Sunday, September 6, 2015

ጳጉሜ/ጳጉሜን


ጳጉሜ ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም ሐገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ጸጋ / Thirty months of sunshine / በመባል ትታወቃች ፡፡ ጳጉሜ በዘመነ ዮሐንስ ስድስት በምትሆንበት ጊዜ ጾመ ነቢያት / የገና ጾም/ ህዳር 14 ቀን ይገባና ታህሳስ 28 ቀን ጾሙ ተፈቶ የልደት በዓል ይከበራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፡-2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ 8፡-2 ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡

ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡ 

ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡ወስብሐት ለእግዚአብሔር



መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ጷጉሜ) ይሁንላችሁ፡፡


Tuesday, August 18, 2015

ደብረ ታቦር ትምህርቱ፣ ምስጢሩና ትውፊቱ



ደብረ ታቦር ትምህርቱ፣ ምስጢሩና ትውፊቱ



በፊልጶስ ቂሣሪያ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ጌታችን እንዲህ በማለት ጠየቃቸው፡፡ "የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?" ሐዋርያትም "ሙሴ፣ ኤልያስ ... ከነቢያትም አንዱ ነው ይላሉ" አሉት፡፡ ጌታችንም "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" አላቸው፡፡ ከሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስም ፈጥኖ አንተ "የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ" አለው፡፡ "ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህም" በማለት ደቀ መዝሙሩን አደነቀ፡፡

ይህ በሆነ በስድስተኛ ቀን ጌታችን ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ጴጥሮስን አስከትሎ ወደ ረዥም ተራራ ወጣ፡፡ /ማቴ 17÷18፤ ማር 9÷28፤ ሉቃ 9÷28-36/፡፡

ለምን ይዟቸው መጣ? 

ስለዚህ ትምህርት ሁለት ምክንያቶች ማየት ይቻላል፡፡ ሞትን ስለማይቀም** ሰው ደቀ መዝሙር አስተምሮአቸው /ነግሮአቸው/ ነበር እና ኤልያስን አሳይቶ የደቀ መዝሙሩ የፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወትም እንዲሁ መሆኑን ለመግለጥ፡፡ /ማር. 9/ እንዲሁም በፊልጶስ ቂሣሪያ "እኔ ማን ነኝ" ባላቸው ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ጴጥሮስ የመሰከረውን እውነት በባሕርይ አባቱ በእግዚአብሔር አብ ለማስመስከር ነው፡፡

በዚህ እለት ምስጢረ ሥላሴን እንዲረዱ የሦስትነት ምስጢር ተገልጧል፡፡ ወደ ተራራውም ፊልጶስ ቂሣሪያ የጠየቃቸውና የመለሱለት ትምህርት ብዙም ሳይዘነጋ በ7ኛው ቀን አውጥቷቸዋል፡፡ 

ረጅሙ ተራራ 

ይህ ተራራ ማን ነው? ወንጌላዊው ማቴዎስ "ረዥሙ ተራራ" በማለት የጠራውን ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ "ቅዱስ ተራራ" በማለት ጠርቶታል፡፡ ሥርዓተ ሐዋርያትን የያዘው ሲኖዶስ የተሰኘው መጽሐፍም በስሙ "ታቦር" በማለት ጠርቶታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ረዥሙ እና ቅዱሱ ተራራ በማለት ቅዱስ መጽሐፍ የገለጠው ደብረ ታቦር / የታቦር ተራራ/ ነው ማለት ነው፡፡

የታቦር ተራራ ትንቢት የተነገረለት ምሳሌ የተመሰለለት ደብር ነው፡፡ ትንቢት "ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሁ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል" በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ተናግሮአል፡፡ /መዝ.** /፡፡ ምስጢረ ብርሃንን /መለኮትን አይተዋልና፡፡

በነቢይነትና በምስፍና ሕዝበ እግዚብሔርን ያገለገሉት ዲቦራና ባርቅ ጠላታቸው ሲሳራን ድል ያደረጉት በዚህ ተራራ ነው፡፡ የእስራኤል ጠላት ክፉ ሰው ሲሳራ በዚህ ተራራ ድል እንደሆነ በልበ ሐዋርያት ይፈታተን እና በክፉ አሳብ ያጠራጥራቸው የነበረ ክፉ ጠላት ሰይጣንም በዚህ ተራራ ድል ተነሥቷል፡፡ ምሳሌው ተፈጸመ፡፡

ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ለምን? 

