Thursday, May 16, 2013

ግንቦት 11


ግንቦት 11 በዚህች ቀን የዜማው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ወደ ብሔረ ሕያዋን የተሰወረበት ቀን ነው። ይህ ቅዱስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነጹት አብያተ ክርስቲያናት ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው: እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተከበበ እና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት ::
የዚህ ቅዱስ አባት አዳም የእናቱም ስም ታውክሊያ ሲባሉ :በ512 ዓ ም በአክሱም ከተማ ተወለደ:: እናት እና አባቱም ልጃቸውን ለማስተማር ወደ ዘመዳቸው አባ ጌዴዎን ልከው እንዲማር አደረጉት : ይህም አባት አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ግዜ መቀበልም ማጥናትም ተሳነው እስከ ብዙ ዘመንም መዝሙረ ዳዊትን ሲማር ኖረ ነገር ግን ከልቡ ማጥናትን እምቢ አለው:መምህሩም አብዝቶ ደበደበው ባሳመመውም ግዜ መታገስ ተሳነው ከአባቶቹ ቤትም ወቶ ዕብነ ሃኪም ወደተቀበረበት ገዳም ሄደ : በውስጡም የወርቅ የብር የልብስ መቀመጫዎች የተመሉ ናቸው: ከአንዲትም ዛፍ አጠገብ ደረሰ ከዚያም አረፈ ትልም ወደ ዛፏ ሲወጣ አየ :ወደ ዛፊቱም እኩሌታ ደርሶ ወደ ምድር ይወድቃል :ሁለተኛም ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል መጀመርያ ወደ ደረሰበት ሲደርስ ይወድቃል:ሲወጣ ሲወድቅ ብዙ ግዜ ያደርጋል : ወደ ሌላ ቦታም አይሄድም
ከዚህም በኋላ በብዙ ጥረት በብዙ ትጋት በብዙ ድካም በዚያ ከዛፏ ላይ ወጣ:ከዚያችም ከዛፏ ላይ ተቀምጦ በላ :ቅዱስ ያሬድም ወደዚያ ዛፍ ላይ ይወጣ ዘንድ እንደሚተጋ ብዙ ግዜም ከላይ ሳይደርስ ከመካከል እንደሚወድቅ ከዚያም በኋላ በጭንቅ ወደ አሰበው እንደደረሰ የፈለገውንም እንዳገኘ የትሉን ትጋት ባየ ግዜ ሰውነቱን ግርፋቱን እንደምን አትታገሺም ህማሙንስ እንደምን አትችይም አላት መታገስንስ አብዝተሽ ኖሮ ቢሆን እግዚአብሄር በገለጠልሽ ነበር ይንንም ብሎ አለቀሰ ወደ መምህሩ ወደ ጌዲዮን ተመለሰ አባት ሆይ ይቅር በለን እንደቀድሞ ንገረኝ አስተምረኝም አለው:መምህሩ ጌዲዮንም እንዳልከው ይሁን አለው 150ውን መዝሙረ ዳዊት:መሃልየ ነብያትን :መሃልየ መሃልይን :የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ምስጋና ነገረው:81ዱ መጻህፍትን ትርጓሜ የሌሎች መጽሃፍትን ቁትር እና የመሳሰሉትን መጽሃፍተ ሊቃውንት ሁሉ በአንድ ቀን አጥንቶ ፈጸመ::
ከዚህ በኋላ በብዙ ለቅሶ ወደ እግዚአብሄር በለመነ ግዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ግዜ የብሉይ እና የሃዲስ መጽሃፍትን ተምሮ ፈጸመና ዲቁና ተሾመ:በዚያም ወራት እንደዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማህሌት የለም ነበር በትሁት እንጂ :: እግዚአብሄርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ግዜ ከኤዶም ገነት 3 አእዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ እየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነሱ ጋር አወጡት በዚያም 24ቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማህሌት ተማረ::
ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ግዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በ3 ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ:ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ :የፅዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሰራት የድንኳንን አሰራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ:: ይህቺም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት:የቃሉንም ድምጽ በሰሙ ግዜ ንጉሱም ንግስቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋር የመንግስት ታላላቆች እና ህዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሮጡ:ሲሰሙትም ዋሉ ከዚህም በኋላ ከአመት እስከ አመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምት እና በበጋ:በመጸው እና በጸደይ:በአጽዋማት እና በባእላት :በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በአል በነብያት እና በሃዋርያት በጻድቃን እና በሰማእታት በደናግልም በአል የሚሆን አድርጎ በሶስቱ ዜማው ሰራ :ይህውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው::
የሰው ንግግር የአእዋፍ የእንሥሳትና የአራዊት ጩሀት ከነዚህ ከሶስቱ ዜማ አይወጣም :በአንዲት እለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉስ ገበረመስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሱም የያሬድን ድምጽ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ የብረት ዘንጉን ወይም መቋምያውን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውሃ ፈሰሰ ያሬድም መሃሌቱን እስከሚፈጽም አልተሰማውም ነበር ንጉሱም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለከውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው ንጉስም በማለለት ግዜ ወደ ገዳም ሄጄ እመነኩስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሱም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሃላውን አሰበ እያዘነም አሰናበተው ከዚ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ በተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበርሽ እና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍ ያልሽ የብርሃን መውጫ የህይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና (አንቀጸ ብርሃን) እስከመጨረሻ በተናገረ ግዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ::
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን ሃገር ሄዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ስጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ እግዚአብሄር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚ በኋላ ግንቦት 11 ቀን የተሰወረበት ቦታ በሰሜን ጠለምት ደብረ ሐዊ በተባለው ተራራ ነው፤ በዚህ ቦታ በስሙ የታነጸለት አስደናቂ ገዳም አለው፤ በመዲናችን አዲስ አበባም መስቀል ፍላዎር አካባቢ ግሩም ቤተክርስቲያን አለው ዛሬ ታቦተ ህጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ. በአንድ ወቅት እመቤ...ታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አባ ሕርያቆስን ከብሕንሳ፤ ቅዱስ ኤፍሬምን ደግሞ ከሶርያ ይዛ ለቅዱስ ያሬድ አክሱም ላይ ተገለጸችለት እንዲህም አለቻቸው በሉ አንተ ቅዳሴዬን አንተ ደግሞ ውዳሴዬን ንገሩትና በዜማ ይድረስው አለቻቸው፤ እነርሱም ነገሩት እርሱም የሚጣፍጥ ዜማ ደረሰ፤ዛሬም ድረስ ጠዋትና ማታ ቤተክርስቲያን ድምጿን ከፍ አድርጋ ይምታሰማው እነዚህ ሶስት ግሩማን አባቶች የተባበሩበትን ምስጋና ነው። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን። የአባታችን የአምሳለ ሱራፌል የሊቁ ማህሌታይ የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ በረከቱ ረድኤቱ በኛ በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ በሃገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም በእውነት ይደርብን !!!!!አሜን

ግንቦት 9



በዚህች ቀን የጌታችን የመድሐኒታችንን የእየሱስ ክርስቶስን መስቀል ያገኘችው እሌኒ ቅድስት አረፈች። ይህችም የታላቁ ንጉስ የቆስጠንጢኖስ እናት ነች። ባለቤቷ ተርቢኖስ ይባላል ነጋዴ ነው ባህር ተሻግረው አገር አቋርጠው ለዓመት ሁለት ዓመት ነግደው ይመለሳሉ ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ አገገራቸው ሲመለሱ መርከብ ላይ ጨዋታ ጀመሩ፤ እኛስ በሠላም ወደ አገራችን ገባን ሚስቶቻችን ግን እንዴት ሆነው ይሆን አሉ ተርቢኖስ ሚስቱን እጅግ ያምናት ነበርና የእኔ ሚስት እንደዚህ ዓይነት ነገር አታውቅም የእናንተ ሚስቶች ያደርጉት ይሆናል እንጂ አላቸው፤ ያንተ ሚስት ከሄዋን ልጆች የተለየች ነችን እኔ ሄጄ ወድጃት ወዳኝ ...ለምጃት ለምዳኝ አፍቅሬት አፍቅራኝ ብመጣ ምን ትቀጣለህ አለው፤ እስከዛሬ የደከምኩበት ወረት ላንተ ይሁን ካልሆነልህ ግን ያንተን እወስዳለሁ አለው፤ በዚህ ተወራርደው ተለያዩ ቤቷ ሄደ አላስገባም አለችው፤ ገረዷን አስጠርቶ ሁለቱ ብቻ የሚተዋወቁበትን እቃ ስጪኝ ወርቅ ብር እሰጥሻለሁ አላት፤ እሺ አንተ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እያልክ በከተማው ለፍፍ አለችው እንዳለችው በከተማው እየዞረ ለፈፈ፤ ወደ እሌኒ ቅድስት ገብታ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እየተባለ ነው ገላሽን ታጠቢ ሽቶም ተቀቢ አለቻት እርሷም ገላዋን ልትታጠብ የአንገት ሐብሏን አስቀምጣ ባኞ ገባች፤ የአንገት ሐብሏ የተርቢኖስ ስም አለበት ወስዳ ሰጠችው፤ እርሱም ሄዶ ‘’እየው ለምጃት ለምዳኝ ወድጃት ወዳኝ መጣሁ ውድ ስጦታም ሰጠችኝብሎ ሐብሉን አሳየው አልተጠራጠረም አመነው የለፋበትን ወረት በሙሉ አስረክቦ እያዘነ ወደ ቤቱ ገባ፤ ምነው ጌታዬ አዝነህ አይሃለሁ ምን ሆንክብኝ አለችው ወረቴን በሙሉ መአበል ወሰደው አላት፤ ታዲያ ለእዚህ ታዝናለህ ያንተም የኔም ዘመዶች ወዳጆች ብዙ ናቸው ተበድረን ትነግዳለህ አለችው፤ እርሱም በአሽሙር ልክ ነሽ ያንቺ ወዳጆች ብዙ ናቸው እኔ ግን ወዳጅ የለኝም ደግሞ በሰጠሁበት አገር ተበድሬ በመጸወትኩበት አገር ለምኜ አልኖርም ወደ ሌላ አገር እሄዳለሁ አላት እኔም ካንተ አልለይም ብላ ተከተለችው በመርከብ ተሳፍረው ሄዱ ከባህሩ መሐከል ሲደርሱእሌኒ ሳምንሽ ካድሺኝ ስወድሽ ጠላሺኝብሎ ሐብሉን አውጥቶ አሳያት እኔ አልሰጠሁትም ህያው እግዚያብሔር ምስክሬ ነው አለችው አላመናት ንጹሕ ከሆንሽ ፈጣሪ ያድንሽ ብሎ በሳጥን አድርጎ ከባህር ጣላት ሳጥኑ በቅዱስ ሚካኤል ጣባቂነት እየተንሳፈፈ ባህር ዳርቻ ደረሰ ቆንስጣ የሚባል ንጉስ አገኛት እጅግ መልከመልካም ነበረችና በክብር አገባት ቆስጠንጢኖስንም ወለደችው ቆንስጣ ሲሞት ልጇ ቆስጠንጢኖስ ነገሰ የጌታን መስቀል ለመፈለግ እየሩሳሌም ወረደች መስቀሉንም አገኘች የዚህ ዜና በሰፊው መስከረም 17 የሚተረክ ነው። 80 ዓመቷ ጌታችን ተገለጸላት ወዳጄ እሌኒ ቅድስት ወደኔ ልወስድሽ ነው ይላታል ደነገጠች ምነው መኖር ትፈልጊያለሽን ይላታል እንተን እንዳመሰግን ብዬ ነው ትለዋለች ስንት ዓመት ልጨምርልሽ ይላታል ይህማ ባንተ ቸርነት መግባት ይሆንብኝ የለምን ትለዋለች እንግዲያውስ 40 ዓመት ጨምሬልሻለሁ አላት 120 ዓመቷ ግንቦት 9 በዛሬዋ ቀን አርፋለች ይህች ቅድስት እናት ያገኘችው ግማደ መስቀል ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከእሌኒ ቅድስት በረከት ያሳትፈን።