Thursday, July 3, 2014

ሰኔ 8


ከእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላት አንዱ ነው፤ በዚህ ዕለት ልጇ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ግብጽ በስደት ሳሉ ለህሙማን ድህነት እንዲሆን ውኃን ከዓለት ላይ ያፈለቀበት ቀን ነው፤በዚሁ ቦታ በእመቤታችን ሥም ታላቅ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ የተከበረበትም ቀን ነው፡፡እመቤታችንን ከፍጥረት ዓለም ለይቶ አክብሮ የእናት አማላጅ አድርጎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፡፡
ከተአምር አስቀድሞ ይህ ይነበብ ህዝቡ ዕዝነ ልቦናቸውን ከፍተው ይስሙ፤ በዕብራይስጥ ማርያም የተባለች የእመቤታችንን ተአምር ለመስማት ቀላል አይምሰለው የከበረ ገናና ነውና ወደ ግዝት እንዳይገቡ መስማትን አያስታግሉ ፤ በእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላትና እሁድ በተባለች ሰንበት ወንዶችም ሴቶችም ወደ ቤተክርስቲያን ይሰብሰቡ የተአምሯን መጽሐፍም ያንብቡ፤ ዛሬ ሰኔ 8 ቀን ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ ይህም በስደታቸው ወራት ልጇ ከደረቅ አለት ላይ ውኃን ያፈለቀበት ቀን ነው። ይህ ውኃ እንደ ማር እንደ ወተት የጣፈጠ እንደ ወተትም የነጻ ነው፤ ከዚህ ውኃ የጠጣ ሁሉ ይፈወስ ነበር። ታሪኩ እንዲህ ነው የግብጽ በረሃ በጣም ሲያደክማቸው ከአንድ መንደር ያርፋሉ በዚያም ጌታ ውኃ ይጠማዋል ይህን ባየች ጊዜ እምቤታችን ከመንደሩ ሴቶች ውኃ ልትለምን ሄደች፤ ዮሴፍና ሶሎሜ ግን ደከሟቸው ተኝተው ነበር፤ ውኃ የሚሰጣት የሚመጸውታት ስታጣ ልቧ በሐዘን ተወግቶ ተመልሳ መጣች ጌታን ከተቀመጠበት አንስታ ታቀፈችው ስቅስቅ ብላም አለቀሰች ህጻን ጌታም የእናቱን እንባ ከጉንጮቿ ላይ በእጆቹ ጠረገላት ትንሽዬ ጣቱን (ማርያም ጣት የምንለውን ነው ወደ ምድር አመለከተ ወዲያውኑ ጣፋጭ ውኃ ከአለት ላይ ፈልቆ ጠጡ፤ እንዲህም አለ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ለድህነት ይሁነው ብሎ ባረከው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚጠጣው ሁሉ ከደዌው ይፈወስ ነበር፤ አሁንስ ይኖር ይሆን ? እንጃ፤ የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂያችንን የወለድሽልን እመቤቴ ማርያም ሆይ ሠላምታ ይገባሸል የሄዋን ጽኑ የሚጎዳ ማሰሪያዋ ባንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ውዳሴም ይገባሻል እኛ ከምንወደው እርሱም ከሚወደን ልጅሽ ይቅርታ ያደርግልን ዘንድ ለምኝልን።

LIKE OUR PAGE >>>

Monday, June 9, 2014

እንኳን አደረሳችሁ, ለጦመ ሐዋርያት በሰላምና በጤና አደረሰን:

እንኳን ለጦመ ሐዋርያት በሰላምና በጤና አደረሰን:


LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

በዓለ መንፈስ ቅዱስ/ጰራቅሊጦስ

በዓለ መንፈስ ቅዱስ/ጰራቅሊጦስ

ምንም እንኳን የዕለታትና የዘመናት ሁሉ ባለቤት እርሱ እግዚአብሔር ቢሆንም በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ነገር ሁሉ በሥርዓት ይሁን ብሎ ሐዋርያው እንዳስተማረን በቤተክርስቲያናችን የበዓላት ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ በኋላ ፶ኛው ቀን በዓለ ጰራቅሊጦስ/በዓለ ሃምሳ/በዓለ ጰንጠቆስጢ ወይንም የቤተክርስቲያን የልደት ቀን በመባል ይታወቃል ወይንም ይከበራል። በግሪክ ቋንቋ ጰራቅሊጦስ ማለት አጽናኝ ማለት ነው።

መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ሲሆን ከአብ የሰረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮት በስልጣን በአገዛዝ በመሳሰሉት እኩል ወይንም አንድ ነው። እንደ እግዚአብሔር አብ እና እንደ እግዚአብሔር ወልድ(ኢየሱስ ክርስቶስ) መንፈስ ቅዱስ በራሱ የተለየ አካልና ግብር አለው። ዮሐ.፲፭፥፳፮። መንፈስ ቅዱስ ከዘመናት አስቀድሞ ከአብና ከወልድ ጋር ዓለማትን የፈጠረ ነው። ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር ፴፪፥፮ ላይ <በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ> ሲል ተናግሯል።

መንፈስ ቅዱስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን አላማ አበክሮ የሚገልጽና ጌታችንም ወደ ቀደመ ክብሩ በምስጋናና በእልልታ ካረገ በኋላ በ፲ኛው ቀን ለሐዋርያት ጸጋውን በማፍሰስ የተገለጸ የቤተክርስቲያን ጠባቂና መሪዋ፤ በእግዚአብሔር ልጅ ያመኑትንና በስሙ የተጠሩትን ክርስቲያኖች የሚያጽናና፣ በኃይማኖት በምግባርና በተጋድሎ የሚያጸና፣ ጥበብንና ማስተዋልንም የሚያድል ነው (ኢሣ.፲፩፥ ፪)። ክርስቲያኖች ከጌታ የተማሩትን መልካም የሆነውን የጽድቅ ሥራ እንዲሠሩ ዘወትር በልቦናቸው አድሮ የሚያሳስብ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። <አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔ የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል> ዮሐ. ፲፬፥፳፮ በማለት ሐዋርያት/ክርስቲያኖች በሚሠሩት ሥራ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደማይለያቸው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል።

መንፈስ ቅዱስ በእምነት ጸንተው በጸሎት ለሚተጉ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚሰጥ ኃብት ነው። በተለይም በአንድ ልብ ሆኖ በኅብረት በሚደረግ ጸሎት ምልጃና ጉባዔ መንፈስ ቅዱስ በቶሎ ይሰጣል/ይወርዳል/ይገኛል፤ ለሁሉም እንደ ችሎታውና እንደ አቅሙም ፀጋንና ስጦታን ያድላል። <በዓለ ኀምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበረበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው
በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር> ሐዋ.ሥ. ፪፥ ፩-፬

መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ሰዎች መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠሩና ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር እንዲስቡ እነርሱም በረከትን እንዲቀበሉ ነው። ይህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ልዩ ልዩ እነደሆነ ሐዋረያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ በማለት ዘርዝሮታል፦ የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው አሠራርም ልዩ ልዩ ነው ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ ለአንዱም ትንቢትን መናገር ለአንዱም መናፍስትን መለየት ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። (፩.ቆሮ.፲፪፥፬-፲፩)

እዚህ ላይ በተለይ በልሳን የመናገር ስጦታ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ልሳን ማለት በአንደበት የሚነገር ትርጉሙንም ቋንቋው ሲነገር የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የሚረዱት የሰው ልጆች ልሳን/ቋንቋ ነው። አንዳንዶች የተለየ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች የማይረዱትን ነገር እንደሚያውጡት ያለ ድምጽ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። በዚህ የተታለሉ እኅቶችና ወንድሞች አሉና። ሐዋርያት በልሳን በተናገሩ ጊዜ በዙሪያቸው የነበሩ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች የእነርሱን ሃገር ልሳን/ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተው ተገረሙ ነው የሚለው ቅዱስ ሉቃስ ( ሐዋ.፪ ፥፭-፲፫ )

ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዋናው ምክንያት ሐዋርያት ዓለምን ዞረው አሕዛብን ሁሉ በየቋንቋቸው በማስተማር የክርስቶስ መንግሥት ተካፋይ እንዲሆኑ ዕድል ፈንታ ይኖራቸው ዘንድ ነው። ሌላው በእምነትና በጽናት ተስፋ ለሚያደርጉት ሁሉ ሳይሳሳ በልግስና የሚሰጥ ቸር አምላክ መሆኑን ሲያስተምረን ነው። በዮሐንስ ወንጌል ፫፥ ፴፬ ላይ <እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና> ተብሎ እንደተጠቀሰው። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ <ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም> ዮሐ.፲፬፥፲፰ ያለውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው።

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ ሲባል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ሥጋ ለብሶ እንደተገለጸው ያለ አገላለጽ ሳይሆን ጸጋውን አደላቸው ማለት ነው። እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከደሟ ደምን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ እግዚአብሔርን አሳይቶናል፤ አይተነዋል። ለዚህም <...እኔን ያየ አብን አይቷል...> ዮሐ.፲፬፥፰ ብሎ በቅዱስ ቃሉ በሕገ ወንጌሉ አስተምሮናል። መንፈስ ቅዱስ ግን የማይታይ የእውነት መንፈስ ነው። የሚታየው/የሚገለጸው በሚያሠራው በጎ ሥራ ነው። ዘወትር በምንሠራው የጽድቅ ሥራ ወይንም በደልና ኃጢአትን በሠራን ጊዜም በውስጣችን ሆኖ ሲወቅሰን መንፈስ ቅዱስ ከኛ ጋር እንዳለ እናውቃለን። <እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለም ከእናንተ ጋር እንዲሆን ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሰጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ> ዮሐ.፲፬፥፲፭-፲፯።

መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖች በድፍረት የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት እንዲመሰክሩ የሚያደርግ ነው ፩ቆሮ. ም.፲፪፥፫ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት መመስከር ሲባልም በዘመናችን እንደምንሰማውና እንደምናስተውለው በብዙ ክሕደት ውሰጥ ሆኖ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን የእርሱን አምላክነት በማመን ጌትነቱ አምላካዊ የሆነና እርሱ ራሱ ምልጃን ተቀባይ እንጂ አማላጅ እንዳልሆነ በማመን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ክርስቲያኖችም ዘወትር በተሰጠን ፀጋና ችሎታ ቤተክርስቲያንን፣ ሌሎች ወንድሞችና እኅቶችን፣ ኅዙናንን ማገልገል ባጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ተብለው በሐዋርያው በቅዱስ
ጳውሎስ የተማርነውን ለመፈጸም መትጋት ይኖርብናል። እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የተባሉትም ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ናቸው (ገላ.፭፥፳፪-፳፫)። መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ሲባልም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን በ፵ እና በ፹ ቀን በጥምቀት የተቀበልነውን ነገር ግን በውስጣችን ተዳፍኖ ያለውን መንፈስ በበጎና በጽድቅ ሥራ መቀስቀስ ማለት ነው ። አንዳንድ የዋሃን እንደሚሉት አዲስ መንፈስ እስኪወርድልን እንደ ሐዋርያት በአንድ ቦታ ተሰብስበን ቤት ዘግተን እንቀመጥ ማለት እንዳልሆነ ልናውቅ ያስፈልጋል። እርሱም የሚያረጋጋና የሚያስደስት እንጅ የሚያስገዝፍና የሚያስጮህ እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባናል ።

ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ሥራውን በኛ ላይ እንዲሠራ በሃይማኖት ጸንተን ራሳችንን ከክፉ ገነር በማቀብ እንድንኖር ያሻል። የያዕቆብ ወንድም ይሁዳም በመልዕክቱ እንዲሁ እንድናደርግ ነው የሚያሳስበን <እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለያችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ> ይሁዳ ፩፥፳። በቤተክርስቲያናቸን ትምህርት መሠረት መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው /የወረደው በተለያዩ ምሳሌዎች ነው። በሰው ተመስሎ የተገለጸበት ጊዜ አለ (ዘፍ. ፲፰፥፩) ፣ በርግብ ተመስሎ የወረደበት ጊዜ አለ (ማቴ. ፫፥፲፮)፣ በእሳት የተመሰለበት ጊዜ አለ (ሐዋ.፪፥ ፫፤ ማቴ. ፫፥፲፮)ስለሆነም ዘመናችን ብዙ የሐሰት ትምህርት የሞላበት በተለይም መንፈስ ቅዱስ ወረደልኝ፤ ይወርድልሃል፤ ይወርድልሻል፤ በሚል ማጭበርበርና ማደናገር ብዙዎች ከእውነት የተለዩበት በሐሰት መንፈስ የተወሰዱበት በመሆኑ እውነተኛውን መንፈስ ከሐሰተኛው መንፈስ ለይተን እንድናውቅ ያስፈልጋል። 

በመጨረሻም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን>ብሎ በ፪ኛ.ቆሮ.፲፫፥፲፬ ላይ አንድ እንሆን ዘንድ በኃይሉ እንዲያበረታን እንደጸለየልን እውነትን አውቀንና ተረድተን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያስተማረችንንና የምታስተምረን ተገንዝበን እንድንኖር እርሱ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር

Source: ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ሰ/ት/ቤ/ት/ክ

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 28

ግንቦት 28 በዚህች ቀን ዓለምን ንቃ የተወች ገዳማዊቷ ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ አረፈች። በበርሃ የሚኖረው አባ ዳንኤል ስለዚህች ሴት እንዲህ አለ፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን በጨረቃ ብርሃን በርሃውን አቋርጬ ስጓዝ ተራራ ላይ የተቀመጠ ሰው አየው ግርማው ያስፈራል መላ ሰውነቱን ጸጉር ሸፍኖታል ሰው ይሁን መንፈስ ልረዳ ቀረብኩት እርሱ ግን እንደተመለከተኝ ሮጦ የተሰነ...ጠቀ አለት ውስጥ ገብቶ ተደበቀ፤ ሰው እንደሆነ አወቅኩኝ፤ አባቴ በረከትህን እሻለሁና ወደ ዋሻው አስገባኝ ብዬ ለመንኩት፤ እርሱ ግን ወደኔ መግባት አይቻልህም አለኝ፤ የሴት ድምጽ ነው፤ ለምን አለኳት፤ እርቃኔን ነኝ አለችኝ፤ የለበስኩትን አጽፍ አኖርኩላት እርሱን ለብሳ ወጣች፤ ታሪኳን ሁሉ ነገረችኝ፤ በዘንቢል ሽንብራ በኮዳ ውኃ ይዛ ከወላጆቿ ቤት እንደወጣች ለ 38 ዓመት በኤርትራ በርሃ ሰው ሳታይ ብቻዋን በተጋድሎ እንደኖረች ነገረችኝ እኔም ጻፍኩት ይለናል፤ ይህች ቅድስት እናት ኢትዮጰያዊት እንደሆነች የትውልድ ቦታዋም ሸዋ ውስጥ ተጉለት እንደሆነ በአገራችን አንድ ገዳም እንዳላት ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ "የኢትዮጰያ ተወላጆች ቅዱሳን" በሚል መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፤ ስንክሳሩም ሰርቶላታል፤ ግንቦት 28 በዛሬዋ ቀን እረፍቷ ነው። በረከቷን ያድለን።

