ሐዋርያው እንድርያስ ከእርግብ ጋር ሲነጋገር ህዝቡ ይገረም ነበር። ይህ ሐዋርያ በዛሬዋ እለት ግብራቸው እጅግ ወደ ከፋ አገረ ሰዎች ገብቶ ሲያስተምር አሰቃይተው ገድለውታል። በረከቱ ይደርብን

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Monday, December 9, 2013

ታህሳስ 1


እነሆ የተባረከ የታህሳስ ወር ባተ፤ ይህ ወር ቀኑ 9 ሰዓት ነው ሌሊቱ 15 ሰዓት፤ ቀኑ በጣም አጭር ነው ቶሎ ይመሻል ሌሊቱ በጣም ረጅም ነው፤ ታህሳስ 1 በዚህች ቀን በገለዓድ ይኖር የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ የተወለደበት ቀን ነው፤ ታሪኩ 1ኛ ነገስት 17፤1 ላይ በስፋት ይገኛል፤ በእሳት ሰረገላ የተሰወረው ጥር 6 ቀን ነው፤ እነዚህን ሁለት ቀናት ቤተክርስቲያን ነብዩን አስባ ትውላለች፤ ይህ ነብይ በአገራችን በስሙ የታነጹለት አብያተክርስቲያናት አሉት ከነዚህም በመዲናችን አዲስ አበባ ርዕሰ አድባራት እንጦጦ ደብረ ሐይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፤ ኤርትራ ውስጥም አንድ ቤተክርስቲያን አለው፤ ዛሬ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ አክአብና ኤልዛቤል ምሰኪኑን ናቡቴ ከአባቶቹ እርስት አፈናቅለው በግፍ በገደሉት ጊዜ፤ ንጉሱን ሳይፈራና ሳያፍር በግልጽ የዘለፈ ነብይ ነው፤ ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይንም የለጎመ ነው ይህንንም ያዕቆብ በመልእክቱ እንዲህ ሲል መስክሯል ያዕ 5 ፤ 16 "የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች"
ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Friday, December 6, 2013

ህዳር 29


በዚህች ቀን ተፍጻሚ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አረፈ። በዚህች ሴት ታሪክ እንደርደር ሳራ ትባላለች አገሯ አንጾኪያ ነው ደግ ክርስቲያን ነች ጣኦት አምልኮ በተስፋፋበት ወራት ሁለት ልጆች ወልዳ ነበር የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው ግን አልቻለችም ምነው ቢባል ካህንም ቤተክርስቲያንም ከዚያች አገር ተሰደው ነበርና፤ እስክንድርያ ወስጄ ላስጠምቃቸው ብላ መርከብ ተሳፍራ ጉዞ ጀመረች፤ ታላቅ ሞገድ ተነሳ መርከቧ ልትገለበጥ ደረሰች በዚህ ጊዜ ልጆቼ ሳይጠመቁ ሊሞቱ ነው ብላ ፈራች፤ምላጭ አውጥታ ጡቷን ሰነጠቀች በደሟም የልጆቿ ግንባር ላይ መስቀል እየሰራች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ብላ አጠመቀቻቸው፤ወዲ...ያውኑ ወጀቡ ማዕበሉ ጸጥ አለ እስክንድርያ በሰላም ደረሱ ወደ ሊቀ ጳጳሱ ገባች የዚህ አባት ስም ተፍጻሜ ሰማዕት ጴጥሮስ ይባላል፤ ልጆቿን ሊያጠምቅ ወደ ጸበሉ ሲጠጋ ጸበሉ እንደ ሰም ይረጋል፤ ሌሎች ህጻናት ሲመጡ መፍሰስ ይጀምራል ለሁለተኛ ጊዜ ልጆቿ ሲመጡ ጸበሉ እንደ ሰም ይረጋል ሶስት ጊዜ እንዲሁ ሆነ ነገሩ ምንድን ነው ብሎ ጠየቃት የሆነውን ሁሉ ነገረችው፤ በጣም ተደነቀ እግዚያብሔርንም አመሰገነ ይላል። ተፍጻሜ ሰማዕት ጴጥሮስ 3 ደቀ መዛሙርት ነበሩት አርዮስ፤አኪላስና እለእስክንድሮስ ይባላሉ፤ ለአርዮስ ክህነት ሰጥቶ የሾመው ይህ አባት ነው፤ ምን ዋጋ አለው አርዮስ አጥብቆ ተመራመረ ወልድ ፍጡር ነው ብሎ ወደቀ፤ ይህንንም በድብቅ ለሰው ማስተማር ጀመረ፤ በዚህ ጊዜ ጌታችን ለተፍጻሚተ ሰማዕት ጴጥሮስ የተቀደደ ልብስ ለብሶ ተገለጸለት አንተ ማን ነህ ይለዋል የናዝሪቱ እየሱስ ነኝ ታዲያ ልብስህ ለምን ተቀደደ ይለዋል “አርዮስ ሰጠጣ ለልብስየ” ይለዋል አርዮስ ልብሴን ቀደደው ማለት ነው፤ ከባህሪ አባቴ ከአብ ከባህሪ ህይወቴ ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ ፍጡር ነው አለኝ ይለዋል፤ ይህን ራዕይ እይቶ ብዙም ሳይቆይ አርዮስ መጣ ቁጭ አድርጎ መከረው “በልብህ ያለውን ኑፋቄ ካሰብክ እንዳትናገር ከተናገርክ እንዳትደግመው ብሎም ያስጠነቅቀዋል፤ ሊሰማው ግን አልቻለም፤ አውግዞ ይለየዋል፤ ጓደኞች አኪላስና እለእስክንድሮስ ሊማልዱለት ይመጣሉ፤ አባታችን አርዮስ ተመልሻለው እያለ ነው ከግዝቱ ፍታው ይሉታል፤ እርሱም እንደማይመለስ ጌታ በራዕይ ነግሮኛል አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ደርሷል ከኔ በኃላ አኪላዎስ ሊቀ ጳጳስ ትሆናለህ ጓደኝነት በልጦብህ አርዮስን ከግዝቱ ትፈታዋለህ ነገር ግን ብዙ አትቆይም ትሞታለህ ብሎ ትንቢት ይነግራቸዋል፤ የእረፍቱ ቀን እንደደረሰም አውቆ “ጌታ ሆይ የኔን ሞት የሰማእታት መጨረሻ አድርግሊኝ ከኔ በኃላ የእንድስ እንኳን ሰማእት ደም እይፍሰስ” ብሎ ጸለየ፤ህዳር 29 ቀን የዲዮቅልጥያኖስ ጭፍሮች አንገቱን ቆርጠው ገድለውታል፤ለዚህም ነው ቤተክርሰቲያን “ተፍጻሚ ሰማዕት ጴጥሮስ” ብላ የምትጠራው የሰማእታት መጨረሻ ማለት ነው፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን።