Thursday, July 3, 2014

ሰኔ 24

ሰኔ 24 በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ ሙሴ ጸሊም አረፈ፡፡ አስቀድሞ ሽፍታ ወንበዴ ዘማዊ ጣኦት አምላኪ ነበር፤ በኃላ እንደ አብርሃም አምላኬ ማን ነው ብሎ ተመራመረ፤ ወደ አስቄጥስ ገዳም ብትሄድ አምላክህ ማን እንደሆነ ይነግሩሃል የሚል ራዕይ አየ ተመለከተ፤ ተነስቶም ሄደ አባ ኤስድሮስን አገኛቸው፤አጽናንተው አረጋግተው ወደ አባ መቃርስ ወሰዱት አባ መቃርስም ንስሃውን ተቀብለው ቀኖና ሰጡት ኃላም አመነኮሱት የሽፍቶች አለቃ የነበረው የመነኮሳት አለቃ እስከመሆን ደረሰ፤ ሰይፉን ወርውሮ ከፍቅር ጋር ተወዳጀ፤ሌሊት እየተነሳ ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዳላቸው ነበር ሉሉም ይታዘዛቸው ነበር ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይህን አድርግሊኝ ይሉታል አርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፤ ራሱን ዝቅ አደረገ ትሁትም ሆነ፤ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንብ ነበር፤ እድሜው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ሊቀበል ከመነኮሳት ጋር ሆኖ ወደ አባ መቃርስ ሄደ አርሳቸውም ልጆቼ ከናንተ መካከል በሰማእትነት የሚሞት አለ ብለው ትንቢት ተናገሩ ሙሴ ጸሊምም አባቴ ያ ሰው እኔ ነኝ ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ የሚል ቃል አለ ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር አላቸው፤ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ሊያጠፉ መጡ መነኮሳቱ ሲሸሹ ሙሴ እዚያው ቀረ ሌሎች ሰባት መነኮሳት ከአባታችን ጋር እንሞታለን ብለው አብረውት ሆኑ የበርበር ሰዎች ደረሱ ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው፤ ይህም ሰኔ 24 ቀን ነው፤ የአባታችን የሙሴ ጸሊም ስጋው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፤ ግብጻውን ቤተክርስቲያን ሰርተውለት ታቦት ቀርጸውለት በደንብ ያከብሩታል ገድሉን ጽፈውለታል ፊልምም ሰርተውለታል ይህን ፊልም የኛ ሰዎች ግሩም አድርገው ወደ አማርኛ መልሰውታል፡ የቻለ ገድሉን ያንብብ ያልቻለም ፊልሙን ይመልከተው፤ የዛሬዋን ቀን ስለ ተክለሃይማኖት ብቻ በለን አንመጽውት ስለ ሙሴ ጸሊምም እያልን ይሁን፤ አምላከ ተከልዬ ጠብቀኝ ስንል አምላከ ሙሴ ጸሊም አትርሳኝ ማለትን አንርሳ ይህ ድንቅ አባት የማይረሳ ነውና፡፡ ሙሴ ጸሊም ማለት ሙሴ ጥቁር ሰው ማለት ነው፤ መልኩ ጥቁር ስለሆነ ነው ጥቁሩ ሙሴ ተብሎ የተጠራው፤ እገሌ ጥቁር ሰው እገሌ ጥቁር ስው አሁን የመጣ አይደለም፤ ኳስ መቶ ጎል ያገባ በሙሉ እገሌ ጥቁር ሰው መባል ጀምሯል፤ ቤተክርስቲን ግን ጥንቱንም ቢሆን አንዱን ቅዱስ ከአንዱ ለመለየት ቅጽል ስም ትሰጣለች ለምሳሌ ዮሐንስ አጺር አጭሩ ዮሐንስ ስምኦን ጫማ ሰፊው ሙሴ ጸሊም ጥቁሩ ሰው ሙሴ……ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 23

ሰኔ 23 
በዚህች ቀን የዳዊት ልጅ የቤርሳቤህ ልጅ ጠቢቡ ሰሎሞን አረፈ። በ 12 ዓመቱ ሲነግስ እግዚያብሔርን አንዲት ነገር ለመነው ፍርድ እንዳልገመድል ደሃ እንዳልበድል ጥበብን ስጠኝ ብሎ የልቡን መሻት ሰጠው ፍጹም ጠቢብም አደረገው፤ለ 40 ዓመት በቅን እየፈረደ በንግስና ቆይቶ በ 52 ዓመቱ በዛሬዋ ቀን አረፈ።