ወደ ረዥሙ ተራራ ይዟቸው ወጣ የተባሉት ደቀ መዛሙርት ሦስት ናቸው፡፡ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ጴጥሮስ፡፡ ለምን ተመረጡ?

እግዚአብሔር በልዩ ልዩ ምክንያት ይመርጣል፡፡ ለአገልግሎት ይለያል፣ ምስጢር ይገልጣል ወዘተ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት የመረጠበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ ሙሴ ለምን መስፍን እንደሆነ አይታወቅም፤ አሮን ለምን ካህን እንደሆነ አይታወቅም "ሰው ፊት ያያል እግዚአብሔርን ግን ልብን ያያል" ዳዊትን ሊቀባ የሄደውን ሳሙኤል የእሴይን ልጆች እያየ ሲያሳልፍ የዐይኑን አምሮት ይሄ ይሆንን ይል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ወንድሞቹን እያሳለፈ ብላቴናው ዳዊትን ለመንግሥት የመረጠበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተመረጡበትን ምክንያት ሲያትቱ የዳሰሷቸውን ጥቂት ነጥቦች እንመልከት፡-

ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሹመት ሽልማ ክብር ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲወጡ ከብልየታቸው እንዲታደሱ ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለድኀነተ ዓለም የመጣው በሕማማቱ በሞቱ ቤዛ የሚሆነን አምላክ "ልሰቀል ነው" ባላቸው ጊዜ "አይሁንብህ" ብሎት ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳብ የጠላት እንጂ የሰው ልጆች ሊሆን አይችልም ከሞቱ በቀር ድኀነት ሊያስገኝልን የሚችል የለምና፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግን ከሞተ ክብሬ ምንድን ነው ብሏልና "አይሁንብህ" አለ፡፡ /ማቴ. 16/ በሌላም ስፍራ እንዲሁ "ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲስ ምን እናገኝ ይሆን?" በማለት ይጠይቃል፡፡ /ማቴ.19/፡፡ ጌታ ግን ዋጋችሁ ሰማያዊ ክብራችሁ ዘላለማዊ ነው ሲል እስከ ፍጹማን መዓርግ ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ አድርሶ ብርሃነ መለኮትን ገልጦ ተስፋውን ነገራቸው፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ደቀ መዛሙርትም እናታቸውን ልከው ሹመት ሽልማት መዓረግ ለምነዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን በደብረ ታቦር "በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ነገር" ስለሞቱ እንዲነጋገሩ አደረገ፡፡ ሞቱ እርግጥ ሆነ ማለት ነው፡፡ አባቱም "ኦሆበልዎ ለክርስቶስ"፤ እሺ በሉት እርሱን ስሙት፡፡ ሞቱ እርግጥ በመሆኑ ከልባቸው እንዲጠፋ መርጦ ወደ ቅዱስ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡

"እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም" እንዲል፡፡ በእርሱ ዘንድ ወረት የለም፡፡ አስቀድሞ ከተዓምራቱ ከምሥጢሩ አይለያቸውም ነበርና ብርሃነ መለኮትን ለማየት አበቃቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለማወቅ፣ ለመማር፣ ለመጠየቅ ያሳዩት ትጋት ምስጢር ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህ ምስጢር ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦ የሚቀር አይደለም፡፡ እስከ ዓለም ፍፃሜ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሲገለጥ፣ በመረጣቸውም ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ ኪዳኑን የሚጠብቅ አምላክ ምስጢሩን ይግለጥልን፡፡

ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ "አልክድህም አልተውህም" የሚለው ቢወድደው አይደለምን? ፍቅሩን መግለጡ ለክብር አብቅቶታል፡፡ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም "ጥዋዬን ልትጠጡ አትችሉም" ቢላቸውም አንዳችን በቀኝ ሌላችን በግራ ሆነን አብረንህ እንሞታለን ሲሉ በምስጢር ለምነዋል፡፡ ሞታቸውን ከሞቱ ጋር መደመራቸው ፍቅራቸውን መግለጣቸው ነው፡፡

ከተራራው ግርጌ 

ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ "አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል" በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ "... በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ ... በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል ...." በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14÷1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረውነ ይሁዳ ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡

"የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ" የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ሊለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል ጥበብ ይህን አደረገች፡፡ 8 ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም "ልበ ንጹሐን ብፁአን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና" /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ "ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና" እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡

የተራራው ምስጢር



ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጌታችን ብርሃንነት "በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ" "ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ" "እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" "በሞት ጥላ መካከል ላሉ ብርሃን ወጣላቸው" ... በማለት መስክሯል፡፡ ፀሐየ ጽድቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች የተስፋ ብርሃን፣ የእውቀት ብርሃን፣ የዓይን ብርሃን፣ የሕይወት ብርሃን ነው፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትንም ብርሃን ያለበሰ እርሱ ነው፡፡ ለመላዕክት፣ ለጻድቃን ለቅዱሳን ሁሉ የጽድቅ ብርሃንን ያደለ የማይጠፋ ብርሃን እርሱ ነው፡፡

በጻድቁ አባት በገብረ መንፈስ ቅዱስ ገድል እንደምናነበው ለጻድቁ የጽድቅ ምስክር ሆኖ ለረዥም ጊዜ የቆየውን ዓይነት ብርሃን አይደለም፡፡ አባ አትናቴዎስ ስለ ንስሃውና እመቤታችንን ስለ መውደዱ ካገኘው ብርሂት እድ ጋር እንዴት እናነጻጽረዋለን? ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከተራራው በወረደ ጊዜ የእስራኤልን ዐይን የበዘበዘ ገጸ ብርሃን ምሳሌው ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ ለቅዱሳን ብርሃንን የሚሰጥ የብርሃናት አምላክ፣ ሙሴን ብሩህ ያደረገ፣ ለአባ አትናቴዎስም ብርሂት እድን የሰጠ... ነው እንጂ፡፡ በቅዱሱ ተራራ ማደሪያውን ያደረገ አምላክ በዚህ ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ፡፡

ይህን ልዩ ምስጢር በገለጠባት ቅዱስ ተራራ ደጋግሞ የአብን ምክር ሰማን አብ በደመና "የምወደው የምወልደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙት" ብሏልና፡፡ በከዊን /ከዊነ ቃል ከዊነ ልብ ከዊነ እስትንፋስ/ ሦስት ሲሆኑ በኩነት አንድ ናቸውና በደብረ ታቦር ልብሱ እንደ በረዶ ነጥቶ በአካለ ሥጋ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠው ወልድ ቃልነት አብ በደመና "የምወደው የምወልድ ልጄ" በማለት መሰከረ፡፡

ሙሴ ወ ኤልያስ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋንም የሙታንም አምላክ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ያስመሰከረውም ይኸንኑ ነው፡፡ ወንጌልም ስለምስክርነታቸው ሲናገር "በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ተነጋገሩ" ይላል፡፡ አስቀድመው በፊልጶስ ቂሣርያ ሙሴ፣ ኤልያስ ይሉሃል ብለውት ነበር፡፡ ሙሴ "የኔን የሙሴን አምላክ እንዴት ሙሴ ‹‹ሰው፣ ሩቅ ብእሲ፣ መዋቲ..../ ነህ ይሉሃል ? እኔ ባሕር ከፍዬ ባሻግር፣ ከዐለት ውኃ ባፈልቅ.... እስራኤልን ከዳግመኛ ሞት ላድናቸው ያልተቻለኝን፡፡ አንተ ከዘለዓለም ሞት የምትቤዥን ነህ" በማለት መስክሮለታል፡፡

ኤልያስም የእኔን የኤልያስን አምላክ እንዴት ኤልያስ /የሕያዋን ብቻ፣ የነፍስ ገዥ ብቻ/ ነህ ይሉታል? እኔ እሳት ከሰማይ ባወርድ ከሰጠኸኝ ነው፡፡ አንተ በሞትህ ዓለምን የምታድን ነህ ሲል መስክሮአል፡፡

ከዚህ ምስክርነትና መገለጥ የተነሣ አንተ ስንሞት እያስነሳኸን፣ ሕብስት እያበረከትህ እያበላኸን፣ ሙሴ መና እያወረደ ደመና እየጋረደ ከጠላት እየተጋደለ፣ ኤልያስ እሳት እያዘነመ ቤት /ዳስ/ ሠርተን በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ የሚጠይቁን ሰዱቃውያን፣ የሚያሳድዱን ጸሐፍት ጋር ምን አጣላን በዚህ እንቆይ በማለት እስኪመኝ አደረሰው፡


ትውፊቱ

ቡሄ

ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡

ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ "ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት" እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም "ቡኮ/ሊጥ" ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት "ሙልሙል" የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡

ጅራፍ

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ እና ጀራፍ ማጮኸ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፊቱን እና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምሰክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡

የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኀበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡


ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የት መጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡

የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡

ሙልሙል

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን "ቡሄ" እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ "ሙልሙል" ዳቦ አለ፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያት ምስራች ሊነግሩን፣ ወንጌል ሊሰብኩን በደጃፋችን ቆመው "ቡሄ በሉ" የሚሉንን አዳጊዎች የሚበሉትን መስጠታችን ምሳሌያዊ /መጽሐፋዊ/ ነው፡፡ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ባስተማራችሁበት፣ በደረሳችሁበት ተመገቡ ብሏቸዋል፡፡ /ማቴ 10÷12/ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት "የምስች" ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው "ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ...." ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምስጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምስጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ "ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ" ብለው ይጀምሩታል፡፡ ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡ አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ቤተክርስቲያን የምስጢር ግምጃ ቤት ናት የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ይህንን አውቀን ተረድተን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፋ እንችል ዘንድ ከክፉ ጠላት ከሰይጣን ፈተና፣ በሽታ ከመሳሰሉት ችግሮች ለመዳን ወደ ተራራዋ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሸሽ ከክፉ ነገሮች ሁሉ ማምለጥ ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚጠለሉ ሁሉ ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ አስተዋዮችም ይሆናሉ ሁሉን ማየትና የሚጠቅማቸውን መምረጥ ይችላሉ በሥነ-ምግባር የታነፁ አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጠጋት ከክፉ ሁሉ የሚያመልጡ ይሆናሉ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

Monday, August 17, 2015

ነሐሴ 7 ጽንሰታ ማርያም



ከእመቤታችን 33ቱ ባዓላት አንዱና የመጀመሪያው ነው፤ ይኸውም የተጸነሰችበት ነው፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ፍቅር ከሚቀዘቅዝበት ጭካኔ ከሚነግስበት ከስምንተኛው ሺ ዘመን አታድርሰኝ የዛን ዘመን እህል አታቅምሰኛ ውኃም አታጠጣኝ ብሎ ሲጸልይ የነበረው ጻድቁ ንጉስ አጼ ናኦድ ስምንተኛው ሺ መስከረም አንድ ሊጀምር እርሱ በዛሬዋ ቀን ዓለም ከተፈጠረ በ 7000 ዘመን አረፈ (5500 +1500)
ነሐሴ 7 በዚህች ዕለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተጸነሰች::የእመቤታችን ወላጆችዋ ኢያቄም እና ሃና ይባላሉ:: እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፤ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑዋሉ:፡ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ ፡-
ኢያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ አትጣለኝ አትናቀኝ ፀሎቴን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ፤ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:፡
ሃናም በበኩሏ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ:ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋየምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች:፡ እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቿጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች:፡እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተእግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ(ውሃ) ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስዕለት ገቡ:: ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስእለታችሁን ይቀበልላችሁ ብሎ አሳረገላቸው።
ከዚያም በሁአላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት ፤
ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ይህንን ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ዕለት ነው:: እነሱም እንዲ ያለ ራዕይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፤ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆን ብለው አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራት በፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን ተፀነሰች፡: ምልጃዋ በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን:: ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡



ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Thursday, August 6, 2015

ሥርዓተ ሱባዔ


ሱባኤ፣ምንነቱ፣ሥርዓቱ 


ሥርዓተ ሱባዔ

ሱባዔ ምንድን ነው? ሱባዔ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ሽለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.2.2፤ መዝ.118.164፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም «አንድ ሱባዔ ጾመ» ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም «ሁለት ሱባዔ ጾመ» እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ 

መቼ ተጀመረ?

ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ «መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡» ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ «ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ» ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምጦስ አንቀጽ አራት/፡፡

ሱባዔ ለምን?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ «በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?» እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡

ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሽክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡

እግዚአብሔርን ለመማፀን

ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው /የምንማፀነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡

ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- «ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው?» በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ «ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝ?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማፀነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡

«አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት አድሯል፡፡ በነጋው «ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ሽለሙን መስዬ እኖራለሁ» አለው፡፡ «እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን» ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ «ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ» የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡

ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ «ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ» የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ «ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ» /ኢሳ.56.6/ በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የተለያዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል /ለመሳተፍ/ የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ 

ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ በምዕራፍ 2.9 እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት የሚኖር መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን

በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብፁን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርንና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዘፍ.41.14-36፡፡ ዳን.4.9፤ ዳን.5.4፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ሆነ በመላው ሽክም ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው «እንዲህ ይሆናል» የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማፀኑ ነበር፡፡ ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጸው ይናገሩ ነበር፡፡ ዳን.5.28፡፡

እንዲሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል፡፡ መዝ.8.1፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ 1-14 የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡

«እመቤታችን ያረፈችው ጥር 21 ቀን 50 ዓመተ ምሕረት ነው፡፡ ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴ ሰማኔ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ በታተኗቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወስደው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡» /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡ በዚህ ጊዜ እነርሱ ተደናግጠው ስለተበታተኑ የእመቤታችን የዕረፍቷ ያስጨንቃቸው ነበር፡፡ 
«ቅዱስ ዮሐንስ በተመስጦ እየሄደ ሥጋዋን ያጥን ነበር፡፡ ለሐዋርያት ይህን ይነግራቸዋል፡፡ ለዮሐንስ ተገልጣ ለእኛ ሳትገለጥ ብለው በነሐሴ ሱባዔ ገቡ፡፡ ሁለተኛው ሱባዔ ሲፈጸም በ14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸዋል፤ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ ዐርጋለች፡፡ /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡

እንግዲህ ለቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን የዕርገቷን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን የሱባዔ ወቅት ሕፃናትም ሳይቀሩ ይሳተፉታል፡፡ 

ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6፤ ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡» እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ «በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየኸ በአምስት ቀን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ 

በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ «እነሆ አድንኀለሁ» ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡- «ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን» በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አዳምን በመከተል ልጆቹም አበው ቅዱሳን ነቢያት ሱባዔ በመግባት የተስፋን ዘመን በመቁጠር በመልካም ግብር ተከትለውታል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ነቢያት በተለያየ ስልት ሱባዔ ቆጥረዋል፤ እኛም ሱባዔ ከቆጠሩ ነቢያት የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ «ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡» ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ ቁ.14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡

ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35'19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685'12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡ 

ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡ «እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ሺ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን»፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 1140’7= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ «ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡» ይኸውም ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም «እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች» ሲል ተናግሯል፡፡

የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7’70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡ 

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

የሱባዔ ዓይነቶች

የግል ሱባዔ/ዝግ ሱባዔ/

የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በኣቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው፡፡ ማቴ.6፡5-13፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በኣቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም፡፡ መዝ. 101-6-7፡፡

የማኅበር ሱባዔ

የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ.1፡9፤ መዝ.121፡1፤ ሉቃ.18፡10-14፡፡ 

በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባኤ ይያዛል፡፡.