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 26

ግንቦት 26 
በዚህች ዕለት ዲዲሞስ የተባለው ሐዋርያው ቶማሰ አረፈ፤ እርሱም በላይንደኬ በዛሬዋ ህንድ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳመነ በዚህም መኮንኑ ተቆጥቶ ጽኑ ስቃይ አሰቃየው ቆዳውንም ገፈፈው፤በሰውነቱም ላይ ጨውና ቆምጣጣ አፈሰሱበት፤ይህንን ሁሉ ታገሰ፤በተገፈፈ ቆዳው ስምንት ሙታን አስነሳ ብዙ ገቢረ ታአምራትን አደረገ፤ይህንን አይተው መኮንኑን ጨምሮ ብዙዎች አመኑ።ከዚህ በኃላ በአቴናና መቄዶንያ ገብቶ ሰበከ ንጉሱም ይዞ አሰቃየው በመጨረሻም በጦር ተወግቶ በዛሬዋ ዕለት በሰማዕትነት አረፈ። የጌታን ጎን የዳሰሰች የሐዋርያው ቀኝ እጅ ተአምራትን እያደረገች እስከ ዛሬ በህንድ አለች፤
በረከቱ ይደርብን

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 24

ግንቦት 24

 በዚህች ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን እግዚያብሔርን ይዛ ከዮሴፍና ከሶሎሜ ጋር ወደ ግብጽ የተሰደዱበት ቀን ነው፤ ይህን ቀን ቤተክርስቲያን በደማቁ አክብራው ትውላለች፤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ቤተክርስቲያን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። “እነሆ፥ የጌታ መል...አክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ማቴ 2፤13 በስደት የቆዩት ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ነው የእመቤታችን ስደት ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከት ነው የጣና ደሴቶችን የዋልድባ ገዳምን አክሱምና የትግራይ አውራጃዎችን፤ ድብረ ዓባይና የጎጃም ታላላቅ ገዳማትን በርካታ የኢትዮጵያ አውራጃዎችን በኪደተ እገራቸው ባርከውታል ቀድሰውታል።፤ “የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ አለ ነብዩ ዕንባቆም፤ ዕንባቆም 3፤7። ነብዩ ምን ማለቱ ነው ? መቼ ነው የኢትዮጰያ ድንኳኖች የተጨነቁት ? እመቤታችን በስደት ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣም እይደል። ግን ግን ስደቷ ግንቦት 24 ከሆነ ለምን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን የጽጌ ጾም ብለን ስደቷን እናስባለን ካሉ፤ይህ ሊቃውንቱ የሰሩት ስርዓት ነው፤ ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 25 በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ዘመነ ጽጌ ይባላል የአበባ የልምላሜ ወቅት ነው፤ እመቤታችን ደግሞ በአበባ ትመሰላለች አበባ የፍሬ እናት ነው፡፡ እመቤታችንም የተባረከ ፍሬ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርሰቶስን ያስገኘች አማናዊቷ አበባ ናት፡ ስለዚህም ይህን የስደቷን ወራት በዘመነ ጽጌ ባሉት 40 ቀናት ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን ታስቦ እንዲውል የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስርዓትን ሰሩ። 
እግርሽ ጨረቃን የሚጫማ 
በአሸዋ ስትሮጪ እግርሽ ደማ
ውቅያኖሶቹ ግራ ቀኙ የሚሰፈሩት በእፍኙ
ለእርሱ ለእርሱ ለዝናብ ጌታ ውኃ ነሱ።
ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

እንኳን ለጌታችን ለመድሐኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የእርገት በዓል አደረሳችሁ !!!



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አ፩ዱ አምላክ አሜን

“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)
ዕርገት

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ
የትንሣኤያችን በኩር የሆነው ጌታ በመቃብሩ ቦታ
- ለማርያም መቅደላዊት እና ለሌሎችም ሴቶች (ማቴ 28÷1 የሐዋ 2÷1)፡፡
- ለኤማውስ መንገደኞች( ሉቃ 24÷13)
- ለደቀማዛሙርቱ በተዘጋ ቤት (ዮሐ 20÷8)
- በጥብርያዶስ ባህር ለደቀመዛሙርቱ ዮሐ 21÷4 
ሥርዓትን እያስተማረ አልፎ አልፎም በግልጥ እየታየ ፍርሐታቸውን እያስወገደ አይሁድ እንደሚሉት ሥጋውንም ደቀመዛሙርቱ እንዳልሰረቁት ይልቁንም በሞት ላይ ሥልጣንኑን አሳይቶ መቃብሩን ባዶ አድርጐ በትንሣኤው አለት ላይ ያቆመን፣ ሞት በእርሱ እንደተሸነፈ የማይታየው እየታየ፣ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ዘላለማዊ ጌታ የማይዳሰሰው እየተዳሰሰ ለ40 ቀናት ያክል ቆይቶ ተከታዮቹን ሐዋርያትን ወደቢታንያ አወጣቸው፡፡ እያዩት በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ፡፡ እንዲህ ተብሎ በነብዩ ዳዊት እንደተፃፈው፡- “ዐረገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ” እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ፣ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፣ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ (መዝ 46÷5)

አምላካችን ወደሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀመዛሙርቱን ምን አዘዛቸው?

1. ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡ (ሉቃ 24÷48) ደቀመዛሙርቱ ያዩትንና የሰሙትን ሞትን አሸንፎ የተነሣውን ጌታ ለዓለም ሁሉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የዓላውያንን ነገሥታት፣ የቄሳሮችን ዛቻና ማስፈራሪያ አንዳችም ሳይፈሩ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ ድረስ ሁሉን እያጡና መከራ እየተቀበሉ፣ እየታሰሩና እየተገረፉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ በኋላ ስሙን አትጥሩና በስሙም አታስተምሩ እያሏቸው በሸንጐ ፊት ሲያቆሟቸው፣ ሲገርፏቸው ደስ እያላቸው ከሸንጐ ፊት ይወጡ ነበር፡፡ (የሐዋ 5÷40)፡፡ ስለ ስሙ ምስክር መሆን መነቀፍና መታሰር፣ መደብደብ እንዴት ደስ ይላል!፡፡ እኛም እንደ ደቀመዛሙርቱ ማንንም ሳንፈራ አፋችንን ሞልተን ስለ ስሙ እየመሰከርን ሁሉን ብናጣም ሞታችንን በሞቱ ድል የነሣልንን የሚቃወመንን ጠላታችንን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያስወገደልንን፣ እረፍትና ሰላም የሰጠንን፣ ጨለማውን ገፎ ብርሐንን ያጐናፀፈንን፣ ያለፈውን ታሪካችንን በነበር ላስቀረልን ምስክሮች እንሁን፡፡

2. አጽናኙን እልክላችኋለሁ (ዮሐ 15÷26)፡-
- በአህዛብና በዓላውያን ነገሥታት ፊት ሲቆሙ እውነትን እንዲናገሩ የሚያፅናና ኃይል፣
- ከተዘጋ ቤት ወደ ሠገነት እንዲቆሙ የሚያደርግ ኃይል፣
- ልበ ሙሉ ሆነው ከጥርጥር ወደ ፍፁም እምነት፣ ከፍርሃት ወደ ድፍረት እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ አጽናኝ ኃይል እልክላችኋለሁ፡፡
ይህ ኃይል በዘመናችን በጣም ስለሚያስፈልገን በፍፁም መዘንጋት የለብንም፡፡ እውነትን ለመናገርና ለመመስከር፣ ፍርሐታችን እንዲወገድልን ከፈለግን ይህንን ኃይል ዓለም ሳይሆን የሚሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን አውቀን ጌታ ሆይ እኔን ልጅህ ያንተን ኃይል አጥቼ ደክሜያለሁ፣ ከእኔ የሆነ ኃይል ምንም የለምና ከእኔ አትራቅ፡፡
- ባስልኤልንና ኤልያብን በጥበብ መንፈስ የሞላህ (ዘፀ36÷2)
- ሶምሶንን በጾርዓና በኤሽታኦል ያነቃቃህ (መሳ 14÷18)
- ለደቀመዛሙርቱ ኃይልህን ልከህ 71 ቋንቋ የገለጥክ፣ በየዘመናቱ የተመረጡ አገልጋዮችህ ያፅናናህ፣ የእውነትን ቃል እየላክ ያበረታታህ እኛም እንድንበረታ ኃይልህን ከአርያም ላክልን፣

3. በኢየሩሳሌም ቆዩ (ሉቃ 24÷49)፡- ደቀመዛሙርቱ ከቢታንያ ወደ
ኢየሩሳሌም ተመልሰው በአንድ ልብ ሆነው በኢየሩሳሌም ቀዩ፡፡ በመቆየታቸውም
ሰማያዊ ኃይል አገኙ፡፡
እኛ ሰማያዊ ኃይል ለማግኘት የት እንቆይ?
- በኢየሩሳሌም ቤተክስቲያን መቆየት ያስፈልገናል፣
- በአንድ ልብ ሆነን በቤታችን፣ በአገልግሎታችን፣ በዘር፣ በጐሣ ሳንከፋፈል ይኸ እንዲህ ነው፣ ያ ደግሞ እንዲህ ነው ሳንል ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን የወጣንም እንመለስ፣
- ሰዎች ባይመቹንም፣ ክፉዎች ልባችንንን ቢያቆስሉንም፣ ሰዎች እንጂ ያልተመቹን ክርስቶስና ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ይመቹናል፡፡ ስለዚህም ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን አንውጣ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየበላንና እየጠጣን፣ እያገለገልን፣ ያደግንባት የእኛ ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያናችን ብናዝን የምንጽናናባት፣ አእምሮአችን የሚያርፍባት፣ ሰላም የምናገኝባት ኢየሩሳሌም ቤትክርስቷያናችን ናት፡፡

ማጠቃለያ

አምላካችን የማዳን ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለተከታዮቹ ደቀመዛሙርት ምስክሮቼ ናችሁ፡፡ አጽናኙን እልክላችኋለሁ፡፡ “አንትሙ ንበሩ በሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ሃይለ እማርያም፡፡ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ አዘዛቸው፡፡

በመጨረሻም ወደሰማይ ሲያርግ እጆችንም አንስቶ ባረካቸው፡፡ (ሉቃ 24÷51)
በብሉይ ኪዳን ተፅፎ እንደምናገኘው፡- አባታችን አብርሃምን ባርኮ ያበዛ(ዘፍ12÷1)፣ ያዕቆብን በያቦቅ ወንዝ ሲባረክ ያደረ (ዘፍ35÷9)፣ ያቤጽን ባርኮ ሀገሩን ያሰፋ(1ኛ ዜና 4÷9)፣ አምስቱን እንጀራ፣ ሁለቱን ዓሣ አብዝቶ የባረከ ጌታ ዛሬም በኑሯችን አብዝቶ የሚባርከን፣ ሥራችንን እንድንሠራ በበረከት ያጣነውን ደስታ የሚመልስልን፣ ባርኮ በበረከት ወደሚያትረፈርፍልን፣ ጉድለትን ሳይሆን ሙላትን፣ ማጣት ሳይሆን በረከትን ወደሚሰጠን ደቀመዛሙርቱ ዓይኖቻቸውንም ወደላይ ትኩር ብለው እንደተመለከቱት እንደሐዋርያት ማየት ይጠበቅብናል፡፡ እውነት ነው እርሱን ማየት ከሁሉም ይበልጣልና ወደሰማይ ያረገውን ጌታ አይናችንን አንስተን እንይ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል

LIKE OUR PAGE >>>