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 20

ሰኔ 20 ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ህንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የታነጸው በዛሬዋ ቀን ነው አናጺውም እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። ጴጥሮስ፤ ዮሐንስ በርናባስና ሌሎችም ሐዋርያት በፊልጰስዩስ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ 3 ድንጋዮችን አንስቶ ጎተታቸው እንደ ሰም ተለጠጡ እንደ ግድግዳም ሆኑ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ እየሩሳሌም እምሳያ አድረጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፤ ዳግመኛ በበነጋው ሰኔ 21 ቀን እመቤታችንን እና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል ቅዳሴ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቆረባቸው ፍጹም ደስታም ሆነ። ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታ እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የነሶሎሞን ቤተመቅደስ የአይሁድ ምኩራብ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ስርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፤ ታዲያ ሐዋርያት የት ነበር ህዝቡን የሚያጠምቁት የሚያቆርቡት ካሉ በየሰው ቤት ነበር። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ታላቁ ነብይ ኤልሳዕ አረፈ። ይህ ነብይ በ 12 ጥማድ በሬ ሲያርስ ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ ተከተለኝ አለው ምንም ሳያቅማማ ሀብት ንብረቱን ትቶ ተከተለው፤ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከማረጉ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ ይለዋል ባንተ ላይ ያደረ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደርቢኝ ይለዋል፤ እንደ ቃሉ ሆነለት ተደረገለት፤ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሳ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነስቷል፤ ኤልያስ አንድ ጊዜ ባህር ሲከፍል ኤልሳዕ ሁለት ጊዜ ባህር ከፍሏል። እምቤታችንን የኤልሳዕ ጋን ይላታል ኤልሳ የመረረውን ውኃ እንዳጣፈጠ እመቤታችንም ይህን መራራ ዓለም ጌታን በመውለዷ አጣፍጣዋለች፤ የዚህ ነብይ ድንቅ ታሪኩ 2ኛ ነገስት ላይ በስፋት ተጽፏል ሰኔ 20 ቀን እረፍቱ ነው ቤተክርስቲያን የዛሬውን ቀን እመቤታችንን እና ነብዩን አስባ ትውላለች። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 12

ሰኔ 12 በዚህች ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀን ነው። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን ጻድቁ ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ያረፈበት ቀን ነው። ቅድስት አፎምያ የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር ታዘክር ነበር ለድሆችም አብዝታ ትረዳ ነበር፤ በዚህ ሰይጣን ቀናባት በመነኩሴ ተመስሎ ሊያስታት ሞከረ በቅዱስ ሚካኤል ስዕል አሳፍራ መለሰችው ከ 3 ወራት በኃላ ሰኔ 12 ቀን ዳግመኛ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ ብሎ ሊፈትናት መጣ፤ ሚካኤል ከሆንክ መስቀልህ የት አለ አለችው ከዚህ በኃላ አፉን ከፍቶ አይኑን አጉረጥርጦ አንገቷን አነቃት “ቅዱስ ሚካኤል ድረስልኝ” ብላ ተጣራች ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ፈጥኖ ወረደ በበትረ መስቀሉም መታው ጊዜዬ ሳይደርስ አታጥፋኝ ስዕልህ ባለበት፤ ስምህ በተጠራበት፤ ድርሳንህ በሚነበብበት፤ ፈጽሞ አልደርስም ብሎ ማለ፤ ተገዘተ ሸሸም፤ ከዚህ በኃላ ቅዱስ ሚካኤል ቅድስት አፎምያን “ወዳጄ አፎምያ ባነቺ ደስ አለኝ ወጋሽ በሰማይ ታላቅ ነው” ብሎ ባርኳት አርጓል። ቅዱስ ላሊበላ (ላልይበላል) ላል ማለት ማር ማለት ነው፤ሲወለድ በንብ ተከቦ ነበርና ማር ይበላል “ላልይበላል” አሉት ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ትባላች እረፍቷ ሐምሌ 27 ነው ልጁ ይትባረክ እረፍቱ መስከረም 24 ቀን ነው ቅዱስ ላሊበላ 40 ዓመት ኢትዮጰያን አስተዳደረ ዓለምን የሚያስደንቅ እጹብ እጽብ የሚያሰኝ ከአንድ አለት ብቻ እጀታ በሌለው መጥረቢያ 12 ውቅር አብያተክርስቲያናትን አነጸ፤ እነዚህ በአንድ ቦታ ስላሉ ነው እንጂ በወሎ በጎንደር በሸዋ ለቁጥር የሚበዙ አብያተክርስቲያናትን አንጿል፤ ታህሳስ 29 ቀን ተወልዶ በ 80 ዓመቱ ሰኔ 12 በዛሬዋ ቀን አርፏል። መጨረሻ ያነጸው ቤተክርስቲያን አዳዲ ማርያምን ነው፤ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ናቸው እንዲያንጽ የጠየቁት እርሱም ጀምሮ ሳይጨርስ አቡነገብረመንፈስ ቅዱስ ወደርሱ ቀርበው ወዳጄ ላሊበላ የእረፍትህ ቀን ደርሷልና ወደ ላስታ ተመለስ አሉት እርሱም ተመለሰ በዚያም አረፈ፤ እራሱ ባነጸው በቤተ ጎሎጎታ ተቀበረ በመቃብሩም ላይ ለ 10 ቀን የማይጠፋ ብርሃን ሲበራ ይታይ ነበር። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።


LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 11

በዚህች ቀን ከሰባቱ ዓበይት ሰማዕታት አንዱ የሆነው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዲዎስ አረፈ። ስንክሳሩ የመልአክት አርአያ ያለው ይለዋል ንጽህናውን ቅድስናውን ሲያጠይቅ፤ የሮም የነገስታት ልጅ ነው ዓለምን ክብሩን ሁሉ ንቆ ወጣ በፍጹም ተጋድሎም ኖረ ለጣኦት አልሰግድም አልሰዋም ብሎ ሰው ሊሰማው የሚከብድ ጽኑ መከራዎችን በትእግስት ተቀበለ በዛሬዋ ቀንም አንገቱን ተቆርጦ በሰማዕትነት አረፈ። ሰኔ 11 ቀን የሚነበበው ስንክሳር ታሪኩን በሰፊው ጽፎታል፤ ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ ይህ ሰማዕት በተለይም በጎንደር ልዩ ክብር እንዳለውና በስሙ ታላላቅ ገዳማት እንደታነጹለት በአጠቃላይ ኢትዮጰያ ውስጥ ከ 16 የማያንሱ አብያተክርቲያናት እንዳሉት “የቅዱሳን ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፤ በነገራችን ላይ በዚሁ ስም የሚጠሩ ታላቅ የኢትዮጰያ ጻድቅ ንጉስም አሉ ዓጼ ገላውዲዎስ ግራኝ መሐመድን ድል የነሱ ናቸው ቤተክርስቲያን መታሰቢያቸውን መጋቢት 27 ቀን ታከብረዋለች። የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የቤተክርስቲያን ማረጃዎች የሚለውን መጽሕፍ ይመልከቱ ።ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 9

ሰኔ 9 በዚህች ቀን ከተራራማው ከአፍሬም አገር አርማቴም ከተባለ ቦታ የወጣው የሐና ልጅ ታላቁ ነብይ ሳሙኤል አረፈ። ይህ ነብይ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ገልአርታ ውስጥ ታቦት እንዳለው ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ የቅዱሳን ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል። ነብዩ ሳሙኤል በብዙ እንባ በታላቅ ትዕግስት የተገኘ ነብይ ነው ሐና መካን ሆና ለረጅም ዘመን ታለቅስ ነበር ሰዎችም ይዘባበቱባት ነበር ይህች የበቅሎ ዘመድ ቢወልዷት እንጂ የማትወልድ በኃጢያቷ ብዛት እየው እግዚያብሔር ልጅ ነሳት፤ደግሞ እኮ አታፍርም ወደ ቤተ እግዚያብሔር ትሄዳለች ይሏት ነበር፤ ከእለታት በአንዱ ቀን እጇን ወደላይ አንስታ ከንፈሯን እያንቀሳቀሰች በለሆሳስ እያለቀሰች ስትጸልይ ተመልክቶ ካህኑ ዔሊ ሳይቀር አንቺ ሰካራም በሎ ዘለፋት 1ኛ ሳሙ 1፤14። እግዚያብሔር ግን ጸሎቷን ሰማት እንባዋን አበሰላት ከልጅ በላይ ልጅ ሰጣት እርሷም እንዲህ ብላ ግሩም ምስጋና አመሰገነች ይህንን የሐና ምስጋና ቤተክርስቲያን ዘወትር ትጠቀምበታለች መዝሙረ ዳዊት የጸሎት መጽሐፍ ካልዎት ይህንን ምስጋና እዚያ ላይ ያገኙታል፤ ልቤ በእግዚአብሔር ጸና ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ በማዳንህ ደስ ብሎኛል። እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። ኡፈየው እንዴት ያለ ጣፋጭ ምስጋና ነው፤1ኛ ሳሙ 2፤1። ነብዩ ሳሙኤል ሳኦልን ከአህያ ጠባቂነት ጠርቶ በእስራኤል ላይ ያነገሰ ነው ዳዊትን ደግሞ ከእረኝነት ጠርቶ ለእስራኤል ያነገሰ ነው፤ ሳኦልን በእስራኤል ዳዊትን ለእስራኤል “በ” እና “ለ” የእነዚህን ቃላት ልዩነት የሐሙስ ውዳሴ ማርያም አንድምታው ላይ በስፋት ተጽፏል፤ ነብዩ ሳሙኤል በ 98 ዓመቱ አረፈ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። 1ኛ ሳሙ 25፤1

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 8


ከእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላት አንዱ ነው፤ በዚህ ዕለት ልጇ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ግብጽ በስደት ሳሉ ለህሙማን ድህነት እንዲሆን ውኃን ከዓለት ላይ ያፈለቀበት ቀን ነው፤በዚሁ ቦታ በእመቤታችን ሥም ታላቅ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ የተከበረበትም ቀን ነው፡፡እመቤታችንን ከፍጥረት ዓለም ለይቶ አክብሮ የእናት አማላጅ አድርጎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፡፡
ከተአምር አስቀድሞ ይህ ይነበብ ህዝቡ ዕዝነ ልቦናቸውን ከፍተው ይስሙ፤ በዕብራይስጥ ማርያም የተባለች የእመቤታችንን ተአምር ለመስማት ቀላል አይምሰለው የከበረ ገናና ነውና ወደ ግዝት እንዳይገቡ መስማትን አያስታግሉ ፤ በእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላትና እሁድ በተባለች ሰንበት ወንዶችም ሴቶችም ወደ ቤተክርስቲያን ይሰብሰቡ የተአምሯን መጽሐፍም ያንብቡ፤ ዛሬ ሰኔ 8 ቀን ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ ይህም በስደታቸው ወራት ልጇ ከደረቅ አለት ላይ ውኃን ያፈለቀበት ቀን ነው። ይህ ውኃ እንደ ማር እንደ ወተት የጣፈጠ እንደ ወተትም የነጻ ነው፤ ከዚህ ውኃ የጠጣ ሁሉ ይፈወስ ነበር። ታሪኩ እንዲህ ነው የግብጽ በረሃ በጣም ሲያደክማቸው ከአንድ መንደር ያርፋሉ በዚያም ጌታ ውኃ ይጠማዋል ይህን ባየች ጊዜ እምቤታችን ከመንደሩ ሴቶች ውኃ ልትለምን ሄደች፤ ዮሴፍና ሶሎሜ ግን ደከሟቸው ተኝተው ነበር፤ ውኃ የሚሰጣት የሚመጸውታት ስታጣ ልቧ በሐዘን ተወግቶ ተመልሳ መጣች ጌታን ከተቀመጠበት አንስታ ታቀፈችው ስቅስቅ ብላም አለቀሰች ህጻን ጌታም የእናቱን እንባ ከጉንጮቿ ላይ በእጆቹ ጠረገላት ትንሽዬ ጣቱን (ማርያም ጣት የምንለውን ነው ወደ ምድር አመለከተ ወዲያውኑ ጣፋጭ ውኃ ከአለት ላይ ፈልቆ ጠጡ፤ እንዲህም አለ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ለድህነት ይሁነው ብሎ ባረከው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚጠጣው ሁሉ ከደዌው ይፈወስ ነበር፤ አሁንስ ይኖር ይሆን ? እንጃ፤ የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂያችንን የወለድሽልን እመቤቴ ማርያም ሆይ ሠላምታ ይገባሸል የሄዋን ጽኑ የሚጎዳ ማሰሪያዋ ባንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ውዳሴም ይገባሻል እኛ ከምንወደው እርሱም ከሚወደን ልጅሽ ይቅርታ ያደርግልን ዘንድ ለምኝልን።

LIKE OUR PAGE >>>