Thursday, May 16, 2013
Sunday, May 12, 2013
ዳግም ትንሣኤ
ዳግም ትንሣኤ የተባለበት ምክንያት፡- በኣከባበር፥ በሥርዓት የመጀመሪውን ትንሣኤ ስለሚመስል ነው፡፡ የትንሣኤ ዕለት የሚባለው ቃለ እግዚአብሔር ሳይለወጥ፤ በሙሉ በዚህ ቀን ይደገማል፡፡ ከዚህም ሌላ ሁለት መጠሪያ ስሞች አሉት፡፡ እነዚህም “ፈጸምነ አግብኣተ ግብር” ይባላሉ፡፡ “ፈጸምነ” የተባለበትም፤ የሰሙነ ትንሣኤን በዓል አክብረን ፈጸምን ማለት ነው፡፡ “አግብዖተ ግብር” የተባለበትም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባ ወአቡየ ግብር ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ...እኔ ልሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ” ያለውን ከቅዳሴ በኋላ ሊቃውንት በዚህ ቀን ስለሚዘምሩት ነው፡፡ ዮሐንስ ፲፯፥፬
በተጨማሪም የሐዋርያው ቶማስ ምስክርነት የሚታሰብበት ነው፡፡ ዳግመኛ ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ሳሉ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ሳለ ደጁም ተዘግቶ ሳለ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በመካከላቸው ቁሞ እንዴት ሰነበታችሁ! አስታረቅኋችሁ” አላቸው፡፡ ሁለት ሰዓት አሳልፎ ስለመጣ “እምድኅረ ሰሙን” አለ እንጅ፥ በስምንተኛ ቀን ሲል ነው፡፡ በመጀመሪያው መገለጡ ያልተገኘው ሐዋርያው ቶማስ ትንሣኤውን አላመነም ነበርና፤ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ እጆቼንም እይ፤ እመን እንጅ ተጠራጣሪ አትሁን” አለው፡፡ ቶማስም መለሰ “ጌታዬ አምላኬ ሆይ” አለ፡፡ መዳሰሱን ሲያይ “ጌታዬ”፤ ማቃጠሉን ሲያይ “አምላኬ” አለ፡፡ ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ ሕያዊት ሁና፤ (በሕይወት ትኖራለች) በሕንድ አገር ከታቦት ጋር በመንበሩ ላይ ያስቀምጧታል፡፡ በዓመት በዓመት በእመቤታችን በዓል በአሰተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ፥ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያረፋል፤ እንዲሁ በዓመቱ የሚሾመውን ተራምዳ ትይዘዋለች፤ እንዲህ እያለች ትኖራለች፡፡ ይህም የሚያስተምረን የጌታን ተአምራት፤ የሐዋርያውን ሥልጣንና ብቃት ነው፡፡ጌታም ቶማስ ሆይ! ብታየኝ አመንክን? ሳያዩኝ የሚያምኑብኝ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡ ዮሐ ፳፩፥፳፬-፳፱ ለብርሃነ ትንሣኤው ያደረሰን አምላካችን፥ እስከ ፍጻሜ ሕይወታችን በሃይማኖት የቀናን፤ በምግባር የጸናን ያድርገን! አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ
Wednesday, May 8, 2013
ልደታ ለማርያም
https://www.youtube.com/watch?
ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር:እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ:እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የበቁ ባለጸጎች ነበሩ:ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውምና መካን ነበሩ:አንድ ቀን ጴጥርቃም ቴክታን እህቴ ሆይ ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን ልጅ የለን የሚወርሰን:አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም አላት:እርሱአም ወንድሜ ሆይ አምላከ እስራኤል ለኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ ብላ ብታሰናብተው እንደዚ ያለ ነገር እንኩአንስ ላደርገው በልቦናዬ እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቅብኛል አላት:እሱአም አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም:ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማህጸኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋም ፀሃይን ስትወልድ አየሁ አለችው::
እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሂዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው:ያም ህልም ፈቺ እግዚአብሄር በምህረቱ አይቱአቹአል በሳህሉ መግቡአችሁአል 7 አንስት ጥጆች መውለዳቹ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላቹ ከቤታቹ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዱአ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹ የፀሃይ ነገር ግን አልታወቀኝም አለው:እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ነገራት እርሱአም እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል ብላ ዝም አለች:ከዛም ፀንሳ በ9 ወሩአ ሴት ልጅ ወለደች:ስሙአንም ሄሜን ብለው አወጡላት:ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኑአም ደርዲ ብለው ስም አወጡላት:ደርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደች እና ቶና አለቻት:ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት;ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት:ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት:ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሃናን ወለደች::
ከጴጥርቃና ከቴክታ የተወለዱ 67 ወንዶች ልጆች አሉ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ትውልድ ለመቁጠር ትንቢት አልተነገረላቸውም ሱባኤ አልተቆተረላቸውምና አልተፃፈም:ይህቺም ሃና በስራት በቅጣት አደገች:ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው(መጽሃፍ ቅዱስ ይገልጸዋል) ከቅዱስ እያቄም ጋር አጋቡአት::እነዚህ ቅዱሳን እያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ:ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑ ዋሉ:ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ:እያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው አትጣለኝ:አትናቀኝ:ፀሎተን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ:ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:ሃናም በበኩሉአ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው:ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች: እንዲ ብለው ስይዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቹአ ጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኅኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች:እንዲ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን:ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስለት ገቡ::
ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማላቹ ስእለታችሁን ይቀበልላቹ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላቹ ብሎ አሳረገላቸው:
ከዚያም በሁአላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም እለቱን ራእይ አይተው ነገር አግንተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት:ወፍ የተባለው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:ነጭነቱ ንጽሃ ባህሪው ነው:ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱ:የኢያቄምን ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው እወቅ ሲል ነው:7ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባህሪው:ምልአቱ:ስፍሃቱ:ርቀቱ:ልእልናው:ዕበዩ መንግስቱ ናቸው:ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው::ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት:ነጭነቱአ ንጽህናዋ:ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቱአ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሱአ ነው:ይህንኑም ራእይ ያዩት ሃምሌ 30 ዕለት ነው::
እነሱም እንዲ ያለ ራዕይ ካየን:ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም:ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆን ብለው አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7 ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ:ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሱአን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራት በፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ተፀነሰች(በኦሪት ስርአት እሁድ ዕለት ባል እና ሚስት መገናኘት ልማድ ነበርና):እመቤታችን የተፀነሰች ዕለት አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ:ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት:የሃናም የአጎቱአ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቹአ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት:እርሱአም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነስቶ ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ ብሎ ሰገደላት:አይሁድ ከዛ ነበሩና ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከዚች ከሃና ማህፀን የምትወለደው ህፃን ሰማይ ምድርን:እመቅ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኑአት ሰማሁአቸው እኔንም ያነሳችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሱአ ናት አላቸው በል ተወው ሰማንህ ብለው ቅናት ጀመሩ::
""እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች::""
እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም የተወለደችበት እለት በአባት እናቱአ ቤት ፍስሃ ደስታ ተደረገበት ቤቱንም ብርሃን መላው በስምንተኛውም ቀን ""ማርያም"" ብለው አወጡላት::ስለምን ማርያም ብለው አወጡላት ቢሉ:እነሆ በዚ አለም ከሚመገቡት ሁሉ ምግብ ለአፍ የሚጥም ለልብ የሚመጥን "ማር" ነው:በገነትም በህይወት የተዘጋጁ ጻድቃን ቅዱሳን "ያም" የሚባል ምግብ አላቸው ::ከዚ ሁሉ የበለጥሽ የከበርሽ ነሽ ሲሉ ስለዚህ "ማርያም" ብለው አወጡላት::የእመቤታችን ማርያም ስም ተነቦ ሳይተረጎም ይቀር ዘንድ አይገባምና:-""ማ"" ማለት ማህደረ መለኮት: ""ር"" ማለት ርግብየ ይቤላ: ""ያ"" ማለት ያንቀዓዱ ኃቤኪ ኩሉ ፍጥረት:""ም"" ማለት ምስሃል ወምስጋድ ወምስትሥራየ ኃጥያት ማለት ነው::አንድም "ማርያም" ማለት ልዩ ከጣዖት:ክብርት እምፍጥረታት:ንጽህት እምሃጥያት:መልክ ከደም ግባት የተሰጣት ማለት ነው:ዳግመኛም "ማርያም" ማለት ተፈስሂ ቤተ ይሁዳ ወተሃሠዪ ቤተ እስራኤል ማለት ነው::
አንድም "ማርያም" ማለት መርህ ለመንግስተ ሰማያት ማለት ነው:ይህስ እንዴት ነው ቢሉ:እነሆ ዛሬ በዚህ አለም ለዕውር መሪ በትር እንዲሰጡት ሁሉ እርሱአም በፍቅሩአ:በጣዕመ ፍቅሩአ የሰውን ሁሉ ኃጥያት:ክፋት ፍቃ ከልጁአ ከወዳጁአ አስታርቃ ከገሃነመ እሳት አውጥታ መንግስተ ሰማያት የምታስገባ ስለሆነች ስለዚህ መርህ ለመንግስተ ሰማያት አሉአት::አንድም ማርያም ማለት ሰረገላ ፀሃይ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ተላኪተ እግዚአብሄር ወሰብእ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ውብህት(ስጥውት) ማለት ነው::
በዚህ በግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን አለምን ልታስምር ከቅድስት ሃና እና ከቅዱስ እያቄም በብዙ ልመና ተገኘች::
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሩአ ጣዕሙአ በረከቱአ ረድኤቱአ አማላጅነቱአ በእውነት በኛ አማላጅነቱአን በምናምን ልጆቹአ ላይ ይደርብን::
ከትንሣኤ እሁድ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜ ...
ሰኞ- ማዕዶት ይባላል፡- ማዕዶት ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት በፋሲካችን በክርስቶስ ትንሣኤ
ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከሃሳር ወደ ክብር መሻገራችንን
እናስባለን፡፡
ማክሰኞ- ቶማስ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቶማስ ጌታን አይቶ ማመኑ፤ ጌታዬና አምላኬ ብሎ መመስከሩ ይዘከራል፡፡ ዮሐ. 20፡27-29
ረቡዕ- አልአዛር ይባላል፡- በዚህ ዕለት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ ኢየሱስ አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው
እናስባለን፡፡ ክርስቶስ የሞትን ስልጣን የሻረ የሕይወት ራስ፤ የመቃብርን ሥርዓት ያጠፋ ትንሣኤ፡ በድልም ያረገ
ንጉሥ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡
ሐሙስ- አዳም ሐሙስ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው ተስፋ እና የተገባለት ኪዳን እንደተፈጸመ አዳምና ልጆቹ ነጻ እንደወጣን እናስባለን፡፡
አርብ- ቅድስት ቤተክርስቲያን ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ
ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ እንዳከበራት
ይነገራል፡፡ ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን ሳይሆን አማኞችን ነው፤ ክርስቶስ ለሕንፃ አልሞተምና፡፡
ቅዳሜ- ቅዱሳት አንስት ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቅዱሳት አንስት የክርስቶስን አካል ሽቶ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸውና ትንሣኤውንም ቀድመው ማየታቸው ይሰበካል፡፡
እሁድ- ዳግም ትንሣኤ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምን መስበኩ እና ሥልጣንን መስጠቱ ይሰበካል፡፡
Sunday, May 5, 2013
እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤዉ በሰላም አደረሳቹ
ትንሣኤውን የምናከብረው ያጡትን በማሰብ ይሁን
የትንሣኤን በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሞትን በመስቀል ላይ ከተቀበለ በኋላ በሦስተኛው ቀን መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ዕለት ነው፡፡
የትንሣኤውም ዓላማ የሰው ልጅ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ አለመቅረቱን ለማስረዳት፣ ክርስቲያኖች ከሞት በኋላ ተስፋ ትንሣኤ እንዳለን ለማጠየቅና ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሐ መነሣት እንዳለብን ለማስተማር መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡
በቤተክርስቲያናችንም እነዚህ ታላላቅ ዓላማዎች ያሉት የትንሣኤ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችን ሞትና ሰይጣን ድል የተነሡበት፣ የሰው ልጅም ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣበት፣ በአዳምና በሔዋን ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ የድል፣ የነጻነትና የሰላም ዕለት ስለሆነ ነው፡፡
ስለዚህም በቤተክርስቲያናችን የትንሣኤ ሰላምታ የተለየ ነው፡፡ ይኸውም፡-
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን. . . በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን. . . አጋዐዞ ለአዳም
ሰላም . . . እም ይእዜሰ
ኮነ . . . ፍስሐ ወሰላም የሚል ነው፡፡
እንግዲህ ይህንን በዓል በየዓመቱ ስናከብር ዓላማውን ዘንግተን በዓሉን የምግብና የመጠጥ ብቻ እንዳናደርገው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
በልዩ ልዩ መንገድ በፈቃዱ የሰይጣን ባሪያ የሆነ፣ ከክርስቲያናዊ ምግባርና ትሩፋት የራቀ ሁሉ ራሱን እንዲመረምርና ለመልካም ሥራ እንዲነሣ የሚያደርግ በዓል መሆኑን ተረድተን ራሳችንን ልናስተካክል ያስፈልጋል፡፡
በዓለም በሥጋ ሥራ በመመላለስ የምንኖር ከዚህ ሥራችን በልቦና ትንሣኤ ተነሥተን የንስሐ ፍሬ የምናፈራበት እንዲሆን ልንተጋ ይገባናል፡፡
ክርስትናችን በስም ብቻ ተወስኖ በዓለም በሥጋ ሥራ የምንኖር ደግሞ ራሳችንን በመመርመር በንስሐ ታጥበንና ታጥነን ትንሣኤውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን በመቀበል እናክብረው፡፡
ሁልጊዜም በዓሉን ከነዳያን ጋር እየተካፈልን የምንኖር መልካም ልማድ ያለን የትሩፋት ሥራችንን እያሳደግን፣ በሃይማኖትና በምግባርም እየበረታን ልንሔድ ያስፈልጋል፡፡ ክርስትና ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ የምናፈራበት የዕድገት ጉዞ እንጂ በምንሠራት ጥቂት የትሩፋት ሥራ ብቻ ረሥተን የምንቆምበት አይደለምና በትሩፋት ላይ ትሩፋት፣ በጸጋ ላይ ጸጋ እየጨመርን መሔድ ይገባናል፡፡
ትንሣኤውን በማሰብ ነዳያንን የምናስፈስከውም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራትም ሁልጊዜ በሬ እያረዱ ፋሲካውን ማክበር ብቻ ሳይሆን፤ ነዳያኑንና ወጥተው ለመለመን አፍረው በየቤቱ የተቀመጡ ወገኖቻችንን ጭምር በማስታወስ እንዲሁም በልማት የሚያሳትፍ ሥራ ወደመሥራት በማደግ ችግረኞቹን በዘላቂ ልማት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይገባናል፡፡
ከዚህም ሌላ ነዳያኑን በዚህ ዓለም በሥጋ ስላጡ በነፍሳቸው በመንፈሳዊ ሕይወት እውቀት አግኝተዋል ማለት ስላልሆነ፤ በነፍሳቸው የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ መንፈሳዊውንም ምግብ ልንመግባቸው ያስፈልጋል፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)