የዐዋጅ ሱባዔ

የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲነደ እንዲሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የሆነ መቅሰፍት ሲከሰት፣ እግዚአብሔር መሽቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ እስራኤላውያን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሦስት ቀን ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ አድርገዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አርጤክስስ አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማፅነዋል፡፡ አስቴር 4፡16 - 28፡፡

በአገራችንም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፡- «ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ» በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፤ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ያስደነቀ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሱ የሚያስችል ፋና ወጊ የሆነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ነው፡፡ 

ቅድመ ዝግጅት

ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡ 

ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/

በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡

ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው «በዋሻ እዘጋለሁ» ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዐቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡

ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ «ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም» የሚል አቋም ለመያዝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡

ጊዜ ሱባዔ /በሱባዔ ጊዜ/

በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡

በሱባዔ ወቅት በቅደም ተከተል መጸለይ አለብን፡፡ መጀመሪያ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አአትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀልኸ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንዱ አምላክ መላ ሰውነቴን በትእምርተ መስቀል አማትባለሁ» እያለ ሰጊድን ከሚያነሣው ሲደርስ መስገድ መስቀልን ከሚያነሣ ላይ ስንደርስ ማማተብ ይገባል፡፡

በማስከተል አቡነ ዘበሰማያት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች በመዝገበ ጸሎት የተካተቱትን መጸለይ፤ ቀጥሎ አቡነ ዘበሰማያት፣ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ከጸለይን በኋላ አቡነ ዘበሰማያት መድገም፤ ከዚያ 41 ጊዜ ኪርያላይሶን ይባላል፡፡ ሌላው በሱባዔ ጊዜ ከተሐራሚ የሚጠበቀው ነገር ኃጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ነው፡፡ ሲያለቅስም ለእያንዳንዱ በደል እንባ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡ 

በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡ 

ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/

ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ሱባዔ የገባ ሰው ሁሉ ራእይ ላያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የኅሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡ 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Soruce: http://eotc-mkidusan.org/site/index.php?option=com_content&task=view&id=161&Itemid=26


ጾመ ፍልሰታ

ጾመ ፍልሰታ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም


<ፍልሰታ > የሚለው ቃል የሚገልጸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለቆ መሔድን መሰደድን መፍለስን ያመለክታል :: ይህም የእመቤታችንን ሥጋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን
ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡ ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 3፡7 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የመወደድ ሞገስ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሣረግ የእናትነት ሥራ ሥትሠራላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን /የተቀበለችውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በዐራቱ ማእዘን «ሰዓሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን» የማይላት የለም፡፡


በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው «የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደምግብ ተመግቤው» እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ያዘጋጁላትን፣ አባ ጽጌ ድንግል የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችን ዘወትር መማጸን የቀደምት ኢትዮጵያውያንም የዛሬዎች ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ግብር ነው፡፡


ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት ሆኗ እንድታገለግል በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር አስረክቧል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅሪት እናት አማላጅ መሆኗን አሳይቷል፡፡ «ለዚሁም የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል» ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ምስክር ነው፡፡ እናት ሆኗ እንድታጽናናቸው በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ከእግረ መስቀሉ ስር ሰባቱን አጽራሐ መስቀል ሲያስተጋባ ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ «እኖኋት እናትህ፤ ድንግል ማርያምን ጠርቶ እነሆ ልጅሽ» ዮሐ. 19፡26፡፡ በማለት እመቤታችን የእናት ሥራ ለሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት እንድትሠራላቸው ምእመናንም ልጅ እንዲሆኗት በማያሻማ ቃሉ ተናግሯል፡፡


ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ በቤታቸው አኑረዋታል፤ ብትሠወርባቸው ፈልገዋታል፡፡ ብትርቃቸው ናፍቀዋታል፡፡ እርሷም ሲጠሯት ታደምጣቸዋለች፣ ሲፈልጓት ትገኝላቸዋለች፡፡ ይኸውም የሆነው ልጇ በአዳምና በልጆቿ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ ብትቀምስ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያት መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴ ሰማኒ እንደቀበሯት ስለ እመቤታችን የተጻፉ መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡


የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍት «ከመ ትንሣኤ ወልዳ» እንደ ልጇ ትንሣኤ ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሰረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ እማኝ ደግሞ የተከፈነችበትን በፍታ /ጨርቅ/ ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲገለጥላቸው ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው፡፡ ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡


እነዚህ በቅድስናቸው የተመሠከረላቸው ቅዱሳን እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ከነሐሴ 1-16 በየዓመቱ አንደሚጾም ይታወቃል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሄ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት ሰዓት ነው ብለን እናምናለን፡፡


ኢትዮጵያ የእመቤታችን አሥራት አገር ስትሆን እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን እናት መሆኗ እየተነገረ ለምን በፈተና ውስጥ አለፍን? ልጇ በአሥራት ኢትዮጵያን የሰጠባት ሀገር አባቶች ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መንፈሳዊነት /ኀይለ መንሳዊ/ ተዘንግቶ ሥጋዊ ጥበብ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ሲታይ ምን ይባላል? «እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ» ማቴ. 24፡15፡፡ የተባለው ቀን ደርሶ ይሆንን?


ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት ለገጠማት ችግር መፍትሔ እመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ብትሠወርባቸው አባቶች ሱባዔ ገብተው እንዳገኟት የፍቅር እናት ናትና ፍቅር አንድነት እንድትሰጠን እርሷን መማጸን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን እንድትሞላ ውዳሴዋን እየደገሙ ድንግልን መማጸን ያስፈልጋል፡፡


በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጉልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍ አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በዚህ በወርኀ ጾም እመቤታችን ምልጃዋ ከአገራችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር እንዲሆን በሱባዔ እንማጸናት፡፡


በጾመ ፍልሰታ ከሊሂቅ እስከ ደቂቅ በማስቀደስ፣ በጾምና በጸሎት ሁለቱን ሳምንታት እንደሚያሳልፉት ይታወቃል፡፡ በሱባዔው የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች የሚወገድበት ምእመናን በበረከት የሚጐበኙበት ቅድስና የሚሰፍንበት መንፈሳዊነት ትልቅ ከበሬታ የሚገኝበት ጾም እንዲሆን ሁሉም ምእመን መትጋት አለበት፡፡


ሁለቱ ሳምንታት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር፣ የበደልነውን የምንክስበት ጾም መሆን አለበት፡፡


ቀናቱን እየቆጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ እመቤታችን የአገራችን አሥራት የሁላችን እናት በመሆኗ የእናትነት ሥራ እንድትሠራልን በሚገባ ልንማጸናት ይገባል እንጂ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ብለን ውዳሴ ማርያም በደገመ አፋችን ሰው የምናማ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከሆነ እመቤታችንን አናውቃትም፡ እመቤታችንም አታውቀንም፡፡ ስለዚህ ጾመ ፍልሰታን እስኪ ሁላችን ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች ድንግልን በአንድ ድምፅ እንጥራት፡፡


የእመቤታችንን ጾመ ፍልሰታ፤ እንደ ብርሃን ተስፋ በማድረግ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ይማጸኑ እንላለን፡፡ ውዳሴ ማርያሙ፤ ሰዓታቱ ጨለማን ተገን አድርጐ ከሚቃጣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ድርብ ኀይል አለው፤ እስኪ ለቅድስና፣ ለንጽሕና ለመንፈሳዊነት ቅድሚያ እንስጥና የእግዚአብሔርን ብድራት እንጠብቅ፡፡ ጾመ ፍልሰታ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና የጠራ አሠራር፣ በቤተ ክርስቲያን የሚሰፍንበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡ 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር