የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም በድንግልና የወለደችውን እውነተኛውን ክርስቶስን በእውነተኛው መንገድ የምታመልኩት የተዋሕዶ ልጆች ሁላችሁ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ፣ እንኳን አደረሰን!!!
ያዕቆብን እንደወለደ… ኤልዩድም አልዓዛርን እንደወለደ… እንዲህ ዝም ብሎ በአንድ ቃል አልተናገረውም ይልቁንም ከመ ዝ ውእቱ ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ... የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበር ሲል ለነጊር እፁብ የሆነውን ለመሥማትም ጣእም ያለው የልድቱን ነገር በሠፊው ተነተነው እንጂ...
ዮሐንሥም በወንጌሉ ሢናገር ቀዳሚሁ ቃል ውዕቱ... በመጀመሪያ ቃል ነበር ሲል ቀዳማዊነቱን ይናገራል ዳግመኛም ቃል ሥጋ ኮነ... ቃልም ሥጋ ሆነ ሲል ቀደሞ የነበረ እርሱ ሰው መሆኑን ነገረን።
ሉቃስ በወንጌሉ ጥንተ ነገሩን ገልጦ ሲናገር እንዲህ አለ፦ "በዚያም ወራት አገሩ ሁሉ ይፃፍ ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ፡፡" የግዛቱን ስፋት የህዝቡን ብዛት ያውቅ ዘንድ ሁሉም በየወገኑ እንዲፃፍ እንዲቆጠር ከያሉት ከተማ ወደየወገናቸው ወጡ፡፡ ጌታ በወንጌሉ የናንተስ የራስ ፀጉራቹ ሳይቀር የተቆጠረ ነው፡፡ ሰማያዊ አባታችሁ ሳያውቅ ከእናንተ አንድም አይወድቅም ብሎ እንደተናገረ፡ እርሱ ግን ሊቆጠር ከዳዊት ወገን ስለሆነ ወደ ይሁዳ ምድር ወረደ፡፡ ይሄ የአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ምክንያት ሆኖት ከናዝሬት አገር ከገሊላ እንዲወጡና ትንቢት ወደተነገረበት ቤተልሔም ወደምትባል የዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ምድር እንዲሄዱ ሆነ፡፡ በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ መድኃኒዓለምን ወለደችው።
ይህንን አስደናቂ ልደት ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ ለመግለጽ እንደተቸገረ ሲገልጽ፦
ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረ እርሱ ትንሽ ህፃን ሆኗልና፡፡ እኔ ፈፅሜ አደንቃለሁ ፤ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን ፡ በዘላለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ ፡ ከስጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ ፡ ሃጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት ፤ ይህን ወዷልና፡፡
ወዳጆቼ ድንቅ ለሚሆን ጨለማንም አጥፍቶ በብርሃን ለለወጠ ልደቱ እንኳን አደረሳችሁ።
ከመ ዝ ውእቱ ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ። by Binyam Aregawi Tewahdo himanotachin - YouTube
No comments:
Post a Comment